የአልኮል መጠጦች ቢጠጡ ምን አለበት?
ምዕራፍ 33
የአልኮል መጠጦች ቢጠጡ ምን አለበት?
‘የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ስህተት ነውን? በእርግጥ ይጎዳልን? ወይስ መጥፎ የሆነው ለአዋቂዎች ሳይሆን ለወጣቶች ብቻ ነው?’ እነዚህ ጥያቄዎች በአእምሮአችሁ ይጉላሉ ይሆናል። ደግሞም ወላጆቻችሁ የአልኮል መጠጥ ተገዢዎች ይሆኑ ይሆናል። በእናንተ ዕድሜ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች (መጠጣት በሚፈቀድበት ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እንኳን) ይጠጣሉ። የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች የአልኮል መጠጥ መጠጣትን በጣም ጥሩ ነገር አድርገው ያቀርባሉ።
የአልኮል መጠጥ በልከኝነት ከተወሰደ በእርግጥም ደስ ሊያሰኝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ወይን የሰውን ልብ እንደሚያስደስት ወይም ደግሞ ለምግብ ጣዕም እንደሚጨምር ይገልጻል። (መክብብ 9:7) አለ አግባብ ከተወሰደ ግን ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከፖሊሶች ጋር ከመጋጨት ጀምሮ አለ ዕድሜ እስከ መሞት የሚያደርሱ ከባድ ችግሮችን ይፈጥራል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ወይን አሿፊ ነው፣ የሚያሰክር መጠጥም ሁከተኛ ነው። በእርሱም የሚሳሳት ሰው ጠቢብ አይደለም።” (ምሳሌ 20:1 አዓት) ታዲያ የአልኮል መጠጥ ስለመጠጣት ኃላፊነት የሚሰማችሁ ሰዎች መሆናችሁን የሚያንጸባርቅ ውሳኔ ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው።
ይሁን እንጂ ስለ አልኮል መጠጥና ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች የምታውቁት በእርግጥ ምን ያህል ነው? የሚቀጥሉት የመፈተኛ ጥያቄዎች ምን ያህል እውቀት እንዳላችሁ እንድትገመግሙ ያስችሏችኋል። በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ እውነት ወይም ሐሰት የሚል ምልክት አድርጉባቸው፦
1. የአልኮል መጠጦች በአብዛኛው መንፈስ የሚያነቃቁ ናቸው․ ____
2. አልኮልን በማንኛውም መጠን መውሰድ ለሰውነት ጎጂ ነው․ ____
3. ሁሉም የአልኮል መጠጦች ማለትም ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያላቸው እንደ ዊስኪና አረቄ ያሉት መጠጦች፣ የወይን ጠጅ፣ ቢራና የመሳሰሉት ወደ ደም ሥሮቻችሁ ገብተው ከሰውነታችሁ ጋር የሚዋሃዱበት ፍጥነት እኩል ነው․ ____
4. አንድ ሰው ከሰከረ ቡና ቢጠጣ ወይም በቀዝቃዛ ውኃ ገላውን ቢታጠብ ስካሩ ቶሎ ሊበርድለት ይችላል․ ____
5. መጠኑ አንድ ዓይነት የሆነ የአልኮል መጠጥ የጠጡ ሰዎች ሁሉ በመጠጡ ምክንያት የሚሰማቸው ስሜት አንድ ዓይነት ነው․ ____
6. ስካርና የአልኮል ሱሰኛ መሆን አንድ ናቸው․ ____
7. የአልኮል መጠጦችና እንቅልፍ አስወሳጅ መድኃኒቶች (እንደ ባርቢቹሬትስ ያሉት) አንድ ላይ ሲወሰዱ አንዳቸው የሌላውን ውጤት ያበዛሉ․ ____
8. አንድ ሰው የሚጠጣውን መጠጥ እያቀያየረ ቢጠጣ ቶሎ አይሰክርም․ ____
9. ሰውነታችን የአልኮል መጠጦችን የሚያዋህደው ልክ እንደ ምግብ ነው․ ____
አሁን መልሶቻችሁን በገጽ 270 ላይ ከተሰጡት ጋር አስተያዩ። ስለ አልኮል መጠጦች ያሏችሁ አንዳንድ ግንዛቤዎች ስህተት ሆነው አገኛችኋቸው? ከሆነ የአልኮል መጠጦችን አስመልክቶ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ አላዋቂ መሆን ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዘቡ። መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ አለ አግባብ ከተጠቀሙበት “እንደ እባብ ይነድፋል፣ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል” በማለት ያስጠነቅቀናል።— ምሳሌ 23:32
ለምሳሌ ያህል ጆን ገና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ እያለ ሚስት አገባ።
አንድ ቀን ማታ ከወጣት ሚስቱ ጋር ከተጣላ በኋላ ለመስከር ቆርጦ ከቤቱ በቁጣ ወጣ። ግማሽ ጠርሙስ የሚያክል ቮድካ ጭልጥ አድርጎ ከጠጣ በኋላ ራሱን ስቶ ወደቀ። ሐኪሞችና ነርሶች ሕይወቱን ለማትረፍ ባይረባረቡለት ኖሮ ሊሞት ይችል ነበር። ከፍተኛ መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ በጥድፊያ መጨለጥ ለሞት ሊያደርስ እንደሚችል እንዳላወቀ ግልጽ ነው። አለማወቁ ሕይወቱን አሳጥቶት ነበር።የአልኮል መጠጥ ጭንቀት ያባብሳል
የአልኮል መጠጥ ከሚያስከትላቸው መሠሪ መዘዞች አንዱ ይህ ነው። አልኮል የሰውነትን የአሠራር ቅልጥፍና የሚቀንስ እንጂ የሚያነቃቃ አይደለም። ከጠጣችሁ በኋላ የተነቃቃችሁ መስሎ የሚሰማችሁ አልኮል የጭንቀታችሁን መጠን ስለሚቀንሰው ወይም ስለሚያረግበው ነው። ሰውነታችሁ ዘና ይላል። ከመጠጣታችሁ በፊት የነበራችሁ ጭንቀት ይቀንሳል። ስለዚህ የአልኮል መጠጥ በልከኛ መጠን ከተወሰደ አንድ ሰው በመጠኑም ቢሆን ‘ሥቃዩን እንዲረሳ’ ሊረዳው ይችላል። (ምሳሌ 31:6, 7) ለምሳሌ ያህል ፖል የተባለ አንድ ወጣት የቤተሰቡን ችግር ለመርሳት ሲል አብዝቶ ጠጣ። “የአልኮል መጠጥ ከሚሰማኝ ጭንቀት የምገላገልበት መንገድ መሆኑን ያወቅሁት ገና ድሮ ነው፣ አእምሮዬን ያዝናናልኛል” በማለት ያስታውሳል።
ታዲያ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ምንም ጉዳት አያደርስም፣ አይደል? አዎን፣ ብላችሁ ከመለሳችሁ ተሳስታችኋል! አልኮል ቀደም ሲል የነበረውን የጭንቀት ስሜት የማባባስ ጠባይ አለው። አንድ ሁለት ሰዓት ካለፈ በኋላ የማዝናናት ውጤቱ ያልፍና ጭንቀታችሁ ይመለስባችኋል። አሁን የሚመለሰው ግን በፊት ወደነበረበት መጠን አይደለም። ከመጠጣታችሁ በፊት ከነበረው መጠን በጣም ይባባሳል። ከወትሮው የበለጠ ጭንቀት ወይም ውጥረት ይሰማችኋል። የአልኮሉ ውጤት ከሰውነታችሁ እስኪወጣ ድረስ 12 ሰዓት ሊቆይ ይችላል። እርግጥ ደግማችሁ ከጠጣችሁ የጭንቀታችሁ መጠን ተመልሶ ሊወርድ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁለት ሰዓት
ከሚያክል ጊዜ በኋላ የጭንቀቱ መጠን ተመልሶ ከፍ ይልባችኋል። በዚህ ጊዜ ደግሞ መጠኑ ከበፊቱ ሁሉ የበለጠ ይሆናል! በዚህ ዓይነት ማቋረጫ በሌለው የጭንቀት ማሻቀብና ማሽቆልቆል ሽክርክሪት ውስጥ ትገባላችሁ።ስለዚህ የኋላ ኋላ አልኮል ጭንቀታችሁን ፈጽሞ የማይቀንስ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። እንዲያውም ጭንቀታችሁን ሊጨምርባችሁ ይችላል። የአልኮሉ ውጤት ሲለቃችሁ ችግራችሁ እዚያው የነበረበት ቦታ ሆኖ ይጠብቃችኋል።
በስሜት ቀጭጮ መቅረት
የአልኮል መጠጥ ሥራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲሠሩ እንደሚረዳቸው የሚናገሩ ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ዴኒስ በጣም ዓይን አፋር ስለነበረ ከሰዎች ጋር ትንሽ እንኳን መጫወት ከባድ ሆኖበት ነበር። በኋላ ግን አንድ መላ አገኘ። “ትንሽ ከጠጣሁ በኋላ ሰውነቴ ዘና ይላል” ብሏል።
ችግሩ አንድ ሰው ብስለት የሚያገኘው ዴኒስ እንዳደረገው ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች በመሸሽ ሳይሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ መሆኑ ነው። በወጣትነት ዕድሜያችሁ የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች ለማሸነፍ መጣራችሁ ወደፊት ትልልቅ ሰዎች ስትሆኑ የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች የምታሸንፉበትን ልምምድ ይሰጣችኋል እንጂ አይጎዳችሁም። በመሆኑም ዴኒስ የኋላ ኋላ የአልኮል መጠጥ የሚያስገኝለት ጊዜያዊ ውጤት ዓይን አፋርነቱን ለማሸነፍ እንዳልረዳው ተገነዘበ። “የአልኮሉ ውጤት ሲለቀኝ ወደነበርኩበት ጉድጓድ እገባለሁ” በማለት ገልጿል። ዴኒስ ዛሬ ብዙ ዓመታት ካሳለፈ በኋላ እንዴት ሆኖ ይሆን? በመቀጠል “በራሴ እውነተኛ ችሎታ ሐሳቤን ለሰዎች እንዴት እንደምገልጽ እስከ ዛሬ አልተማርኩም። በዚያው ቀጭጬ የቀረሁ ይመስለኛል” ብሏል።
የአልኮል መጠጦችን እንደ ጭንቀት መቋቋሚያ ምርኩዝ አድርጎ መጠቀምም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ሳለች እንዲህ ታደርግ የነበረችው ጆን እንደሚከተለው በማለት ሐቁን አምናለች፦ “በቅርቡ በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ባጋጠመኝ ጊዜ ‘አሁን ብጠጣ ጥሩ ነበር’ ብዬ አሰብኩ። በመጠጥ ኃይል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠር የምትችሉ ይመስላችኋል።” ግን ነገሩ እንዲህ አይደለም!
በኒው ዮርክ ስቴት ጆርናል ኦቭ ሜዲስን ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ እንደሚከተለው ብሏል፦ “አደንዛዥ ዕፆች [የአልኮል መጠጥ ጭምር] በትምህርት፣ በማኅበራዊ ኑሮ ወይም ከግለሰቦች ጋር ባለን ግንኙነት
ረገድ የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለማቃለል የሚያስችሉ ዘዴዎች ተደርገው በሚወሰዱበት ጊዜ ጤናማ የሆኑ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችሉ ችሎታዎችን የመማር አስፈላጊነት ይቀንሳል። የዚህ ውጤት ደግሞ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት አስቸጋሪ እስከሚሆንበትና ግለሰቡ ከሌሎች የተገለለ እንደሆነ እስከሚሰማው የጉልምስና ዘመን ድረስ ላይታወቅ ይችላል።” ችግሮችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማሸነፍ እጅግ የተሻለ ይሆናል!“እርሱ ግን አልጠጣም”
የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ተከተሉ። በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት በጣም አስጨናቂ የሆነ የመከራ ጊዜ አጋጥሞት ነበር። ኢየሱስ አልፎ ከተሰጠና ከተያዘ በኋላ የተደረጉበትን ተከታታይ ምርመራዎችና የሐሰት ክሶች ታግሦ አሳልፏል። በመጨረሻም ሌሊቱን በሙሉ ሳይተኛ አድሮ ለስቅላት አልፎ ተሰጠ።— ማርቆስ 14:43 እስከ 15:15፤ ሉቃስ 22:47 እስከ 23:25
ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ስሜቱን የሚያደነዝዝለት ነገር፣ ማለትም የደረሰበትን አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያቀልለት ስሜት የሚያደነዝዝ ነገር ቀርቦለት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም” በማለት ይገልጻል። (ማርቆስ 15:22, 23) ኢየሱስ አእምሮውንና ስሜቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ፈልጎ ነበር። የደረሰበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በታማኝነት ለመጋፈጥ ፈለገ። ከችግር የሚሸሽ ሰው አልነበረም! ይሁንና በኋላ ጥማቱን የሚያረካለት ምንም ዓይነት ማደንዘዣ መድኃኒት ያልተቀላቀለበት ትንሽ የወይን ጠጅ በቀረበለት ጊዜ ተቀብሎ ጠጥቷል።— ዮሐንስ 19:28–30
እናንተን የሚያጋጥሟችሁ ችግሮች ወይም ጭንቀቶች በኢየሱስ ላይ ከደረሱት ጋር ሲወዳደሩ ከቁም ነገር የማይገቡ ናቸው። ቢሆንም ከኢየሱስ ተሞክሮ ጠቃሚ ትምህርት ልታገኙ ትችላላችሁ። ችግሮቻችሁን፣ ጭንቀቶቻችሁንና አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የአልኮል መጠጦችን የመሰሉ ስሜት የሚያደነዝዙ ነገሮችን ከመውሰድ ይልቅ ፊት ለፊት ብትጋፈጡአቸው በጣም የተሻለ ይሆንላችኋል። የኑሮን ችግሮች በመጋፈጥ ረገድ ተጨማሪ ተሞክሮ ባገኛችሁ መጠን ችግሮችን የመፍታት ችሎታችሁ እየዳበረ ይሄዳል። ጤናማ የሆነ ስሜታዊ ብስለት ያላችሁ ሆናችሁ ታድጋላችሁ።
ሕጋዊ ዕድሜ ላይ ስትደርሱ አልፎ አልፎና በልከኝነት ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት የመምረጡ ጉዳይ የእናንተው (ምናልባትም የወላጆቻችሁ) ውሳኔ ይሆናል። ውሳኔያችሁ በእውቀት ላይ የተመሠረተና በአስተዋይነት የተደረገ ይሁን። ላለመጠጣት ብትመርጡ ምንም ዓይነት ጥፋት እንደሠራችሁ ሊሰማችሁ አይገባም። ሕጋዊ ዕድሜ ላይ ደርሳችሁ ለመጠጣት ከወሰናችሁ ግን ኃላፊነት የሚሰማችሁ መሆናችሁን በሚያሳይ መንገድ ጠጡ። ከችግር ለመሸሽ ወይም የውሸት ድፍረት ለማግኘት ብላችሁ አትጠጡ። “ብዙ መጠጣት ጯሂና ቂል ያደርግሃል። መስከር ደደብነት ነው” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግልጽና ቀጥተኛ ነው።— ምሳሌ 20:1 ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ብዙ ወጣቶች የአልኮል መጠጦችን የሚጠጡት ለምንድን ነው?
◻ ስለ አልኮል መጠጥ አንዳንድ ስህተት የሆኑ የተለመዱ ግንዛቤዎች ምንድን ናቸው?
◻ ጠጥቶ መኪና መንዳት የሚያመጣቸው አንዳንድ አደጋዎች ምንድን ናቸው?
◻ የአልኮል መጠጥን ከችግር መሸሻ አድርጎ መጠቀም ምን ዓይነት አደጋዎች ያስከትላል?
◻ አንድ ወጣት ችግር ሲያጋጥመው ምን ማድረግ አለበት? ለምንስ?
[በገጽ 268 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአልኮል መጠጥ አንድ ሰው የውሸት ስሜታዊ ደስታና ትካዜ እንዲፈራረቁበት ስለሚያደርግ በቀላሉ ሊላቀቅ በማይችለው ሽክርክሪት ውስጥ ያስገባዋል
[በገጽ 271 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በራሴ እውነተኛ ችሎታ ሐሳቤን ለሰዎች እንዴት እንደምገልጽ እስከ ዛሬ አልተማርኩም። በዚያው ቀጭጬ የቀረሁ ይመስለኛል”—በአፍላ የጉርምስና ዕድሜው የአልኮል መጠጥ አለ አግባብ ይጠጣ የነበረ ወጣት የተናገረው
[በገጽ 264 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘መጠጣት የጀመርንበት ምክንያት’
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ሳሉ ጠጪዎች ከነበሩ ወጣቶች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
ጠያቂ፦ ትጠጡ የነበረው ለምንድን ነው?
ቢል፦ መጀመሪያ ላይ መጠጣት የጀመርኩት ጓደኞቼ ጠጪዎች ስለነበሩ ነው። በተለይ ቅዳሜና እሑድ መጠጣት የተለመደ ነገር ነበር።
ዴኒስ፦ እኔ መጠጣት የጀመርኩት ዕድሜዬ 14 ዓመት አካባቢ ሲሆን ነበር። አባቴ ከባድ ጠጪ ነበር። በቤታችን ሁልጊዜ የመጠጥ ግብዣ ይደረግ ነበር። በልጅነቴ መጠጣት ማኅበራዊ ግዴታ እንደሆነ አድርጌ ተመለከትኩ። ከዚያም ከፍ ስል መረን ከተለቀቁ ልጆች ጋር ገጠምኩ። በልጆቹ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስል መጠጣት ጀመርኩ።
ማርክ፦ ስፖርት አዘወትር ነበር። በቅርጫት ኳስ ቡድን ውስጥ ከነበሩት ልጆች ጋር መጠጣት የጀመርኩት 15 ዓመት ሲሆነኝ እንደነበረ እገምታለሁ። መጠጣት እንድጀምር ያደረገኝ ዋናው ምክንያት አዲስ ነገር ለመሞከርና ለማወቅ የነበረኝ ጉጉት ነው ብዬ አስባለሁ።
ጆን፦ ቴሌቪዥን ላይ አያቸው የነበሩት ነገሮች በጣም ነክተውኛል። ተዋናዮቹ ሲጠጡ እመለከት ነበር። በጣም ጥሩ ነገር ይመስል ነበር።
ፓል፦ አባቴ የአልኮል ሱሰኛ ነበር። ብዙ ችግሮች የደረሱብን የአልኮል ሱሰኛ ስለነበረ እንደሆነ አሁን መገንዘብ ችያለሁ። የአልኮል ሱሰኛ ከመሆን ለመሸሽ እጣጣር ነበር። ግራ የሚገባ ቢሆንም ወደ መጠጥ ዞር ያልኩበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነበር።
ጆን፦ ወላጆቼ አብዛኛውን ጊዜ አብዝተው አይጠጡም ነበር። አባቴ ግን በግብዣዎች ላይ በጣም ብዙ መጠጣት እንደሚችል በጉራ ይናገር እንደነበረ ትዝ ይለኛል። እኔም ያንን አመለካከት ያዝኩ መሰለኝ፣ ልዩ ሰው እንደሆንኩ ማሰብ ጀመርኩ። አንድ ጊዜ ጓደኞቼና እኔ ከልክ ያለፈ ጠጣን። ለበርካታ ሰዓቶች አለማቋረጥ ጠጣን። በእርግጥም እንደ ሌሎቹ ልጆች አልሰከርኩም። ‘ልክ እንደ አባቴ ነኝ’ ብዬ ማሰብ እንደጀመርኩ ትዝ ይለኛል። አባቴ ስለ አልኮል የነበረው አመለካከት በእርግጥ ነክቶኛል ብዬ እገምታለሁ።
ጠያቂ፦ ብዙዎች እስኪሰክሩ ድረስ የሚጠጡት ለምንድን ነው?
ማርክ፦ እንጠጣ የነበረው ለዚሁ ነው። የምንጠጣው ለመስከር ብለን ነበር። እኔ ለጣዕሙ ምንም ደንታ አልነበረኝም።
ጠያቂ፦ ስለዚህ ስትጠጣ የነበረው መጠጡ ለሚሰጥህ ስሜት እንጂ ለጣዕሙ ስትል አልነበረም ማለት ነው?
ማርክ፦ አዎን።
ሀሪ፦ እኔም የምለው እንዲሁ ነው። አልኮል መጠጣት መሰላል ከመውጣት ጋር ይመሳሰላል። በጠጣህ ቁጥር ከፍ እያልክ ትሄዳለህ። ወደሚቀጥለው የመሰላሉ መወጣጫ ትሸጋገራለህ።
[በገጽ 270 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እውነት ወይም ሐሰት ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ (ገጽ 263)
1. ሐሰት። አልኮል ባመዛኙ ሰውነትን የማደንዘዝ ባሕርይ አለው። መጠጥ ስትጠጡ የሞቅታና የደስታ ስሜት የሚሰማችሁ ከመጠጣታችሁ በፊት የነበረባችሁ የጭንቀት ስሜት እንዲቀንስ በማድረግ የተዝናና መንፈስ እንዳላችሁ ሆኖ እንዲሰማችሁ ስለሚያደርግ ነው።
2. ሐሰት። በልክ ወይም አነስተኛ መጠን ያለው አልኮል መጠጣት በሰውነት ላይ ከባድ ጉዳት የሚያመጣ አይመስልም። ይሁን እንጂ ለረዥም ጊዜ አብዝቶ መጠጣት ልብን፣ አንጎልን፣ ጉበትንና ሌሎችንም የአካል ክፍሎች ሊጎዳ ይችላል።
3. ሐሰት። ከባድ የአልኮል መጠጦች ከወይን ወይም ከቢራ በበለጠ ፍጥነት ከሰውነት ጋር ይዋሃዳሉ።
4. ሐሰት። ቡና መጠጣት ሊያነቃችሁ፣ በቀዝቃዛ ውኃ ገላችሁን መታጠብ ደግሞ ሊያረጥባችሁ ይችላል። ቢሆንም አልኮል በአንድ ሰዓት 330 ሲ ሲ በሚያክል ፍጥነት በጉበታችሁ አማካኝነት ከሰውነታችሁ ጋር ተዋህዶ እስኪያልቅ ድረስ በደማችሁ ውስጥ ይቆያል።
5. ሐሰት። አልኮል የሚያስከትልባችሁ ውጤት በክብደታችሁና ምግብ መብላት አለመብላታችሁን በመሰሉ በርካታ ምክንያቶች ይነካል።
6. ሐሰት። ስካር የሚገልጸው ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣትን ነው። የአልኮል ሱሰኛ መሆን ግን በመጠጣት ረገድ ራስን ለመቆጣጠር አለመቻል ነው። ይሁን እንጂ የሚሰክር ሁሉ የመጠጥ ሱሰኛ አይደለም። የመጠጥ ሱሰኛ የሆነም ሁሉ ሰካራም አይደለም።
7. እውነት። አንዳንድ መድኃኒቶች ከአልኮል ጋር ሲደባለቁ ከአልኮሉ ወይም ከመድኃኒቱ ብቻ ከሚጠበቀው የተለመደ ውጤት እጅግ የበዛ ውጤት ያስከትላሉ። ለምሳሌ ያህል አልኮልን እንቅልፍ አስወሳጅ ወይም ሥቃይ አስታጋሽ ከሆኑ መድኃኒቶች ጋር መውሰድ ከባድ የሱስ ስሜት፣ ዐቅል መሳት ወይም ሞት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም አንድ ብርጭቆ መጠጥ ከአንድ እንክብል መድኃኒት ጋር መውሰድ ከምታስቡት የበለጠ ከፍተኛ ውጤት ሊያስክትል ይችላል። በእርግጥም የመድኃኒቱ ውጤት ሦስት እጥፍ፣ አራት እጥፍ፣ አሥር እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ ይሆናል!
8. ሐሰት። ስካር የሚመጣው ወደ ሰውነት በገባው የአልኮል ጠቅላላ መጠን ነው። የጂን፣ የዊስኪ፣ የቮድካ ወይም ሌላ ዓይነት የአልኮል መጠጥ መሆኑ ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም።
9. ሐሰት። አልኮል እንደ አብዛኞቹ ሌሎች ምግቦች ከሰውነት ጋር የሚዋሃደው በቀስታ አይደለም። ከተጠጣው አልኮል 20 በመቶ የሚሆነው ወዲያውኑ በጨጓራ ግድግዳዎች በኩል ወደ ደም ሥሮች ይገባል። የቀረው ደግሞ ከጨጓራ ወደ ትንሹ አንጀት ያልፍና ከዚያ ወደ ደም ይገባል።
[በገጽ 266, 267 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]
መኪና መንዳትና መጠጣት—ሞት የሚያስከትል ቅንጅት
“ሰክሮ መኪና መንዳት ከ16–24 ዓመት ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች መሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች የአንደኛነቱን ደረጃ ይዟል” ይላል የ1984 ሪፖርት ኦን ዘ ናሽናል ኮንፈረንስ ፎር ዩዝ ኦን ድሪንኪንግ ኤንድ ድራይቪንግ። በእርግጥም “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ወጣት በአልኮል ምክንያት የመጋጨት ዕድሉ ከሌሎች አሽከርካሪዎች ጋር ሲወዳደር በአራት እጥፍ የበለጠ ነው።” (ጀስት አሎንግ ፎር ዘ ራይድ) እንዲህ ዓይነቱ አላስፈላጊ እልቂት ከሚደርስባቸው ምክንያቶች አንዱ አልኮል ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች ብዙ እውነት ያልሆኑ አባባሎች ተስፋፍተው መገኘታቸው ነው። ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት፦
የሚባለው፦ የጠጣኸው ሁለት ቢራ ብቻ ከሆነ መኪና ብታሽከረክር ምንም አደጋ አያስከትልብህም።
ሐቁ፦ “በሁለት ባለ 355 ሲ ሲ ጠርሙስ ቢራ ውስጥ የሚገኘው አልኮል ከተወሰደ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የአሽከርካሪውን መኪና የመቆጣጠር ቅልጥፍና በሁለት አምስተኛ ሰኮንድ ይቀንስበታል። ይህ ማለት መኪናው 90 ኪሎ ሜትር በሰዓት የሚጓዝ ከሆነ መኪናውን ሙሉ በሙሉ ከማቆሙ በፊት 10 ሜትር ያህል ይሄድበታል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ግጭት ሊያስከትል ይችላል።— ደቨሎፕመንት ኦቭ ኤ ትራፊክ ሴፍቲ ኤንድ አልኮሆል ፕሮግራም ፎር ሲኒየር አዳልትስ፣ በጄምስ ኤል ማልፌቲ፣ ኢዲ ዲ፣ እና ዳርሊን ጄ ዊንተር፣ ፒ ኤች ዲ
የሚባለው፦ እንደሰከራችሁ እስካልተሰማችሁ ድረስ ብታሽከረክሩ ምንም ችግር አያጋጥማችሁም።
ሐቁ፦ በስሜታችሁ መተማመን አደገኛ ነው። አልኮል ደህና ነህ የሚል የተሳሳተ ስሜት ስለሚፈጥር አሽከርካሪው ችሎታዎቹ ሁሉ ቀንሰው ሳለ እርሱ ግን ነገሮችን መቆጣጠር የሚችል ሆኖ እንዲሰማው ያደርጋል።
አልኮል ጠጥቶ መኪና መንዳት ለማንኛውም ሰው አደገኛ ቢሆንም ለወጣቶች ደግሞ ይበልጥ አደገኛ ነው። አልኮል የጠጡ ወጣቶች መኪና የመንዳት ቅልጥፍናቸው “ከጎልማሶች ይልቅ ቶሎ ይቀንሳል። ምክንያቱም መኪና ማሽከርከር አዲስና ገና ሙሉ በሙሉ ያልተዋሃዳቸው ሙያ ስለሆነ ነው። በአጭሩ አብዛኞቹ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ተሞክሮ የሌላቸው አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተሞክሮ የሌላቸው ጠጪዎችም ናቸው። አልኮል መጠጣትና መኪና ማሽከርከር ሲዋሐዱ ደግሞ የባሰ ይሆናል።”—ሴኒየር አዳልትስ፣ ትራፊክ ሴፍቲ ኤንድ አልኮሆል ፕሮግራም ሊደርስ ጋይድ፣ በዳርሊን ጄ ዊንተር፣ ፒ ኤች ዲ የተዘጋጀ።
በተጨማሪም አንድን ወጣት የሚያሰክረው የአልኮል መጠን አንድን ጎልማሳ ሰው ለማስከር ከሚያስፈልገው የአልኮል መጠን ያነሰ ነው። ባጠቃላይ ሲታይ ወጣቶች ከጎልማሳ ሰዎች ያነሰ የሰውነት ክብደት አላቸው። የአንድ ሰው ክብደት ባነሰ መጠን ደግሞ የሚወሰደውን አልኮል ኃይል ለማዳከም የሚያስፈልገው በሰውነቱ ውስጥ ያለ ፈሳሽ አነስተኛ ነው። በደም ሥሮቻችሁ ውስጥ ያለው የአልኮል ክምችት ከፍተኛ በሆነ መጠን ስካራችሁም እንዲሁ ከፍ ያለ ይሆናል።
“ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ።” (ምሳሌ 22:3) ጠጥታችሁ መኪና ማሽከርከር ይህን ያህል አደገኛ ከሆነ ጠጥታችሁ ላለመንዳት ለራሳችሁ ቃል ብትገቡ “ብልህ” ሆናችሁ ማለት ነው። እንዲህ በማድረግም አካለ ስንኩል ከሚያደርግ ወይም ሞት ከሚያስከትል አደጋ ራሳችሁን ማዳን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሕይወትም አክብሮት ታሳያላችሁ።
በተጨማሪም (1) የሚያሰክር መጠጥ ጠጥቶ መኪና ከሚነዳ አሽከርካሪ ጋር ለመጓዝ ወደ መኪናው ላትገቡ እና (2) ጓደኛችሁም ቢሆን ሲጠጣ ከነበረ መኪና እንዲነዳ ላትፈቅዱ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይህም ጓደኛችሁን ያናድደው ይሆናል። ይሁን እንጂ የመጠጡ ሞቅታ ለቆት ወደ አእምሮው ሲመለስ ያደረጋችሁትን ነገር ሊያደንቅ ይችላል።— ከመዝሙር 141:5 ጋር አወዳድሩ።
[ሥዕሎች]
ሲጠጣ የቆየ ሰው ወደሚያሽከረክረው መኪና አትግቡ፤ እንዲሁም ጓደኛችሁ ሲጠጣ ከቆየ እንዲነዳ አትፍቀዱ
[በገጽ 262 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እኩዮች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና አንዳንድ ጊዜ ወላጆችም እንኳን ወጣቶች መጠጣት እንዲጀምሩ ተጽእኖ ሊያደርጉባቸው ይችላሉ
[በገጽ 265 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአልኮል መጠጥ አለ አግባብ ከተወሰደ ‘እንደ እባብ ሊናደፍ’ ይችላል
[በገጽ 269 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ መኪና መንዳት ብዙውን ጊዜ ይህን የመሰለ አደጋ ያስከትላል