ክፍል 9
እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ጠየቁ
የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ሳኦል ለይሖዋ ታዛዥ ሳይሆን ቀረ። ከሳኦል በኋላ ዳዊት የነገሠ ሲሆን አምላክ ከእሱ ጋር የዘላለማዊ መንግሥት ቃል ኪዳን አደረገ
ሳምሶን ከሞተ በኋላ ሳሙኤል በእስራኤል ነቢይና መስፍን ሆኖ ያገለግል ነበር። እስራኤላውያን እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ጊዜ ሳሙኤልን ጠየቁት። ይህ ጥያቄ ይሖዋን ቅር ያሰኘው ቢሆንም የፈለጉትን እንዲያደርግላቸው ለሳሙኤል ነገረው። አምላክ፣ ሳኦል የሚባል ትሑት ሰው ንጉሥ እንዲሆን መረጠ። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ትዕቢተኛ እንዲሁም የይሖዋን መመሪያ የማይታዘዝ ሆነ። ይሖዋም ሳኦልን ንጉሥ እንዳይሆን የናቀው ሲሆን በምትኩ ዳዊት የሚባለውን ወጣት እንዲቀባ ለሳሙኤል ነገረው። ይሁንና ዳዊት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከመጀመሩ በፊት ዓመታት ማለፍ ነበረባቸው።
ዳዊት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በሳኦል ሠራዊት ውስጥ ያገለግሉ የነበሩትን ወንድሞቹን ለመጠየቅ ሄደ። በዚያ ወቅት ከእስራኤላውያን ጠላቶች መካከል ጎልያድ የሚባል አንድ ግዙፍ ጦረኛ በተደጋጋሚ እየወጣ ሕዝቡንና አምላካቸውን ይገዳደር የነበረ ሲሆን መላው የእስራኤል ሠራዊት በፍርሃት ተውጦ ነበር። ይህ ግዙፍ ሰው እስራኤላውያንን በመገዳደር በውጊያ የሚገጥመው ሰው እንዲልኩለት መጠየቁን ዳዊት ሲሰማ በሁኔታው በመቆጣት ከእሱ ጋር ለመዋጋት ተስማማ። ይህ ወጣት፣ ቁመቱ ወደ ሦስት ሜትር የሚጠጋውን ባላንጣውን ለመግጠም የሄደው ወንጭፍና ጥቂት ድንጋዮች ብቻ ይዞ ነበር። ጎልያድ ይህንን ሲያይ አሾፈበት፤ ዳዊት ግን የሚዋጋው በይሖዋ አምላክ ስም በመሆኑ ከጎልያድ የተሻለ ትጥቅ እንዳለው ተናገረ! ዳዊት አንዲት ድንጋይ በመወንጨፍ ጎልያድን ከገደለው በኋላ የዚህን ግዙፍ ሰው ሰይፍ መዝዞ ራሱን ቆረጠው። የፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ይህንን ሲመለከት በድንጋጤ ሸሸ።
መጀመሪያ ላይ ሳኦል በዳዊት ድፍረት ስለተደነቀ ይህን ወጣት በሠራዊቱ ላይ ሾመው። ይሁን እንጂ ሳኦል፣ ዳዊት እንደተሳካለት ሲመለከት ከፍተኛ ቅናት አደረበት። በዚህም ምክንያት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ለዓመታት በስደት ለመኖር ተገደደ። ያም ሆኖ ዳዊት፣ ሳኦል በይሖዋ የተሾመ መሆኑን በማሰብ ሊገድለው ይፈልግ ለነበረው ለዚህ ንጉሥ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። በመጨረሻም ሳኦል በጦርነት ሞተ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ዳዊት፣ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ንጉሥ ሆነ።
“እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።” —2 ሳሙኤል 7:13
ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ለመሥራት እጅግ ጓጉቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚሠራለት ከዳዊት ዘሮች አንዱ እንደሚሆን ነገረው። ቤተ መቅደሱን የሠራው የዳዊት ልጅ ሰለሞን ነበር። ያም ቢሆን አምላክ ከዳዊት ጋር አስደናቂ ቃል ኪዳን በመግባት ወሮታውን ከፍሎታል፦ ከዳዊት ዘር ከሁሉ የሚበልጥ ሥርወ መንግሥት እንደሚገኝ ቃል ገብቶለታል። የኋላ ኋላም በኤደን ተስፋ የተሰጠበት ዘር ወይም አዳኝ በዳዊት የንግሥና መሥመር ይመጣል። ይህ አዳኝ በአምላክ የተሾመው መሲሕ ነው፤ መሲሕ የሚለው ቃል “የተቀባ” የሚል ትርጉም አለው። መሲሑ፣ ለዘላለም የሚኖር መንግሥት ወይም መስተዳድር ንጉሥ እንደሚሆን ይሖዋ ቃል ገብቷል።
ዳዊት፣ ይሖዋ ባደረገለት ነገር ልቡ በጥልቅ ስለተነካ እሱን ለማመስገን ሲል ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው የግንባታ ቁሳቁስና የከበሩ ማዕድናት አከማቸ። በተጨማሪም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ብዙ መዝሙራትን ጽፏል። ዳዊት “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ” በማለት በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ተናግሯል።—2 ሳሙኤል 23:2
—በ1 ሳሙኤል፤ በ2 ሳሙኤል እና በ1 ዜና መዋዕል መጻሕፍት እንዲሁም በኢሳይያስ 9:7፤ በማቴዎስ 21:9፤ በሉቃስ 1:32 እና በዮሐንስ 7:42 ላይ የተመሠረተ።