ምዕራፍ 115
በምድር ላይ የምትቋቋም አዲስ ገነት
እነዚህን ረጃጅም ዛፎች፣ የሚያማምሩ አበባዎችና ትላልቅ ተራራዎች ተመልከት። የሚታየው ነገር ሁሉ ደስ አይልም? አጋዘኗ ከትንሹ ልጅ እጅ ላይ ስትበላ ተመልከት። አንበሶቹንና በመስኩ ላይ ቆመው የሚታዩትን ፈረሶችም ተመልከት። በእንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ በሚገኝ ቤት ውስጥ መኖር አትፈልግም?
አምላክ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም እንድትኖር ይፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን እያሠቃዩ ያሉት የተለያዩ ሕመሞች እንዲደርሱብህ አይፈልግም። በአዲሲቷ ገነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- ‘አምላክ ከእነርሱ ጋር ይሆናል። ሞት ወይም ለቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም። የቀድሞዎቹ ነገሮች አልፈዋል።’
ኢየሱስ ይህ አስደናቂ ለውጥ እንዲከናወን ያደርጋል። ይህን የሚያደርገው መቼ እንደሆነ ታውቃለህ? አዎ፣ ክፋትን ሁሉና ክፉ ሰዎችን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ካጠፋ በኋላ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ ዓይነት በሽታ የነበረባቸውን ሰዎች እንዳዳነና አልፎ ተርፎም የሞቱ ሰዎችን እንዳስነሳ አስታውስ። ኢየሱስ ይህን ያደረገው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ በመላዋ ምድር ላይ ምን እንደሚያደርግ ለማሳየት ነው።
በምድር ላይ በምትቋቋመው አዲስ ገነት ውስጥ የሚኖረው ሁኔታ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! ኢየሱስ ከመረጣቸው የተወሰኑ ሰዎች ጋር በሰማይ ሆኖ ይገዛል። እነዚህ ገዥዎች በምድር ላይ ያሉት ሰዎች በሙሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያሟሉላቸዋል፤ እንዲሁም ደስተኞች እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። አምላክ በሚያቋቁማት አዲስ ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጠን ምን ማድረግ እንዳለብን እስቲ እንመልከት።