ምዕራፍ 93
ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መገበ
አንድ አሳዛኝ ነገር ተፈጸመ። አጥማቂው ዮሐንስ ተገደለ። የንጉሡ ሚስት የሆነችው ሄሮድያዳ ዮሐንስን አትወደውም ነበር። ንጉሡ የዮሐንስን ራስ እንዲያስቆርጠው አደረገች።
ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም አዘነ። ብቻውን ሆኖ ሰው ወደሌለበት አካባቢ ሄደ። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ተከተሉት። ኢየሱስ ሕዝቡን ሲያይ በጣም አዘነላቸው። ስለዚህ ስለ አምላክ መንግሥት ነገራቸው፤ እንዲሁም የታመሙትን ፈወሳቸው።
ቀኑ ሲመሽ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ መጥተው ‘አሁን መሽቷል፤ ይህ ደግሞ ሰው የማይኖርበት ቦታ ነው። በዚህ አካባቢ ወደሚገኙ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት’ አሉት።
ኢየሱስ ‘መሄድ የለባቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው’ አላቸው። ወደ ፊልጶስ ዞር አለና ‘ለእነዚህ ሰዎች በሙሉ የሚበቃ ምግብ ልንገዛ የምንችለው ከየት ነው?’ ሲል ጠየቀው።
ፊልጶስም ‘ለእያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ ምግብ ለማዳረስ እንኳ በጣም ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል’ ሲል መለሰለት። እንድሪያስ ‘ምግባችንን የያዘው ልጅ አምስት ዳቦና ሁለት ዓሣ ይዟል። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም’ አለው።
ኢየሱስ ‘ሕዝቡ ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ ንገሯቸው’ አላቸው። ከዚያም አምላክ ምግቡን ስለ ሰጣቸው አመስግኖ ቆራረሰው። ቀጥሎም ደቀ መዛሙርቱ ዳቦውንና ዓሣውን ለሕዝቡ ሁሉ አደሉ። 5, 000 ወንዶችና ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶችና ልጆች ነበሩ። ሁሉም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ። ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ሲሰበስቡ 12 መሶብ ሙሉ ሆነ!
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ የገሊላን ባሕር አቋርጠው እንዲሄዱ አደረገ። ሌሊት አንድ ኃይለኛ ነፋስ መጣ፤ ማዕበሉም ጀልባዋን አናወጣት። ደቀ መዛሙርቱ በጣም ፈሩ። ከዚያም እኩለ ሌሊት ላይ አንድ ሰው በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ ሲመጣ አዩ። የሚያዩት ነገር ምን እንደሆነ ስላላወቁ በፍርሃት መጮህ ጀመሩ።
ኢየሱስ ‘እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!’ አላቸው። በዚህም ጊዜ ሊያምኑ አልቻሉም። ስለዚህ ጴጥሮስ ‘እውነት አንተ ጌታ ኢየሱስ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ መምጣት እንድችል አድርገኝ’ አለው። ኢየሱስ ‘ና!’ አለው። ጴጥሮስም ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ ተራመደ! ከዚያም ፈራና መስጠም ጀመረ፤ ሆኖም ኢየሱስ አዳነው።
ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ እንደገና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መገበ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሰዎቹን የመገበው በሰባት ዳቦና በጥቂት ትናንሽ ዓሦች ነበር። ልክ እንደ በፊቱ ምግቡ ተትረፍርፎ ነበር። ኢየሱስ ለሰዎች የሚያደርገው እንክብካቤ አያስደስትም? የአምላክ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ ምንም የሚያስጨንቀን ነገር አይኖርም!