ምዕራፍ 51
ሩትና ናዖሚ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሩት የሚባል መጽሐፍ ታገኛለህ። መጽሐፉ እስራኤላውያን መሳፍንት በነበሯቸው ዘመን ይኖር የነበረ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው። ሩት ወጣት ሞዓባዊት ሴት ናት፤ የአምላክ ሕዝብ ከሆኑት ከእስራኤላውያን ወገን አልነበረችም። ይሁን እንጂ ሩት ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ ስትማር ይሖዋን በጣም ወደደችው። ናዖሚ ሩትን ስለ ይሖዋ እንድትማር የረዳቻት አረጋዊት ሴት ናት።
ናዖሚ እስራኤላዊ ሴት ናት። እሷና ባሏ እንዲሁም ሁለት ወንዶች ልጆቻቸው በእስራኤል ረሃብ በነበረበት ዘመን ወደ ሞዓብ ምድር ሄዱ። ከዚያም ከዕለታት አንድ ቀን የናዖሚ ባል ሞተ። በኋላ የናዖሚ ልጆች ሩትና ዖርፋ የተባሉ ሁለት ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። ከ10 ዓመታት በኋላ ግን ሁለቱ የናዖሚ ልጆች ሞቱ። ናዖሚና ሁለቱ ሴቶች ምንኛ አዝነው ይሆን! ከዚህ በኋላ ናዖሚ ምን ታደርግ ይሆን?
ከዕለታት አንድ ቀን ናዖሚ ረጅሙን ጉዞ ተጉዛ ወገኖቿ ወዳሉበት ወደ አገሯ ለመመለስ ወሰነች። ሩትና ዖርፋ ከእርሷ ጋር ለመኖር ፈለጉ፤ ስለዚህም አብረዋት ሄዱ። በመንገዱ ላይ ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ግን ናዖሚ ሴቶቹን ‘ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ’ አለቻቸው።
ናዖሚ ሴቶቹን ለመሰናበት ሳመቻቸው። በዚህ ጊዜ ናዖሚን በጣም ይወዷት ስለነበር ማልቀስ ጀመሩ። ‘አይሆንም! ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን’ አሏት። ሆኖም ናዖሚ ‘ልጆቼ ሆይ፣ ተመለሱ። እዚሁ ብትሆኑ ይሻላል’ አለቻቸው። ስለዚህ ዖርፋ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ሩት ግን አልተመለሰችም።
ናዖሚ ሩትን ‘ዖርፋ ተመልሳለች። አንቺም ከእርሷ ጋር ወደ ቤት ተመለሺ’ አለቻት። ሩት ግን ‘አንቺን ትቼ እንድመለስ ለማድረግ አትሞክሪ! ከአንቺ ጋር ልሂድ። ወደምትሄጂበት ሁሉ እሄዳለሁ፤ አንቺ በምትኖሪበት እኖራለሁ። ሕዝብሽ ሕዝቤ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል። በምትሞችበት ስፍራ እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ’ ስትል መለሰችላት። ናዖሚ ይህን ስትሰማ ሩት ወደ ቤቷ እንድትመለስ ለማግባባት የምታደርገውን ጥረት አቆመች።
በመጨረሻም ሁለቱ ሴቶች ወደ እስራኤል ምድር ደረሱ። በዚያም መኖር ጀመሩ። ወቅቱ ገብስ የሚሰበሰብበት ጊዜ ስለነበረ ሩት ወዲያውኑ በእርሻ ቦታዎች መሥራት ጀመረች። ቦዔዝ የተባለ አንድ ሰው በእርሱ እርሻ ላይ ገብስ እንድትሰበስብ ፈቀደላት። የቦዔዝ እናት ማን እንደሆነች ታውቃለህ? በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ረዓብ ናት።
አንድ ቀን ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት:- ‘ታሪክሽን በሙሉ ለናዖሚም ያደረግሽላትን መልካም ነገር ሰምቻለሁ። አባትሽንና እናትሽን አገርሽንም ትተሽ ከዚህ በፊት ከማታውቂው ሕዝብ ጋር ለመኖር እንዴት እንደመጣሽ አውቃለሁ። ይሖዋ ይባርክሽ!’
ሩት ‘ጌታዬ ሆይ፣ መልካም አድርገህልኛል። በመልካም አነጋገርህ አጽናንተኸኛል’ ስትል መለሰችለት። ቦዔዝ ሩትን በጣም ወደዳት፤ ብዙም ሳይቆይ ተጋቡ። ይህ ናዖሚን ምንኛ አስደስቷት ይሆን! ሆኖም ሩትና ቦዔዝ የመጀመሪያ ልጃቸውን ኢዮቤድን ሲወልዱ ናዖሚ ይበልጥ ተደስታለች። በኋላ ኢዮቤድ የዳዊት አያት ሆነ፤ ቆየት ብሎ ስለ ዳዊት ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሩት መጽሐፍ