ምዕራፍ 76
ኢየሩሳሌም ጠፋች
ንጉሥ ናቡከደነፆር በደንብ የተማሩትን እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው ከ10 ዓመታት በላይ አልፈው ነበር። አሁን ምን እየተከናወነ እንዳለ ተመልከት! ኢየሩሳሌም በእሳት እየተቃጠለች ነው። ያልተገደሉት እስራኤላውያን ደግሞ እስረኞች ሆነው ወደ ባቢሎን እየተወሰዱ ነው።
ይህ የይሖዋ ነቢያት ሕዝቡ ክፉ መንገዳቸውን ካልለወጡ ይመጣል ብለው ያስጠነቀቁት ነገር እንደሆነ አስታውስ። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ነቢያቱን አልሰሟቸውም። ይሖዋን ማምለክ ሲገባቸው የሐሰት አማልክትን ማምለካቸውን ቀጠሉ። ስለዚህ ሕዝቡ መቀጣት ይገባቸው ነበር። እንዲህ የምንለው የአምላክ ነቢይ የሆነው ሕዝቅኤል እስራኤላውያን ይፈጽሟቸው ስለነበሩት መጥፎ ነገሮች ስለ ገለጸልን ነው።
ሕዝቅኤል ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ሕዝቅኤል ይህ ታላቅ ጥፋት በኢየሩሳሌም ላይ ከመድረሱ ከ10 ዓመታት በፊት ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው ወጣቶች አንዱ ነው። ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ማለትም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ወደ ባቢሎን የተወሰዱት በዚህ ጊዜ ነበር።
ሕዝቅኤል በባቢሎን እያለ ይሖዋ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየተፈጸሙ የነበሩትን መጥፎ ነገሮች ያሳየው ነበር። ይሖዋ ይህን ያደረገው በተአምር ነበር። በዚያ ወቅት ሕዝቅኤል በባቢሎን የነበረ ቢሆንም ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይከናወን የነበረውን እያንዳንዱን ነገር ያሳየው ነበር። ሕዝቅኤል ያየው ነገር በጣም የሚያስደነግጥ ነበር!
ይሖዋ ሕዝቅኤልን እንዲህ አለው:- ‘ሕዝቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች ተመልከት። እባቦችና ሌሎች እንስሳት የተሳሉባቸውን ግድግዳዎች ተመልከት። በተጨማሪም እስራኤላውያን እነዚህን ሥዕሎች ሲያመልኩ ተመልከት!’ ሕዝቅኤል እነዚህን ነገሮች መመልከት ችሎ ነበር፤ እየተፈጸመ የነበረውንም ነገር ጽፎታል።
ይሖዋ ሕዝቅኤልን ‘የእስራኤላውያን አለቆች በድብቅ የሚያደርጉትን ነገር ታያለህ?’ አለው። አዎ፣ ሕዝቅኤል ይህንንም ማየት ችሎ ነበር። 70 ሰዎች ነበሩ፤ ሁሉም የሐሰት አማልክት እያመለኩ ነበር። ‘ይሖዋ አያየንም። እርሱ ምድሪቱን ትቷታል’ ይሉ ነበር።
ከዚያም ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ሰሜናዊ መግቢያ ላይ የነበሩ አንዳንድ ሴቶችን ለሕዝቅኤል አሳየው። በዚያ ተቀምጠው የሐሰት አምላክ የሆነውን ተሙዝን እያመለኩ ነበር። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ደጃፍ ላይ ያሉትን ሰዎች ደግሞ ተመልከት አለው! ወደ 25 የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ። ሕዝቅኤል አያቸው። ወደ ምሥራቅ ተደፍተው ፀሐይን እያመለኩ ነበር!
ይሖዋ ‘እነዚህ ሰዎች አቃልለውኛል። መጥፎ ነገሮችን ከመሥራትም አልፈው እነዚህን ነገሮች በቤተ መቅደሴ ውስጥ መፈጸም ጀምረዋል!’ አለ። ስለዚህ ይሖዋ ‘ቁጣዬን አወርድባቸዋለሁ። ጥፋት ሲደርስባቸውም አላዝንላቸውም’ ብሎ ማለ።
ይሖዋ ለሕዝቅኤል እነዚህን ነገሮች ካሳየው በኋላ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስራኤላውያን በናቡከደነፆር ላይ ዓመፁ። ስለዚህ ናቡከደነፆር ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት ሄደ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ባቢሎናውያን የኢየሩሳሌምን ግንብ ደርምሰው ገቡና ከተማይቱን አቃጥለው አመድ አደረጓት። አብዛኞቹ ሰዎች ተገድለዋል አለዚያም እስረኞች ሆነው ወደ ባቢሎን ተወስደዋል።
ይሖዋ ይህ አስከፊ ጥፋት በእስራኤላውያን ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋን ባለመስማታቸውና ሕጎቹን ባለመታዘዛቸው ነው። ይህ ሁኔታ ምንጊዜም አምላክ ያለውን ማድረጋችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል።
በመጀመሪያ ጥቂት ሰዎች በእስራኤል ምድር እንዲቀሩ ተፈቅዶላቸው ነበር። ንጉሥ ናቡከደነፆር በእነዚህ ሰዎች ላይ ጎዶልያስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ አለቃ አድርጎ ሾመ። በኋላ ግን ጥቂት እስራኤላውያን ጎዶልያስን ገደሉት። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ይህ መጥፎ ነገር ስለተፈጸመ ባቢሎናውያን መጥተው ሁላችንንም ያጠፉናል ብለው ፈሩ። ስለዚህ ኤርምያስ ከእነርሱ ጋር እንዲሄድ አስገደዱትና ወደ ግብጽ ሸሹ።
ከዚህ በኋላ የእስራኤል ምድር ሰው አልባ ሆነ። ለ70 ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የሚኖር አንድም ሰው አልነበረም። ሙሉ በሙሉ ባዶ ነበረች። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከ70 ዓመታት በኋላ ሕዝቡን ወደዚች ምድር እንደሚመልሳቸው ቃል ገብቷል። ወደ ባቢሎን ምድር የተወሰዱት የአምላክ ሕዝቦች በእነዚህ ዓመታት ምን ደርሶባቸው ይሆን? እስቲ እንመልከት።