ምዕራፍ 74
ያለ ፍርሃት ይናገር የነበረው ሰው
ሰዎቹ በዚህ ሰው ላይ ሲያሾፉበት ተመልከት። ይህ ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ኤርምያስ ነው። ኤርምያስ ታላቅ የአምላክ ነቢይ ነው።
ንጉሥ ኢዮስያስ ጣዖታቱን ከምድሪቱ ላይ ማጥፋት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ኤርምያስን የእሱ ነቢይ እንዲሆን አዘዘው። ኤርምያስ ግን ልጅ ስለሆንኩ ነቢይ ለመሆን አልችልም ብሎ አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደሚረዳው ነገረው።
ኤርምያስ እስራኤላውያን መጥፎ ነገር መሥራታቸውን እንዲያቆሙ ነገራቸው። ‘አሕዛብ የሚያመልኳቸው አማልክት የሐሰት አማልክት ናቸው’ አላቸው። ሆኖም ብዙዎቹ እስራኤላውያን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ከማምለክ ይልቅ ጣዖታትን ማምለክ መርጠው ነበር። ኤርምያስ በክፋት ድርጊታቸው የተነሳ አምላክ እንደሚቀጣቸው ሲነግራቸው ይስቁበት ነበር።
ብዙ ዓመታት አለፉ። ኢዮስያስ ሞተና ከሦስት ወራት በኋላ ልጁ ኢዮአቄም ነገሠ። ኤርምያስ ‘መጥፎ ነገር መሥራታችሁን ካላቆማችሁ ኢየሩሳሌም ትጠፋለች’ በማለት ሕዝቡን ማሳሰቡን ቀጠለ። ካህናቱ ኤርምያስን ያዙትና ‘እንዲህ ብለህ በመናገርህ መገደል አለብህ’ ብለው ጮኹ። ከዚያም ለእስራኤል መሳፍንት ‘ኤርምያስ ከተማችን ትጠፋለች ብሎ ስለተናገረ መሞት አለበት’ አሏቸው።
ኤርምያስ ምን ያደርግ ይሆን? ምንም አልፈራም! ሁሉንም እንዲህ አላቸው:- ‘እንዲህ ብዬ እንድናገር የላከኝ ይሖዋ ነው። መጥፎ ነገር መሥራታችሁን ካላቆማችሁ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ያጠፋታል። እኔን ብትገድሉኝ ግን ምንም ጥፋት ያልሠራን ሰው መግደላችሁ እንደሆነ እወቁ።’
መሳፍንቱ ኤርምያስን ተዉት፤ ሆኖም እስራኤላውያን መጥፎ መንገዳቸውን አላስተካከሉም። ከጊዜ በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መጣና ኢየሩሳሌምን ወረራት። በመጨረሻ ናቡከደነፆር እስራኤላውያንን አገልጋዮቹ አደረጋቸው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያንን ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። የማታውቃቸው ሰዎች ከአገርህ አውጥተው ወደማታውቀው አገር ቢወስዱህ የሚኖረውን ሁኔታ እስቲ አስበው!