ምዕራፍ 31
ሙሴና አሮን ፈርዖንን አነጋገሩት
ሙሴ ወደ ግብፅ ሲመለስ ለወንድሙ ለአሮን ስለተፈጸሙት ተአምራት ሁሉ ነገረው። ሙሴና አሮን እነዚህን ተአምራት ለእስራኤላውያን ሲያሳዩአቸው ሕዝቡ በሙሉ ይሖዋ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ አመኑ።
ከዚያም ሙሴና አሮን ፈርዖንን ለማነጋገር ሄዱ። ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ “ሕዝቤ ወደ ምድረ በዳ ሄደው ያመልኩኝ ዘንድ ሦስት ቀን ፍቀድላቸው” ብሏል’ ብለው ነገሩት። ይሁን እንጂ ፈርዖን ‘በይሖዋ አላምንም። እስራኤልንም አልለቅም’ ሲል መለሰ።
ሕዝቡ ከሥራ ነፃ ሆነው ይሖዋን ለማምለክ የሚችሉበት ጊዜ ለማግኘት ፈቃድ በመጠየቃቸው ፈርዖን ተቆጣ። በዚህም የተነሳ ከበፊቱ የበለጠ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው። እስራኤላውያን ይህ ችግር የደረሰብን በአንተ ምክንያት ነው ብለው በሙሴ ላይ አማረሩ፤ ሙሴም በጣም አዘነ። ይሖዋ ግን ምንም አትጨነቅ አለው። ‘ፈርዖን ሕዝቤን እንዲለቅ አደርገዋለሁ’ አለ።
ሙሴና አሮን ፈርዖንን እንደገና ለማነጋገር ሄዱ። በዚህ ጊዜ አንድ ተአምር ፈጸሙ። አሮን በትሩን ሲጥለው ትልቅ እባብ ሆነ። ይሁን እንጂ የፈርዖንም ጠቢባን በትሮቻቸውን ሲጥሉ በትሮቹ እባቦች ሆኑ። ግን ተመልከት! የአሮን እባብ የጠቢባኖቹን እባቦች እየበላቸው ነው። ያም ሆኖ ግን ፈርዖን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።
ይሖዋ ፈርዖንን አንድ ትምህርት ሊያስተምረው ነው። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? 10 መቅሠፍቶችን ወይም እጅግ አስከፊ የሆኑ ችግሮችን በግብፅ አገር ላይ በማምጣት ነው።
ብዙዎቹ መቅሰፍቶች ከደረሱ በኋላ ፈርዖን ወደ ሙሴ መልእክተኞችን ልኮ ‘መቅሰፍቱን አቁምልን፤ እስራኤልን እለቃለሁ’ አለው። ይሁን እንጂ መቅሰፍቱ ሲቆም ፈርዖን ሐሳቡን ለወጠ። ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም። ሆኖም በመጨረሻ ከአሥረኛው መቅሰፍት በኋላ ፈርዖን እስራኤላውያንን ለቀቃቸው።
አሥሩ መቅሰፍቶች እያንዳንዳቸው ምን እንደሆኑ ታውቃለህ? ገጹን ግለጥና እነዚህ መቅሰፍቶች ምን እንደሆኑ እንመልከት።