በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሌሎች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

“ላደርግልህ የምችለው ነገር ካለ ንገረኝ።” ብዙዎቻችን የሚወዱት ሰው የሞተባቸው ዘመዶቻችንን ወይም ወዳጆቻችንን እንዲህ እንላቸዋለን። በእርግጥ ይህን የምንላቸው ከልባችን ነው። እነሱን ለመርዳት የምንችለውን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። ይሁን እንጂ ሐዘንተኛው ሰው እኛን ጠርቶ “አንድ የምታደርግልኝ ነገር አለ” ይለናል? አብዛኛውን ጊዜ አይልም። ሐዘን የደረሰበትን ሰው ለመርዳትና ለማጽናናት የምንፈልግ ከሆነ በራሳችን ተነሳስተን አንድ ነገር ልናደርግለት እንደሚገባ ግልጽ ነው።

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው” ይላል። (ምሳሌ 15:23፤ 25:11) ምን እንደሚባልና ምን እንደማይባል፣ ምን እንደሚደረግና ምን እንደማይደረግ ማወቅ አስፈላጊ ነው። የሚወዱት ሰው የሞተባቸው አንዳንድ ሰዎች ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

ማድረግ የሚገቡን ነገሮች . . .

አዳምጡ፦ ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ . . . መሆን አለበት” ይላል። አንድን ሐዘንተኛ ልትረዱ ከምትችሉባቸው ጠቃሚ መንገዶች አንዱ፣ ሐዘንተኛው የሚናገረውን በማዳመጥ የሐዘኑ ተካፋይ መሆን ነው። የሚወዱት ሰው የሞተባቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ ግለሰቡ፣ ለሞቱ ምክንያት ስለሆነው አደጋ ወይም በሽታ አሊያም ከሞቱ በኋላ ስለሚሰማቸው ስሜት መናገር ይፈልጉ ይሆናል። ስለዚህ “ስለ ሁኔታው ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብላችሁ ጠይቁ። ራሳቸው እንዲወስኑ ፍቀዱላቸው። አንድ ወጣት አባቱ የሞተበትን ጊዜ አስታውሶ ሲናገር “ሰዎች ስለ አሟሟቱ ጠይቀውኝ የምናገረውን በጥሞና ሲያዳምጡ ቀለል ይለኝ ነበር” ብሏል። መልስ ወይም መፍትሔ የመስጠት ግዴታ እንዳለባችሁ ሳታስቡ በትዕግሥትና በአዘኔታ አዳምጧቸው። ሊያካፍሏችሁ የፈለጉትን ሁሉ እንዲናገሩ ፍቀዱላቸው።

አጽናኗቸው፦ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንዳደረጉ ንገሯቸው (ወይም እውነት የሆነና የሚያጽናና ሌላ ሐሳብ አካፍሏቸው)። የሐዘን፣ የቁጣ፣ የጥፋተኝነት ወይም ማንኛውም ዓይነት ሌላ ስሜት የሚሰማቸው ከሆነ እንዲህ የሚሰማቸው እነሱ ብቻ እንዳልሆኑ አረጋግጡላቸው። ተመሳሳይ ሁኔታ ደርሶባቸው ሐዘኑን ተቋቁመው ስለተጽናኑ ሌሎች ሰዎች ንገሯቸው። እንዲህ ያለው ‘ደስ የሚያሰኝ ቃል ለአጥንት ፈውስ እንደሆነ’ ምሳሌ 16:24 ይናገራል።—1 ተሰሎንቄ 5:11, 14

ከጎናቸው ሁኑ፦ ብዙ ወዳጆችና ዘመዶች አብረዋቸው በሚሆኑባቸው በሐዘኑ የመጀመሪያ ቀናት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ወደ ዕለታዊ ተግባራቸው ከተመለሱ በኋላም ለወራት ያህል ከጎናቸው እንደሆናችሁ አሳዩዋቸው። እንዲህ በማድረግ ‘በመከራ ቀን’ የማይለይ “እውነተኛ ወዳጅ” ትሆኗቸዋላችሁ። (ምሳሌ 17:17) ልጇን በመኪና አደጋ ያጣችው ቴሬሳ “ወዳጆቻችን፣ ቤታችን ውስጥ ብዙ ጊዜ ብቻችንን እንዳንሆን ሲሉ ምሽት ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲኖሩን ያደርጉ ነበር። ይህም ይሰማን የነበረውን የባዶነት ስሜት እንድንቋቋም ረድቶናል” ብላለች። የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳ በሠርጋቸው ቀን ወይም ግለሰቡ በሞተበት ቀንና እንደነዚህ ባሉት ሌሎች ጊዜያት ሐዘናቸው ሊቀሰቀስ ይችላል። እንደነዚህ ያሉትን ቀኖች አስታውሳችሁ ልትጠይቋቸውና ካስፈለገም ልታጽናኗቸው እንድትችሉ ለምን እነዚህን ቀኖች የቀን መቁጠሪያችሁ ላይ ምልክት አታደርጉባቸውም?

ልታደርጉላቸው የሚገባ ነገር እንዳለ ካስተዋላችሁ እስክትጠየቁ ድረስ አትጠብቁ፤ በራሳችሁ ተነሳስታችሁ አድርጉላቸው

በራሳችሁ ተነሳስታችሁ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አድርጉላቸው፦ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፈጸም የሚልኩት ሰው ይፈልጋሉ? ልጆቻቸውን የሚጠብቅላቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል? ሊጠይቋቸው የመጡ ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ማረፊያ ቦታ ያስፈልጋቸዋል? ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ግራ ስለሚጋቡ ሌሎች ሰዎችን እንዲህ አድርጉልኝ ማለት ይቅርና ራሳቸው እንኳ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው አያውቁም። ስለዚህ ልታደርጉላቸው የሚገባ ነገር እንዳለ ካስተዋላችሁ በራሳችሁ ተነሳስታችሁ አድርጉላቸው እንጂ እስክትጠየቁ ድረስ አትጠብቁ። (1 ቆሮንቶስ 10:24፤ ከ1 ዮሐንስ 3:17, 18 ጋር አወዳድሩ።) ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “‘እንድናደርግልሽ የምትፈልጊው ነገር ካለ ንገሪን’ ያሉኝ ብዙዎች ናቸው። አንዲት ወዳጄ ግን እንዲህ ብላ አልጠየቀችኝም። በቀጥታ ወደ መኝታ ቤት ገባችና ባሌ በሞተበት ጊዜ ቆሽሾ የነበረውን አንሶላ አውጥታ ማጠብ ጀመረች። ሌላዋ ደግሞ ባልዲ፣ ውኃና የማጽጃ ዕቃ ይዛ ባሌ አስታውኮበት የነበረውን ምንጣፍ መጥረግ ጀመረች። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከጉባኤ ሽማግሌዎች አንዱ የሥራ ልብሱን ለብሶና መሣሪያዎቹን ይዞ መጣና ‘መጠገን የሚያስፈልገው ነገር መኖሩ አይቀርም። ምን ልጠግንልሽ?’ አለኝ። ይህ ሰው፣ ከማጠፊያው ተላቅቆ የነበረውን በሬን ስለጠገነልኝና ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዘ ነገር ስለሠራልኝ በጣም ደስ አለኝ!”—ከያዕቆብ 1:27 ጋር አወዳድሩ።

ቤታችሁ አስተናግዷቸው፦ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዳ መቀበልን አትርሱ” ሲል ያሳስበናል። (ዕብራውያን 13:2) በተለይ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች እንግዳ ተቀባይ መሆን ይገባናል። “በተመቸህ ቀን ብቅ በል” ከማለት ይልቅ የተወሰነ ቀንና ጊዜ ቀጥራችሁ ጋብዟቸው። ግብዣችሁን አንቀበልም ቢሉም በቀላሉ ተስፋ አትቁረጡ። ሳትጫኗቸው ደጋግማችሁ መጠየቅ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ምናልባት ግብዣችሁን ያልተቀበሉት በሌሎች ፊት ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው እንዳያለቅሱ በመስጋት ሊሆን ይችላል። አለዚያም እንዲህ ባለው ጊዜ መጋበዝና ከሌሎች ጋር መደሰት አግባብ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችውን ሊዲያ የተባለች እንግዳ ተቀባይ ሴት አስታውሱ። ወደ ቤቷ እንዲገባ ተጋብዞ የነበረው ሉቃስ “እንድንገባም አስገደደችን” ሲል ጽፏል።—የሐዋርያት ሥራ 16:15

ታጋሾችና አስተዋዮች ሁኑ፦ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች መጀመሪያ ላይ በሚናገሩት ነገር አትገረሙ። ተናድደው ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል አስታውሱ። የተቆጡት በቀጥታ በእናንተ ላይ ከሆነም አጸፋውን እንዳትመልሱ አስተዋዮችና ታጋሾች መሆን ያስፈልጋችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” በማለት ይመክራል።—ቆላስይስ 3:12, 13

ደብዳቤ ጻፉላቸው፦ የሐዘን መግለጫ ወይም የማጽናኛ ሐሳብ የያዘ ደብዳቤ ወይም ካርድ የሚኖረው ጠቀሜታ ብዙ ጊዜ ይዘነጋል። ጥቅሙ ምንድን ነው? እናቷን በካንሰር ያጣችው ሲንዲ እንዲህ ብላለች፦ “አንዲት ጓደኛዬ ደስ የሚል ደብዳቤ ጻፈችልኝ። ደግሜ ደጋግሜ ላነበው ስለቻልኩ በእጅጉ ረድቶኛል።” ይህ ዓይነቱ ደብዳቤ ወይም የማጽናኛ ካርድ “አጭር” ቢሆንም ከልባችሁ የሚሰማችሁን ስሜት የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 13:22) ለሐዘንተኛው ከልብ እንደምታስቡና እናንተም ሟቹን የምታስታውሱበት ልዩ ምክንያት እንዳላችሁ ወይም ደግሞ ሟቹ በሕይወታችሁ ውስጥ ስላሳደረው በጎ ተጽዕኖ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል።

አብራችኋቸው ጸልዩ፦ ሐዘን ከደረሰበት ሰው ጋር ሆናችሁ ወይም ብቻችሁን ሆናችሁ ስለ እሱ የምታቀርቡት ጸሎት የሚኖረውን ኃይል አቅልላችሁ አትመልከቱ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው” ይላል። (ያዕቆብ 5:16) ለምሳሌ፣ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ስለ እነሱ የምናቀርበውን ጸሎት መስማታቸው እንደ ጥፋተኝነት ስሜት ያሉትን አፍራሽ ስሜቶች ለማሸነፍ ሊረዳቸው ይችላል።—ከያዕቆብ 5:13-15 ጋር አወዳድሩ።

ማድረግ የማይገቡን ነገሮች . . .

ወደ ሆስፒታሉ መሄዳችሁ ብቻ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ሊያጽናናው ይችላል

ምን እንደምትናገሩ ወይም ምን እንደምታደርጉ ባለማወቃችሁ ምክንያት አትራቋቸው፦ ‘አሁን ብቻቸውን መሆን እንደሚያስፈልጋቸው እርግጠኛ ነኝ’ እንል ይሆናል። ይህን የምንለው ግን የተሳሳተ ነገር እንዳንናገር ወይም እንዳናደርግ በመፍራት መሄድ ስላልፈለግን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ወዳጆች፣ ዘመዶች ወይም የእምነት ባልደረቦች ከሐዘንተኛው ሰው መሸሻቸው ግለሰቡ ይበልጥ ብቸኝነት እንዲሰማው ያደርገዋል፤ ይህም ሐዘኑን ያከብድበታል። ያልተወሳሰበ ንግግርና ቀላል የሚመስሉ ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ አስታውሱ። (ኤፌሶን 4:32) አብራችኋቸው መሆናችሁ ብቻ ሊያጽናናቸው ይችላል። (ከሐዋርያት ሥራ 28:15 ጋር አወዳድሩ።) ቴሬሳ ልጇ የሞተችበትን ቀን አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ የሆስፒታሉ የእንግዶች መቀመጫ በወንድሞችና በእህቶች ተሞላ። ሁሉም ሽማግሌዎችና ሚስቶቻቸው መጥተው ነበር። አንዳንዶቹ ሴቶች የፀጉራቸውን መጠቅለያ እንኳ አላወለቁም። ሌሎቹ ደግሞ የሥራ ልብሳቸውን እንደለበሱ ነበሩ። ሁሉም ይሠሩ የነበረውን ሥራ ጥለው መጥተዋል። ብዙዎቹ የሚናገሩት እንደጠፋቸው ነግረውናል፤ ምንም ባይሉንም ግን ቅር አላለንም፤ አስፈላጊው ነገር መምጣታቸው ብቻ ነበር።”

ማልቀሳቸውን እንዲያቆሙ አትጫኗቸው፦ ‘ተው፣ ማልቀሱ ይብቃህ’ ለማለት እንፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንባቸውን እንዲያፈስሱ ብንፈቅድላቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል። ካተሪን ባሏ የሞተበትን ጊዜ አስታውሳ ስትናገር “ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጹና አልቅሰው እንዲወጣላቸው መፍቀድ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል” ብላለች። እንዴት ሊሰማቸው እንደሚገባ ከመናገር መቆጠብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የእነሱን ሐዘን እንዳትቀሰቅሱ በመፍራት የራሳችሁን ስሜት መደበቅ እንደሚያስፈልጋችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” ይላል።—ሮም 12:15

የሟቹን ልብሶች ወይም የግል ዕቃዎች ራሳቸው ለመጣል ዝግጁ ከመሆናቸው በፊት እንዲያስወግዱ ምክር ለመስጠት አትቸኩሉ፦ ሟቹን እንዲያስታውሱ የሚያደርጓቸው ነገሮች ሐዘናቸውን ያራዝሙባቸዋል ብለን በማሰብ እነዚህን ነገሮች ቢያስወግዱ ጥሩ እንደሚሆን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ “ከዓይን የራቀ ከልብ ይርቃል” የሚለው አባባል እዚህ ላይ ላይሠራ ይችላል። ሐዘንተኛው ሐዘኑን ለመርሳት ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልገው ይሆናል። ያዕቆብ ወጣት ልጁን ዮሴፍን አውሬ እንደበላው ባሰበ ጊዜ ምን እንደተሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የዮሴፍን በደም የተነከረ ልብስ ከተመለከተ በኋላ “ለብዙ ቀናት ለልጁ አለቀሰ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ሞከሩ፤ እሱ ግን ፈጽሞ ሊጽናና አልቻለም።”—ዘፍጥረት 37:31-35

‘ሌላ ልጅ መውለድ ትችያለሽ’ አትበሉ፦ ልጇን በሞት ያጣች አንዲት እናት “ሌላ ልጅ ልወልድ እንደምችል የሚነግሩኝ ሰዎች ያናድዱኝ ነበር” ብላለች። ሰዎች ይህን የሚናገሩት ለማጽናናት ብለው ቢሆንም የሞተው ልጅ በሌላ ልጅ ሊተካ እንደሚችል መናገር በሐዘን ላይ የሚገኙትን ወላጆች ‘እንደ ሰይፍ ሊወጋቸው’ ይችላል። (ምሳሌ 12:18) አንድ ልጅ በሌላ ልጅ ፈጽሞ ሊተካ አይችልም። ለምን ቢባል እያንዳንዱ ልጅ የራሱ የሆነ ልዩ ባሕርይ ስላለው ነው።

ሟቹን በስም መጥቀስ ተገቢ እንዳልሆነ አይሰማችሁ፦ አንዲት እናት “ብዙ ሰዎች የልጄን የጂሚን ስም መጥራትም ሆነ ስለ እሱ መናገር አይፈልጉም ነበር” ትላለች። “ይህን ማድረጋቸው በተወሰነ መጠን ስሜቴን ጎድቶታል።” ስለዚህ የሟቹ ስም ሲነሳ የጨዋታውን ርዕስ ለማስለወጥ አትሞክሩ። ሐዘንተኛውን ስለ ሟቹ ማውራት ይፈልግ እንደሆነ ጠይቁት። (ከኢዮብ 1:18, 19 እና 10:1 ጋር አወዳድሩ።) የሚወዱት ሰው የሞተባቸው አንዳንድ ሰዎች፣ ወዳጆቻቸው ሟቹን አንስተው ተወዳጅ ስለሆኑ ልዩ ባሕርያቱ ሲናገሩ መስማት ያስደስታቸዋል።—ከሐዋርያት ሥራ 9:36-39 ጋር አወዳድሩ።

‘መሞቱ ይሻለዋል’ ብላችሁ ለመናገር አትቸኩሉ፦ ሞቱ ጥሩ የሚሆንበትን ምክንያት መናገር ሁልጊዜ ሰዎችን ‘ያጽናናል’ ማለት አይቻልም። (1 ተሰሎንቄ 5:14) አንዲት ሴት እናቷ የሞተችበትን ጊዜ አስታውሳ ስትናገር “‘ከሥቃይ ተገላግላለች’ ወይም ‘እሷስ አረፈች’ ይሉኛል። እኔ ግን እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን መስማት አልፈልግም ነበር” ብላለች። እንደነዚህ ያሉት አባባሎች፣ ቋሚዎቹ ማዘን እንደማይገባቸው ወይም በሞት ያጡት ሰው ያን ያህል ትልቅ ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ያደርጋል። እነዚህ ሰዎች በጣም የሚወዱትን ሰው በማጣታቸው ምክንያት ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።

‘እንዴት እንደሚሰማህ አውቃለሁ’ ባትሉ የተሻለ ሊሆን ይችላል፦ እውነት እንዴት እንደሚሰማቸው ታውቃላችሁ? ለምሳሌ ያህል፣ ልጅ ሞቶባችሁ የማያውቅ ከሆነ ልጁ የሞተበት አንድ ወላጅ እንዴት እንደሚሰማው ማወቅ ትችላላችሁ? እናንተም ልጃችሁን በሞት አጥታችሁ ቢሆን እንኳ የእናንተ ስሜት ከሌሎች ሊለይ እንደሚችል ተገንዘቡ። (ከሰቆቃወ ኤርምያስ 1:12 ጋር አወዳድሩ።) በሌላ በኩል ግን ተገቢ መስሎ ከታያችሁ፣ እናንተ ከደረሰባችሁ ሐዘን እንዴት ልትጽናኑ እንደቻላችሁ ብትናገሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ልጇ የተገደለችባት አንዲት ሴት፣ ልጇ የሞተችባት ሌላ እናት ከሐዘኗ እንዴት እንደተጽናናች በነገረቻት ጊዜ እሷም ልትጽናና ችላለች። “ልጇ የሞተችባት ይህች ሴት ታሪኳን ስትጀምር ‘እንዴት እንደሚሰማሽ አውቃለሁ’ አላለችም። ምን ደርሶባት እንደነበረና ምን እንዳደረገች ከነገረችኝ በኋላ ነገሩን እንዳስብበት ተወችኝ” ስትል ተናግራለች።

ሐዘን የደረሰበትን ሰው ለመርዳት ርኅራኄ፣ አስተዋይነትና ፍቅር ያስፈልጋል። ሐዘንተኛው ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እርዳታችሁን እስኪጠይቅ አትጠብቁ። “የማደርግልህ ነገር ካለ . . .” አትበሉ። ልታደርጉለት የሚያስፈልገውን “ነገር” ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ ከዚያም በራሳችሁ ተነሳስታችሁ አድርጉለት።

አሁንም መልስ የሚያሻቸው ጥያቄዎች አሉ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚሰጠውን ተስፋ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ተስፋ ለእናንተም ሆነ ለሞተባችሁ ሰው ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? ይህ ተስፋ አስተማማኝ መሆኑን እንዴት ልናውቅ እንችላለን?