በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ ተጠርጋ ትጠፋለች

ዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ ተጠርጋ ትጠፋለች

ምዕራፍ 15

ዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ ተጠርጋ ትጠፋለች

1, 2. የጦር መሣሪያ የታጠቁትን ኃያላን ብሔራት ፈጣሪ እንዴት ይመለከታቸዋል? በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት የይሖዋ ውሳኔ ምንድን ነው?

ዛሬ ዓለም ከምን ጊዜውም የበለጠ በጦር መሣሪያ በኃይል ታጥቋል። ብሔራት ያሏቸው የኑክሌር መሣሪያዎች ለሰው ልጅ ሕልውና አስጊ ሆነዋል። ታዲያ የሰብዓዊው ቤተሰብ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሁኔታውን እንዴት ይመለከተዋል? ይህ ነገር በኢሳይያስ ምዕራፍ 34 ትንቢት ውስጥ ተገልጿል፤ እርሱም በሚከተሉት ቃላት ይከፈታል:-

2 “እናንተ አሕዛብ (ብሔራት) ሆይ፣ ቅረቡ፣ ስሙ፣ እናንተ ወገኖች ሆይ አድምጡ፣ ምድርና መላዋ፣ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ። [የይሖዋ (አዓት)] ቁጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፣ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፣ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፣ ተራሮችም ከደማቸው የተነሳ ይርሳሉ፣ [ይቀልጣሉ]። የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፣ ሰማያትም (ውጤት አልባ የሆኑት ሰብዓዊ መንግሥታት) እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፣ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋሉ።” (ኢሳይያስ 34:1–4) በእርግጥ መዓት እንደሚመጣ የሚናገር ትንቢት ነው።

3. (ሀ) ብሔራት እንዲያዳምጡ የተጠሩት ምንን ነበር? ይሖዋስ እንደዚያ ብሎ በትክክል ሊያዛቸው ይችል የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ብሔራት እንዳላዳመጡ የሚያሳየው ምንድን ነው?

3 የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ዛሬ ካሉት ብሔራት ጋር ክርክር አለው። ከ1919 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወጅ ያደረገውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልዕክት እንዲያዳምጡ የተጠሩት ለዚህ ነው። በምሥክሮቹ አማካኝነት እርሱ የሚናገረውን ነገር ማዳመጥ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ የዓለም ሁኔታዎች አዝማሚያ እንደሚያረጋግጠው ይህንን አላደረጉም፤ “የሰላም መስፍን” በሆነውና ንጉሥ ሆኖ በተሾመው ልጁ የሚመራውን ሰማያዊ መንግሥት ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታትን የመረጡት ብሔራት ምሥክሮቹን በቁም ነገር አልተመለከቷቸውም።

ኢሳይያስ በኤዶም ላይ የተናገረው ትንቢት

4, 5. (ሀ) ኤዶማውያን እነማን ነበሩ? መንትያ ወንድማቸው ለሆነው ለእስራኤል ሕዝብ ምን ዓይነት አቋም ይዘው ነበር? (ለ) ስለዚህ ይሖዋ ኤዶምን በሚመለከት ምን ውሳኔ አስተላለፈ?

4 በተለይ በዛሬዎቹ ብሔራዊ ወገኖች መካከል አንዲት በኃላፊነት የምትጠየቅ ኃይል አለች። ያችም ኃይል በዚህ ትንቢት ውስጥ ስሙ በግልጽ በተጠቀሰው የኤዶም ሕዝብ ተመስላለች። ኤዶማውያን የብኩርና መብቱን ለመንትያ ወንድሙ ለያዕቆብ ‘በእንጀራና በምሥር ወጥ’ የሸጠው የኤሳው ዝርያዎች ናቸው። ኤሳው “ኤዶም” ተብሎ መጠራት የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው፣ ትርጉሙም “ቀይ” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 25:24–34) ያዕቆብ የብኩርና መብቱን ቦታ ስለያዘበት ዔሳው ለመንትያ ወንድሙ ጥላቻ አደረበት። ምንም እንኳ የመንትያ ወንድማማች ሕዝቦች ቢሆኑም ኤዶም ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ወይም ለያዕቆብ ክፉ ጠላት ሆኖ ነበር። ለዚህ በአምላክ ሕዝብ ላይ ለነበረው ጥላቻ ኤዶም ተገቢ የሆነውን የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቁጣ በራሱ ላይ አምጥቶ ነበር፤ እርሱም ኤዶም ለዘላለም እንዲደመሰስ ወሰነበት። ይህ መለኮታዊ ውሳኔ በሚከተሉት የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት ውስጥ ተገልጿል:-

5 “ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፣ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። [ይሖዋ (አዓት)] መሥዋዕት በባሶራ፣ [በታወቀችው የኤዶም ከተማ] ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና [የይሖዋ (አዓት)] ሰይፍ በደም ተሞልታለች፣ በስብም፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፣ በአውራ በግ ኩላሊት ስብ ወፍራለች።”— ኢሳይያስ 34:5, 6

6. (ሀ) ይሖዋ ‘ሰይፉን’ በኤዶም ላይ “በሰማይ” እንደሰነዘረ ሊናገር የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሁዳ መንግሥት በባቢሎን ጥቃት ሲደርስበት ኤዶም በይሖዋ ሕዝብ ላይ ምን ወንድማዊ ያልሆነ ዝንባሌ አሳየ?

6 የነፍስ መግደል አስተሳሰብ ያለው የኤዶም ሕዝብ ምድር በይሖዋ “ሰይፍ” አማካኝነት በራሳቸው ደም መጥገብ ይኖርበታል። የኤዶም ግዛት ከፍ ያለ ተራራማ ምድር ነበር። (ኤርምያስ 49:16) ስለዚህ ይሖዋ በዚያች አገር ውስጥ ሰዎች እንዲታረዱ በማድረግ በሥዕላዊ አገላለጽ የፍርድ ሰይፉን “በሰማይ” እንደሚጠቀምበት ሊናገር ችሏል። ኤዶም ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ነበራት፤ የጦር ኃይሎችዋም አገሪቱን ከወራሪዎች ለመከላከል እስከ ሰማይ በሚደርሱት ሸንተረሮች ውስጥ ይዘዋወሩ ነበር። በዚህም ምክንያት የኤዶም ጦር ሠራዊት “የሰማይ ሠራዊት” ተብሎ ሊጠራ ችሏል። ይሁን እንጂ ኃያሉ ኤዶም የመንትያ ወንድሙ የእስራኤል ሕዝብ በባቢሎን ሠራዊት በተጠቃበት ጊዜ ምንም እርዳታ አልሰጠም። እንዲያውም ኤዶም የይሁዳ መንግሥት መገልበጡን በማየቱ ተደስቶና አጥፊዎቹንም አበረታቶ ነበር። (መዝሙር 137:7) የኤዶም ተንኮል ሕይወታቸውን ለማዳን የሚሮጡትን ግለሰቦች አሳድዶ እስከ መያዝና ለጠላት አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሶ ነበር። (አብድዩ 10–14) ኤዶማውያን በይሖዋ ላይ በትዕቢት እየተናገሩ ባዶዋን የቀረችውን የእስራኤላውያንን አገር ለመያዝ ዕቅድ አድርገው ነበር።— ሕዝቅኤል 35:10–15

7. የእስራኤል አምላክ የኤዶምን ሕዝብ የተንኮል አድራጎት የተመለከተው እንዴት ነው?

7 የጥንትዋ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ኤዶማውያን ለተመረጡት ሕዝቦቹ ያሳዩትን ወንድማዊ ያልሆነ ባሕርይ እንዲሁ አለፈውን? አላለፈውም። የአምላክ ልብ ጽዮን ተብላ በምትጠራ ምድራዊ ድርጅቱ ላይ በተንኮል ለተደረገው ነገር ‘የበቀል ቀን’ እና “የብድራት ዓመት” ለማምጣት ዓላማ ያደረገው ለዚህ ነው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “[የይሖዋ (አዓት)] የበቀሉ ቀን ስለ ጽዮንም (በአጽናፈ ዓለሙ ፍርድ ቤት የሚታይ) ክርክር የብድራት ዓመት ነው።”— ኢሳይያስ 34:8፤ ሕዝቅኤል 25:12–14

8. (ሀ) በኤዶም ላይ ቅጣትን ለማምጣት ይሖዋ የተጠቀመው በማን ነበር? (ለ) ነቢዩ አብድዩ ስለ ኤዶም ምን በሎ ተነበየ?

8 ከኢየሩሳሌም ጥፋት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር አማካኝነት በኤዶማውያን ላይ የጽድቅ በቀሉን መግለጽ ጀመረ። (ኤርምያስ 25:8, 15, 17, 21) የባቢሎን ሠራዊት በኤዶም ላይ በተንቀሳቀሰ ጊዜ ኤዶማውያንን ምንም ሊያድናቸው የሚችል አልነበረም! የባቢሎን ሠራዊት ኤዶማውያንን ከፍተኛ ከሆነው ድንጋያማ መኖሪያቸው አንከባለሏቸው። ይህ በኤዶም ላይ “የብድራት ዓመት” ነበር። ይሖዋ በሌላው ነቢይ በኩል በትንቢት እንዳስነገረው ሆኗል። “በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፣ ለዘላለምም ትጠፋለህ። . . . አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፣ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል።”— አብድዩ 10, 15

9. የኤዶም ዘመናዊ አምሳያ ማን ናት? ለምንስ?

9 በተጨማሪም ይህ ይሖዋ ለዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃል። ይህች ማን ናት? በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የይሖዋን አገልጋዮች በመሳደብና በማሳደድ የመሪነቱን ቦታ የያዘችው ማን ናት? በትዕቢተኞቹ የቄሶች ቡድን አማካኝነት ከዳተኛዋ ሕዝበ ክርስትና አይደለችምን? አዎን ነች! የሐሰት ክርስትና ግዛት የሆነችው ሕዝበ ክርስትና በዚህ ዓለም ጉዳዮች ረገድ ወደ ላይ በመንጠራራት ራስዋን ከፍ ከፍ አድርጋለች። እርስዋም በሰው ዘር የነገሮች ሥርዓት ድርጅት ከፍተኛዋ ክፍል ናት፣ ሃይማኖቶቿም የታላቂቱ ባቢሎን ጉልህ ክፍል ናቸው። ነገር ግን ይሖዋ በሕዝቦቹ፣ በምስክሮቹ ላይ ባሳየችው አሳፋሪ ጠባይ ምክንያት በዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ ላይ “የብድራት ዓመት” አውጆአል።

የኤዶም ዓይነት ዕጣ

10. ኢሳይያስ 34:9, 10 የኤዶምን ዕጣ የሚገልጸው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ ትንቢቱ ዛሬ የሚሠራው በማን ላይ ነው?

10 የዚህን የኢሳይያስን ትንቢት ተጨማሪ ክፍል በምንመረምርበት ጊዜ የዛሬዋን ሕዝበ ክርስትና በአእምሮአችን ለመያዝ እንችላለን:- “የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፣ አፈርዋም ዲን ይሆናል፣ መሬትዋም የሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች። በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፣ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል።” (ኢሳይያስ 34:9, 10) ስለዚህ የውሃ መውረጃ ሸለቆዎቿ ዝፍት (ሬንጅ) እንደሚወርድባቸው ያህል ስለሚሆኑ የኤዶም ምድር ደርቆ እንደተሰነጣጠቀ፣ አፈርዋም ዲን እንደሆነና ሊቀጣጠሉ የሚችሉት እነዚህ ንጥረ ነገሮች በእሳት እንደተያያዙ ሆኖ ተገልጿል።— ከራእይ 17:16 ጋር አወዳድር።

11, 12. በኢሳይያስ 34:10–15 ላይ በተሰጠው ትንቢታዊ መግለጫ መሠረት የኤዶም ምድር ምን ይሆናል? እንደዚህ ያለው የምድሪቱ ሁኔታስ እስከ ምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል?

11 የኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፣ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሷታል፤ ጉጉትና ቁራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድ የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል። መሳፍንቶቿን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፣ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ። በአዳራሽዋም እሾህ በቅጥሮቿም ሳማና አሜኬላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጎን ስፍራ ትሆናለች። የምድረበዳም አራዊት ከተኩሎች ጋር ይገናኛሉ፣ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች። በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቁላልም ትጥላለች”— ኢሳይያስ 34:10–15

12 በሰዎች በኩል ኤዶም “የባዶነት” ምድር ትሆናለች። የምድረበዳም አራዊት፣ ወፎችና እባቦች ብቻ የሚኖሩባት ጠፍ መሬት ትሆናለች። ይህ የምድሪቱ ደርቆ የመሰነጣጠቅ ሁኔታ ቁጥር 10 ላይ እንደተገለጸው “ለዘላለም ዓለም” መቀጠል ነበረበት። ለቀድሞ ነዋሪዎችዋ ምንም እንደገና የመመለስ ተስፋ አልነበራቸውም።— አብድዩ 18

13. “በይሖዋ መጽሐፍ” ውስጥ ስለ ሕዝበ ክርስትና ምን ተተንብዮአል? ይህስ መጽሐፍ ምንድን ነው?

13 ይህ በዘመናዊቷ የኤዶም አምሳያ በሕዝበ ክርስትና ላይ ለሚመጣው ከባድ መከራ እንዴት ያለ ጥላ ነው! እርስዋ ምስክሮቹን በጭካኔ የምታሳድደው የይሖዋ አምላክ ክፉ ጠላት እንደሆነች አሳይታለች። ስለዚህ ከአርማጌዶን በፊት የሚፈጸመው እየቀረበ ያለው ጥፋትዋ “[በይሖዋ (አዓት)] መጽሐፍ” ተተንብዮአል። (ኢሳይያስ 34:16) ይህ “የይሖዋ መጽሐፍ” ልዩ በሆነ መንገድ ጠላቶቹ ከሆኑትና ሕዝቡን ከሚጨቁኑት ጋር ሒሳብ በዝርዝር የሚተሳሰብበት መጽሐፍ ነው። ‘በይሖዋ መጽሐፍ’ ውስጥ ስለ ጥንትዋ ኤዶም የተነገረው ሁሉ እውነት ሆኗል፤ ይህም በዘመናዊቷ ኤዶም በሕዝበ ክርስትና ላይ ትንቢቱ በተመሳሳይ እውነት እንደሚሆን ዋስትና ይሰጣል።

14. የዛሬዎቹ የኤዶማውያን አምሳያዎች ያልተቀበሉት ነገር ምንድን ነው? የትኛውንስ የይሖዋን ሕዝቦች ምሳሌ ሳይከተሉ ቀርተዋል?

14 የዛሬዎቹ የኤዶም አምሳያዎች በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ውስጥ ይሖዋ አምላክን እንደ ንጉሥ አድርገው አልተቀበሉትም። ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና ዋናኛዋ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ስለሆነች መቅሰፍቶችዋን እንድትቀበል ተፈርዶባታል። ከታላቂቱ ባቢሎን “ውጡ” የሚለውን የይሖዋን ትእዛዝ አልፈጸመችም። (ራእይ 18:4) የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎችን ወይም “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉትን “ሌሎች በጎች” ምሳሌ አልቀዳችም።

15, 16. በራእይ 17 እና 18 እንዲሁም በኢሳይያስ 34 ላይ እንደ ተተነበየው የሕዝበ ክርስትና የወደፊት ሁኔታ ምንድን ነው?

15 የሕዝበ ክርስትና የወደፊት ሁኔታ በእርግጥም የጨለመ ነው። ፖለቲካዊ ወዳጆቿን ለማባበልና እርስዋን ፈጽሞ ለማጥፋት የጥቃት ርምጃ ለመውሰድ በአንድነት እንዳይሰበሰቡ ለማድረግ የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነች፣ ይሁን እንጂ በከንቱ ነው!

16 በራእይ ምዕራፍ 17 እና 18 መሠረት ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ይኸውም በሁሉም አካሎቿና በሕዝበ ክርስትናም ላይ ጭምር አውሬያዊ እርምጃ ለመውሰድ ፖለቲካዊውንና ወታደራዊ ኃይላቸውን እንዲሰጡ በልባቸው ያደርጋል። ይህም ከመላዋ ምድር የሐሰት ክርስትናን ያስወግዳል። የሕዝበ ክርስትና ሁኔታ በኢሳይያስ 34 ላይ ከተለገጸው የጨለመ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ይሆናል። ታላቂቱ ባቢሎንን በሚያጠፉት ብሔራት ላይ የሚመጣውን ወሳኙን ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን የሚሆነውን ጦርነት’ ለማየት በሕይወት አትቆይም። የኤዶም አምሳያ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ከምድር ገጽ ላይ “ለዓለምና ለዘላለም” ሙሉ በሙሉ ትጠፋለች።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 122 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአንድ ጊዜ መብል ብሎ የብኵርና መብቱን የሸጠው የኤሳው ዘሮች በሆኑት በኤዶማውያን ላይ የደረሰው ዓይነት ፍርድ በሕዝበ ክርስትናም ላይ ይደርሳል