በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ድርጅት በታማኝነት ማስታወስ

የይሖዋን ድርጅት በታማኝነት ማስታወስ

ምዕራፍ 17

የይሖዋን ድርጅት በታማኝነት ማስታወስ

1. ለማን ታማኝ ስለመሆን ማሰብ ይኖርብናል? ስለዚህ ጉዳይ ንጉሥ ዳዊት ምን ብሏል?

በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ለአገሩ ሊኖረው ስለሚገባው ታማኝነት ብዙ ተነግሯል። ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ገዥዎችና ሕዝቦች የሚኖሩበት አገር የሚገኝባትን ምድር ለፈጠረው አምላክ ታማኝ ስለመሆን ምን ያህል ይናገራሉ? በጥንት ዘመን የእስራኤሉ ንጉሥ ዳዊት የፈጣሪው አምላክ የይሖዋ ታማኝ አምላኪ ነበር። ዳዊት ለታማኝ አምላኩ “ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ” ብሎታል። [2 ሳሙኤል 22:26 (አዓት)፤ መዝሙር 18:25] እነዚህ ቃላት አንተ ለአምላክ ያለህን ዝንባሌ ይገልጻሉን?

2. ይሖዋ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ታማኝ ሆኖ እንደቀጠለ እንዴት እናውቃለን?

2 ዛሬ የሰው ዘር ያለው አጠቃላይ ዝንባሌ ለአምላክ ታማኝ ስለ መሆን የሚጨነቅ መሆኑን አያሳይም። ይህም ሆኖ ግን ይሖዋ ለሰብአዊው ቤተሰብ ታማኝ ነው። አምላክ የሰውን ልጅ አልጣለውም። ታማኝ ልጁ እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) አምላክ የሰውን ዘር ዓለም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለአምላክ የነበራቸውን ታማኝነት እንዲያፈርሱ ላታለላቸው ለታላቁ ጠላት ለሰይጣን አሳልፎ አልሰጠውም። እንዲሁም አምላክ በ2370 ከዘአበ የቀረውን የሰው ዘር በሙሉ ጠራርጐ ካጠፋው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ኖኅንና ቤተሰቡን በማዳን ታማኝነቱን አሳይቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5) በዚህ መንገድ ፈጣሪ ሰብአዊው ቤተሰብ እንደ አዲስ እንዲጀምር አድርጓል።

3. (ሀ) ዛሬ ስላለው አመጽ ምን ሊባል ይቻላል? አምላክስ ስለዚህ ነገር ምን ለማድረግ ዓላማ አለው? (ለ) ለይሖዋ ታማኝ በመሆን የሚገኘው ሽልማት ምንድን ነው?

3 ዛሬ በመላው ምድር ላይ ያለው ዓመፅ ከ4, 000 ዓመታት በፊት በኖኅ ዘመን ከነበረው የበለጠ ተባብሷል። (ዘፍጥረት 6:11) ስለዚህ ያው አምላክ አሁን ያለውን ዓለማዊ የነገሮች ሥርዓት ጠራርጐ ከሕልውና ውጭ ለማድረግ በቂ ምክንያት አለው። ዓላማውም ይህንን ለማድረግ ነው፤ ይሁን እንጂ ይህንን ሲያደርግ በምድር ላይ ያሉትን ታማኞቹን አያጠፋቸውም። “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፣ ታማኞቹንም አይተዋቸውም” ከሚለው ከመዝሙር 37:28 (አዓት) ጋር የሚስማማ ነገር ያደርጋል። በኖኅ ዘመን እንዳደረገውም ‘በአዲስ ሰማያትና በአዲስ ምድር’ ለተገነባው አዲስ የነገሮች ሥርዓት የጽድቅ አጀማመር ያደርግለታል። (2 ጴጥሮስ 3:13) የታማኝነት ሽልማቱ ታላቅ ነው። ሕይወትን የሚያሰጥ ነው!

4. የእስራኤል ሕዝብ በጊዜው የይሖዋ የሚታይ ድርጅት እንደነበረ እንዴት እናውቃለን?

4 በንጉሥ ዳዊት የግዛት ዘመን የእስራኤል ሕዝብ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ነበር። ዳዊት ለመላው ሕዝብ ምሳሌ ሆኖ ነበር። ያ ሕዝብ የይሖዋ የሚታይ ድርጅት ነበር። በተለይ የእርሱ የሆኑ የተደራጁ ሕዝቦቹ ነበሩ። በአሞጽ 3:1, 2 ላይ የተገለጸው የአምላክ ማሳሰቢያ የሚገልጸው ይህንን እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም:- “የእስራኤል ልጆች ሆይ፣ [ይሖዋ (አዓት)] በእናንተ፣ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ እንዲህም ብሏል:- እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ።”— ከ1 ነገሥት 8:41–43 ጋር አወዳድር

5. (ሀ) በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስህተቶችን ለማስገባት ሙከራዎች ተደርገው ነበርን? (ለ) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ምን ነገር ይመጣል ተብሎ ተተንብዮ ነበር?

5 ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እውነታ ጋር በመስማማት ይኸው አምላክ ይሖዋ ዛሬም በምድር ላይ አንድ የተደራጀ ሕዝብ፣ አንድ የሚታይ ድርጅት አለው። ይህ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ ድርጅት ነው። ይሁን እንጂ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ማለትም የክርስቲያን ጉባኤን ንጹሕ አቋም ለማስጠበቅ የማይበገሩ ተከላካይ የነበሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ወደ አምላክ ድርጅት ውስጥ ስሕተቶችን ለማስገባት ሙከራዎች ተደርገው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16–18) ከሐዋርያው ዮሐንስ ሞት በኋላ (ከ98 እዘአ ብዙም ሳይቆይ) በትንቢት የተነገረለት ክህደት ብቅ ማለት ጀመረ።— ሥራ 20:30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 3፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1

6. (ሀ) ክህደት ለምን ያህል ጊዜ ገንኖ ቆይቷል? ከምንስ ውጤት ጋር? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ወደ ምን የምርኮ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

6 ይህ ክህደት ከ17 መቶ ዘመናት ለሚበልጡ ጊዜያት እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ ገንኖ ቆይቷል። በዚያን ጊዜ ሕዝበ ክርስትና በመቶ በሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተከፋፈለች። የእውነተኛዎቹን የአምላክ ሕዝቦች ማንነት ለመለየት አስቸግሮ ነበር። ሕዝበ ክርስትና በቅዱሳን ጽሑፎች ሃይማኖታዊ ቋንቋ ላይ በጥብቅ ያልተመሠረቱ ሐሰት የተቀላቀለባቸውን ሃይማኖታዊ ቋንቋዎች ለሚናገሩት ለትልልቆቹም ሆኑ ለትንንሾቹ የሃይማኖት ድርጅቶች ባቤል ነበረች። እንደነዚህ ያሉት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ኢየሩሳሌምን ካጠፋው የባቢሎን ግዛት በጣም በሚበልጥ በአንድ ግዛት ምርኮኞች ሆነው ተወስደዋል። ይሁን እንጂ የጥንቷ ባቢሎን ምን ትመስል ነበር? ምርኮኞች ሆነው የተያዙት አይሁዶች ዝንባሌስ ምን ነበር?

በባቢሎን የነበሩት ምርኮኞች በታማኝነት ጽዮንን አስበዋት ነበር

7. (ሀ) በሃይማኖታዊ አባባል የጥንቷ ባቢሎን ምድር ምን ይመስል ነበር? (ለ) ይህስ በአይሁዳውያን ምርኮኞች ላይ ምን ውጤት አስከትሎ መሆን ይኖርበታል?

7 የጥንቷ ባቢሎን ጣዖቶች የሞሉባት የሐሰት አማልክት ምድር ነበረች። (ዳንኤል 5:4) ያለ ምንም ዓይነት ምስል አንዱን እውነተኛ አምላክ ብቻ ያመልኩ የነበሩትን ታማኝ አይሁዶች ልብ ይህ የብዙ የሐሰት አማልክት አምልኮ እንዴት ነክቶ እንደሚሆን ልንገምተው እንችላለን። በኢየሩሳሌም ውስጥ ይገኝ የነበረውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ ውበት በመመልከት ፋንታ በመላው የባቢሎን ምድር ውስጥ ይመለከቱ የነበረው የእነዚህን የሐሰት አማልክት ቤተመቅደሶችና ጣዖቶቻቸውን ነበር። * የዚህ የአንዱ ብቻውን እውነተኛ የሆነው አምላክ አምላኪዎች በዚህ ሁሉ ነገር እንዴት ያለ የጥላቻ ስሜት ተሰምቷቸው ይሆን!

8. (ሀ) አይሁዶች ተማርከው የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነበር? ታማኝ የሆኑት አይሁዶች ምን ጉጉት ነበራቸው? (ለ) መዝሙር 137:1–4 የታማኝ አይሁዳውያን ምርኮኞችን ኀዘን የሚገልጸው እንዴት ነው?

8 በኤርምያስ ትንቢት መሠረት እንደገና የሚመለሱበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ለ70 ዓመታት ይህንን ችለው መኖር ነበረባቸው። (2 ዜና 36:18–21፤ ኤርምያስ 25:11, 12) ይሖዋን የሚወዱትንና እርሱ በመረጣት ከተማ ውስጥ በተሠራለት ቤተመቅደስ ሊያመልኩት የሚፈልጉት የአይሁድ ምርኮኞች አሳዛኝ ሁኔታ በመዝሙር 137:1–4 ላይ ተገልጾልናል:- “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፣ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆአችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፣ የወሰዱንም [በማሾፍ፣ ለደስታ]:- የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። [የይሖዋን (አዓት)] ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?”

9. ባቢሎናውያን “የይሖዋን ዝማሬ” መዘመር የሚመለከቱት እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ በ70ዎቹ ዓመታት ፍጻሜ ላይ ምን ነገር ሊደርስ ነበር?

9 “የይሖዋ ዝማሬ” በቅዱስ መቅደሱ የሚያመልኩት የነፃ ሕዝቦቹ መዝሙር መሆን ይኖርበታል። እነዚህ አይሁዶች በተማረኩበት ምድር ለእነዚያ ባቢሎናውያን “የይሖዋን ዝማሬ” ቢዘምሩ ኖሮ ለማራኪዎቻቸው ከባቢሎን አማልክት እንደሚያንስ እንደ አንድ ተራ አምላክ ስም በማድረግ በይሖዋ ስም ላይ ለማፌዝ አጋጣሚ ይሆን ነበር። አስቀድሞውንም ቢሆን ሕዝቡን በአምላክ ከተሰጣቸው የትውልድ አገራቸው ብዙ አማልክት ወዳሉበት ምድር እንዲሄዱ በመፍቀዱ ቅዱስ ስሙ ከባድ ስድብ ደርሶበት ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ባቢሎናውያን በእርሱ ላይ የፌዝ ሳቅ የሚስቁበትና የስሙን ሕዝብ የሚያንቋሽሹበት ጊዜ ለተወሰነ ወቅት ይኸውም ለ70 ዓመታት ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ የባቢሎን የሐሰት አማልክት ይጠፋሉ፣ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ከፍ ከፍ ይላል!

ከይሖዋ ድርጅት ጋር ከልብ መጣበቅ

10. በታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ሥር የነበሩትን የዚህ የ20ኛው መቶ ዘመን የይሖዋን ሕዝቦች በሚመለከት ምን ጥያቄ ይነሣል?

10 ዛሬ በመጀመሪያዋ ባቢሎን ምድር ብቻ ያልተወሰነች ዓለም አቀፍ የሆነች ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ የምትጠራ ሃይማኖታዊ ድርጅት አለች። በጥንትዋ ባቢሎን ውስጥ የነበሩት አይሁዶች የልብ ዝንባሌ ከጥንትዋ እስራኤል አምላክ እንደመጣ ተግሳጽ ተደርጎ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ ላሉትና በኃይል በመገደድ በታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ሥር እንዲወድቁ ለተደረጉት የይሖዋ ሕዝቦች ምሳሌ የሚሆን ነበርን?

11. (ሀ) ታማኝ አይሁዶች ትውልድ አገራቸው ከአእምሮአቸው እንድትፋቅ አደረጉን? (ለ) ምርኮኛው መዝሙራዊ የምርኮኛ ጓደኞቹን ስሜት የገለጸው እንዴት ነበር?

11 ግዞቱ ለአንድ ትውልድ የሚቆይ በመሆኑ በባቢሎን ውስጥ ተረጋግተው መኖርና ልክ በአገራቸው ውስጥ እንዳሉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችል የነበረ ቢሆንም የትውልድ አገራቸው ከትዝታቸው ተፋቀን? ምርኮኛው መዝሙራዊ የምርኮኛ ጓደኞቹን ስሜት ሲናገር ውብ በሆነ መንገድ ይገልጸዋል:- “ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ብረሳሽ፣ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፣ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፣ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።”— መዝሙር 137:5, 6

12. የምርኮኛው መዝሙራዊ የልብ ዝንባሌ የሚገልጸው ምንን ነው?

12 ይህ የምርኮኞቹ እስራኤላውያን የልብ ዝንባሌ የሚገልጸው ነገር ምንድን ነው? አምላክ ለተመረጡት ሕዝቦቹ የሰጣት ምድር ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና እንድትቆይ ባደረገበት ወቅት በዚያን ጊዜ ለነበረችው የምትታይ የይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆንን ነው። አዎን በእነዚያ እስራኤላውያን ልብ ውስጥ የምትታየው የይሖዋ ድርጅት ሕያው ሆና ቀጥላ ነበር።

13. ለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆን ሽልማት ያስገኘው እንዴት ነው?

13 ለጥንቷ የአምላክ የሚታይ ድርጅት እንዲህ ያለውን ታማኝነት ማሳየቱ በጊዜው አጸፋውን ካሣ አስገኝቷል። ይህም የሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሦስተኛዋ የዓለም ኃያል ባቢሎን በተገለበጠችበትና አራተኛው የዓለም ኃያል ሜዶፋርስ የእስራኤልን አምላክ ፈቃድ በፈጸመበት ጊዜ ነበር። እንዴት? ምርኮኞቹን አይሁዳውያንን የዋና ከተማዋ የኢየሩሳሌም እምብርት አድርገው የአምላካቸውን ቤተመቅደስ እንደገና እንዲሠሩ መመሪያ በመስጠት ወደሚታየው የይሖዋ ድርጅት ምድር በመመለስ ነበር። (2 ዜና 36:22, 23) እንደገና የሚሠራው የእውነተኛው አምልኮ ቤተመቅደስ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛበት ከተማ ለመሆን በቅጥር የተከበበች ከተማ ኢየሩሳሌም ጭምር መሠራት ነበረባት።

14. (ሀ) ከአያሌ መቶ ዘመናት በኋላ መሲሑ ስለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ምን አለ? (ለ) ይሖዋ ከኢየሩሳሌም ሆኖ የሚገዛው በምን መንገድ ነው?

14 ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከስድስት መቶ ዘመናት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና።” (ማቴዎስ 5:34, 35) መሲሑ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንደገና የተሠራው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ውስጥ ቆሞ ነበር፤ በምሳሌያዊ አባባልም ይሖዋ አምላክ በዚያ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ ይገዛ ነበር። ስለዚህ የሕዝቡ ዋና ከተማ ከሆነችው ከኢየሩሳሌም ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ ላይ ይገዛ ነበር።

ይሖዋ ለድርጅቱ ታማኝ ሆኖ ይቀጥላል

15. ኢየሱስ ታማኝ ያልነበሩትን የእስራኤል የሃይማኖት መሪዎች ሲያጋልጥ የሚታየውን የይሖዋን ድርጅት ክፍል ማስወገዱ ነበርን? አብራራ።

15 ታዲያ ኢየሱስ ታማኝ ያልነበሩትን የእስራኤል የሃይማኖት መሪዎች ሲያጋልጥና ሲያወግዝ የአምላክን የሚታይ ድርጅት ማስወገዱ ነበርን? አዎን፤ ምክንያቱም እንዲህ ብሏል:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጭቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” (ማቴዎስ 23:37, 38) ኢየሱስ ኢየሩሳሌምንና ‘ልጆችዋን’ ሲተዋቸው ሰማያዊ አባቱን ያለ ምንም ምድራዊ ድርጅት ማስቀረቱ ነበርን? አልነበረም! ምክንያቱም የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ሊሠራው ላለው አዲስ የማይታይ ድርጅት ኢየሱስ ራሱ መሠረት ነበር።

16. ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በሞተበት ጊዜ አምላክ ሥጋዊ እስራኤላውያንን እንደ ተዋቸው የታየው እንዴት ነበር?

16 የሥጋዊ እስራኤላውያን መወገድ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ሲሞት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የነበረችውን ቅድስተ ቅዱሳን ከቅድስት የሚለየው ወፍራም መጋረጃ “ከላይ እስከ ታች” በተቀደደ ጊዜ ታይቷል። በዚያኑ ጊዜ “ምድርም ተናወጠች፣ ዓለቶችም ተሰነጠቁ።” እነዚህ ተዓምራዊ ድርጊቶች በአንድ ዓይነተኛ መንገድ በዚያ ይገዛ የነበረው አምላክ የእስራኤልን ሕዝብና ሃይማኖቷን እንደተዋቸው የሚያሳዩ ነበሩ።— ማቴዎስ 27:51

17. ኢየሱስና ይሖዋ ለአዲሱ ለሚታየው የአምላክ ድርጅት የወደፊት አባሎች ታማኝነትን ያሳዩት እንዴት ነው?

17 ይሖዋ አምላክ በቅርቡ ሊገነባው የነበረው የአዲሱ የሚታይ ድርጅት የወደፊት አባሎች በኢየሩሳሌም ውስጥ ቀርተው ነበር። ኢየሱስ ስለ አንድ ስለሚበልጥ ነገር ሲል ምድራዊቷን ከተማ ለተወው አምላክ አደራ ሰጥቷቸው ነበር። (ዮሐንስ 17:9–15) በዚህ መንገድ ይሖዋ ለታማኝ አባቶቻቸው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ እንዲሁም ለ12ቱ የያዕቆብ ልጆች ልዩ ትኩረትን በማሳየት ለድርጅቱ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። (ዳንኤል 12:1) የሚቀጥለው ምዕራፍ በመዝሙር 137 ላይ በመመሥረት የታማኝነት ትምህርታችንን በሰፊው ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7  ከጥንትዋ ባቢሎን የተገኘ አንድ በኩኒፎርም ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በጠቅላላው በባቢሎን ውስጥ ለዋነኞቹ አማልክት 53 ቤተመቅደሶች፣ ለማርዱክ 55 የጸሎት ቤቶች፣ ለምድራዊ አማልክት 300 የጸሎት ቤቶች፣ ለሰማያዊ አማልክት 600፣ ኢሽታር ለምትባለው የሴት አምላክ 180 መሠዊያዎች፣ ኔርጋልና አዳድ ለሚባሉ አምላኮች 180፣ ለተለያዩ አማልክት ደግሞ ሌሎች 12 መሠዊያዎች ነበሩ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]