ትምህርት 5
የአምላክ ወዳጆች በገነት ውስጥ ይኖራሉ
ገነት አሁን ከምንኖርበት ዓለም ፈጽሞ የተለየች ናት። አምላክ ምድር በመከራና በሐዘን፣ በህመምና በሥቃይ እንድትሞላ ፈጽሞ አይፈልግም ነበር። አምላክ ወደፊት ምድርን ገነት ያደርጋታል። ገነት ምን ትመስል ይሆን? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት:-
ጥሩ ሰዎች። ገነት የአምላክ ወዳጆች መኖሪያ ትሆናለች። አንዳቸው ለሌላው መልካም ነገሮችን ያደርጋሉ። አምላክ ካወጣቸው የጽድቅ መንገዶች ጋር ተስማምተው ይኖራሉ።—ምሳሌ 2:21
የተትረፈረፈ ምግብ። በገነት ውስጥ ረሃብ አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ “በምድሩ ላይ በቂ [“የተትረፈረፈ፣” NW] ምግብ ይኑር” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 72:16 የ1980 ትርጉም
ጥሩ ቤቶችና አስደሳች ሥራ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ ቤት ይኖረዋል። እያንዳንዱ ሰው በሚሠራው ሥራ እውነተኛ ደስታ ያገኛል።—ኢሳይያስ 65:21-23
ዓለም አቀፍ ሰላም። እርስ በርሳቸው የሚዋጉና በጦርነት የሚሞቱ ሰዎች አይኖሩም። የአምላክ ቃል “[እግዚአብሔር] ጦርነትንም ይቆርጣል” በማለት ይናገራል።—ጥሩ ጤና። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያም [በገነት ውስጥ] የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 33:24) በተጨማሪም ሽባ ወይም ዓይነ ሥውር ወይም መስማት የተሳነው ወይም መናገር የማይችል ሰው አይኖርም።—ኢሳይያስ 35:5, 6
ሥቃይ፣ ሐዘንና ሞት ያከትማሉ። የአምላክ ቃል “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” በማለት ይናገራል።—ራእይ 21:4
መጥፎ ሰዎች ድምጥማጣቸው ይጠፋል። ይሖዋ “ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ” በማለት ቃል ይገባል።—ምሳሌ 2:22
ሰዎች እርስ በርሳቸው ተዋድደውና ተከባብረው ይኖራሉ። የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆና፣ ስግብግብነትና ጥላቻ አይኖርም። ሰዎች አንድ ሆነው አምላክ ካወጣቸው የጽድቅ መንገዶች ጋር ተስማምተው ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 26:9