ትምህርት 1
አምላክ ወዳጁ እንድትሆን ይጋብዝሃል
አምላክ ወዳጁ እንድትሆን ይፈልጋል። በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉም በላይ ታላቅ ከሆነው አካል ጋር ወዳጅ መሆን እንደምትችል አስበህ ታውቃለህ? ጥንት ይኖር የነበረው አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ተብሎ ተጠርቷል። (ያዕቆብ 2:23) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ሰዎችም የአምላክ ወዳጅ የነበሩ ሲሆን በብዙ ተባርከዋል። ዛሬ በተለያዩ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎችም ከአምላክ ጋር ወዳጅነትን መሥርተዋል። አንተም የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ።
የአምላክ ወዳጅ መሆን ከማንም ሰው ጋር ከመወዳጀት የሚበልጥ ነው። አምላክ ታማኝ ወዳጆቹን ፈጽሞ አያስቀይማቸውም። (መዝሙር 18:25፣ የ1980 ትርጉም) የአምላክ ወዳጅ መሆን ባለጠጋ ከመሆን የተሻለ ነው። ባለጠጋ የሆነ ሰው ሲሞት ገንዘቡን ሌሎች ሰዎች ይወስዱታል። የአምላክ ወዳጅ የሆኑ ግን ማንም ሊወስደው የማይችለው ሃብት አላቸው።—ማቴዎስ 6:19
አንዳንድ ሰዎች ስለ አምላክ መማርህን እንድታቆም ለማድረግ ሊሞክሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጓደኞችህና የቤተሰብህ አባሎች እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ማቴዎስ 10:36, 37) ሰዎች ቢስቁብህ ወይም ቢያስፈራሩህ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ:- ‘ማስደሰት የምፈልገው ማንን ነው? ሰዎችን ወይስ አምላክን?’ እስቲ አስበው:- አንድ ሰው ምግብ እንዳትበላ ቢከለክልህ እሺ ብለህ ትታዘዘዋለህ? እሺ እንደማትለው የታወቀ ነው! ለመኖር ምግብ መመገብ ይኖርብሃል። አምላክ ደግሞ ለዘላለም እንድትኖር ሊያደርግ ይችላል! ስለዚህ የአምላክ ወዳጅ መሆን ስለምትችልበት መንገድ የምታደርገውን ጥናት ማንም ሰው እንዲያስቆምህ አትፍቀድ።—ዮሐንስ 17:3