በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 10

ጋብቻ—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ

ጋብቻ—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ

‘በሦስት የተገመደ ገመድ ቶሎ አይበጠስም።’መክብብ 4:12

1, 2. (ሀ) አዲስ ተጋቢዎችን ስንመለከት ምን ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል? ለምንስ? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሠርግ መሄድ ደስ ይልሃል? እንዲህ ያለው አጋጣሚ አስደሳች ስለሆነ ብዙዎች ሠርግ መሄድ ይወዳሉ። በሠርጋቸው ዕለት ሙሽሮቹ በጣም አምሮባቸው ትመለከታለህ። ከዚህም በላይ ፊታቸው በደስታ ያበራል! የዚህን ዕለት ያህል የተደሰቱበት ቀን የለም፤ የወደፊቱ ጊዜም ብሩህ ሆኖ ይታያቸዋል።

2 ይሁንና በዛሬው ጊዜ ጋብቻ ከብዙ አቅጣጫ ሲታይ እየተፈረካከሰ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። አዲስ ለተጋቡ ሙሽሮች መልካሙን ሁሉ ብንመኝላቸውም ‘ይህ ትዳር ደስታ የሰፈነበትና ዘለቄታ ያለው ይሆን?’ ብለን የምናስብበት ጊዜም አለ። የዚህ ጥያቄ መልስ የተመካው፣ ባልና ሚስቱ አምላክ ጋብቻን በተመለከተ በሰጣቸው ምክሮች ላይ በመታመናቸውና እነዚህን ምክሮች በተግባር ለማዋል ጥረት በማድረጋቸው ላይ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚፈልጉ ባልና ሚስት ይህን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት አራት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት:- አንድ ሰው ትዳር የሚመሠርተው ለምንድን ነው? ትዳር ለመመሥረት ከወሰንክ ደግሞ የትዳር ጓደኛ እንዲሆንህ መምረጥ የሚኖርብህ ማንን ነው? ለጋብቻ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ባልና ሚስት በትዳራቸው ደስተኞች እንዲሆኑ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

አንድ ሰው የሚያገባው ለምንድን ነው?

3. አንድ ሰው አጥጋቢ ባልሆኑ ምክንያቶች ተገፋፍቶ ማግባቱ ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?

3 አንዳንዶች ጋብቻ ለደስታ የግድ አስፈላጊ እንደሆነና የትዳር ጓደኛ ካላገኘህ በሕይወትህ ደስተኛ መሆን እንደማትችል ይሰማቸዋል። ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው! ሳያገባ የኖረው ኢየሱስ ሳያገቡ መኖር ስጦታ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ ሊቀበለው የሚችል ሁሉ እንዲቀበለው መክሯል። (ማቴዎስ 19:11, 12) ሐዋርያው ጳውሎስም ሳያገቡ መኖር ስላሉት ጥቅሞች ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 7:32-38) ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት ሕግ አላወጡም። እንዲያውም ‘ማግባትን መከልከል’ ‘ከአጋንንት ትምህርቶች’ መካከል ተመድቧል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1-3) ያም ሆኖ ትኩረታቸው ሳይከፋፈል ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ሳያገቡ መኖራቸው የሚያስገኝላቸው ጥቅም አለ። በመሆኑም አንድ ሰው ሌሎች ተጽዕኖ ስላሳደሩበት ወይም አጥጋቢ ባልሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ተገፋፍቶ ለማግባት መወሰኑ ጥበብ አይሆንም።

4. ጥሩ ትዳር ልጆችን ለማሳደግ ምን ዓይነት መሠረት ይሆናል?

4 በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው ጋብቻን ለመመሥረት እንዲወስን የሚያነሳሱት በቂ ምክንያቶች ይኖራሉ? አዎ፣ አሉ። ሳያገቡ መኖር ስጦታ እንደሆነው ሁሉ ጋብቻም አፍቃሪ ከሆነው አምላካችን ያገኘነው ስጦታ ነው። (ዘፍጥረት 2:18) ስለሆነም ጋብቻ መመሥረት የራሱ የሆኑ አንዳንድ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን በረከቶችንም ሊያስገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ትዳር ለቤተሰብ ሕይወት ጥሩ መሠረት ነው። ልጆች ከወላጆቻቸው ፍቅር፣ ተግሣጽና መመሪያ አግኝተው የሚያድጉበት የተረጋጋ ሁኔታ ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 127:3፤ ኤፌሶን 6:1-4) ይሁን እንጂ ጋብቻ የሚመሠረተው ልጆች ወልዶ ለማሳደግ ሲባል ብቻ አይደለም።

5, 6. (ሀ) በመክብብ 4:9-12 መሠረት የቅርብ ጓደኝነት መመሥረት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? (ለ) ጋብቻ በሦስት እንደተገመደ ገመድ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

5 እስቲ ይህ ምዕራፍ የተመሠረተበትን ጥቅስና በጥቅሱ ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች ተመልከት:- “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል። ቢወድቅ የሚያነሣው ረዳት የሌለው ግን፣ እንዴት አሳዛኝ ነው! ደግሞም ሁለቱ አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ ነገር ግን አንዱ ብቻውን እንዴት ሊሞቀው ይችላል? አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል፤ በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።”መክብብ 4:9-12

6 ይህ ጥቅስ በዋነኝነት የሚናገረው ጓደኝነት ስለሚያስገኘው ጥቅም ነው። እርግጥ ነው፣ በጋብቻ ከመቆራኘት የበለጠ የሚያቀራርብ ጓደኝነት የለም። ይህ ጥቅስ እንደሚያሳየው እንዲህ ያለው ቁርኝት ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ፣ እንዲጽናኑና አንዳቸው ሌላውን እንዲጠብቁ ያስችላቸዋል። ጋብቻ ይበልጥ ጥንካሬ እንዲኖረው የሁለቱ ግለሰቦች መተሳሰር ብቻውን በቂ አይደለም። በዚህ ጥቅስ መሠረት በሁለት የተገመደ ገመድ ሊበጠስ ይችላል። በሦስት የተገመደ ገመድ ግን በቀላሉ ሊበጠስ አይችልም። ባልም ሆነ ሚስት በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ይሖዋን የማስደሰት ጉዳይ ከሆነ ጋብቻቸው በሦስት እንደተገመደው ገመድ ይሆናል። በትዳራቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ይሖዋ ስለሆነ ጥምረታቸው በእርግጥም በጣም ጠንካራ ይሆናል።

7, 8. (ሀ) ጳውሎስ የጾታ ፍላጎታቸውን ለመቆጣጠር ለሚታገሉ ያላገቡ ክርስቲያኖች ምን ምክር ጽፏል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይመክረናል?

7 በተጨማሪም አንድ ወንድና አንዲት ሴት የጾታ ፍላጎታቸውን ማርካት የሚችሉበት ትክክለኛው መንገድ ጋብቻ ብቻ ነው። በትዳር ውስጥ የሚፈጸመው የጾታ ግንኙነት የደስታ ምንጭ እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 5:18) አንድ ያላገባ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” ብሎ የሚጠራውን የጾታ ስሜት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያይልበትን ዕድሜ ካለፈም በኋላ የጾታ ፍላጎቱን ለመቆጣጠር መታገል ሊጠይቅበት ይችላል። እንዲህ ያለው ፍላጎት ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ተገቢ ያልሆነ ወይም ርኩስ ድርጊት ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ላላገቡ ሰዎች “ራሳቸውን መግዛት ካቃታቸው ግን ያግቡ፤ ምክንያቱም በስሜት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል” የሚል ምክር ጽፏል።1 ቆሮንቶስ 7:9, 36፤ ያዕቆብ 1:15

8 አንድ ሰው ለማግባት እንዲወስን ያነሳሳው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከጋብቻ ስለሚያገኘው ነገር ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ ይኖርበታል። ጳውሎስ እንዳለው የሚያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:28) ባለትዳሮች ያላገቡ ሰዎች የማያጋጥሟቸው ችግሮች ይደርሱባቸዋል። ይሁን እንጂ ለማግባት ከወሰንክ ችግሮቹን መቀነስና ከጋብቻ የሚገኘውን ደስታና እርካታ ከፍ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ የትዳር ጓደኛህን በጥበብ በመምረጥ ነው።

ጥሩ የትዳር ጓደኛ የሚሆነው ምን ዓይነት ሰው ነው?

9, 10. (ሀ) ጳውሎስ ከማያምኑ ጋር መቆራኘት ያለውን አደጋ በምሳሌ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የማያምን ሰው ስለማግባት የሰጠውን ትእዛዝ ችላ ማለት ብዙውን ጊዜ ምን ውጤት ያስከትላል?

9 ጳውሎስ የትዳር ጓደኛ በምትመርጥበት ጊዜ መመሪያ ሊሆንህ የሚገባ አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ጽፏል። “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) የጳውሎስ ምሳሌ በግብርናው መስክ በሚሠራበት አንድ እውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። በመጠንም ሆነ በጉልበት የማይመጣጠኑ ሁለት እንስሳት አንድ ላይ ቢጠመዱ ሁለቱም ይጎዳሉ። በተመሳሳይም የሚያምንና የማያምን ሰው በጋብቻ ቀንበር አብረው ቢጠመዱ ግጭትና ውጥረት እንደሚፈጠር ምንም ጥርጥር የለውም። አንደኛው የትዳር ጓደኛ ከይሖዋ ፍቅር ሳይወጣ ለመኖር የሚፈልግ ቢሆንና ሌላኛው ወገን ይህ ጉዳይ እምብዛም የማያሳስበው ወይም ጭራሹኑ ደንታ የማይሰጠው ቢሆን፣ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች የተለያዩ ስለሚሆኑ ብዙ ችግር ይፈጠራል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ክርስቲያኖች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ መክሯል።—1 ቆሮንቶስ 7:39

10 አንዳንድ ያላገቡ ክርስቲያኖች ከአሁኑ የብቸኝነት ኑሯቸው ይልቅ አቻ ባልሆነ መንገድ መጠመድ ይሻላል ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ችላ ብለው ይሖዋን የማያገለግል ሰው አግብተዋል። ይሁንና ይህ ሁኔታ አሳዛኝ ውጤት እንደሚያስከትል በተደጋጋሚ ታይቷል። እንዲህ ያለውን እርምጃ የወሰዱ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡት ነገር ካገቡት ሰው ጋር ሊወያዩ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። በዚህ ምክንያት የሚሰማቸው የብቸኝነት ስሜት ከማግባታቸው በፊት ከነበሩበት የብቸኝነት ኑሮ እጅግ የከፋ ይሆንባቸዋል። የሚያስደስተው ግን በዚህ ረገድ የተሰጠው መለኮታዊ ትእዛዝ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው አምነው በታማኝነት የሚታዘዙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ያላገቡ ክርስቲያኖች አሉ። (መዝሙር 32:8) እነዚህ ክርስቲያኖች ወደፊት እንደሚያገቡ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ይሁንና ይሖዋ አምላክን ከሚያመልኩ መካከል የትዳር ጓደኛ የሚሆናቸው ሰው እስኪያገኙ ድረስ ሳያገቡ ይኖራሉ።

11. የትዳር ጓደኛ የሚሆንህን ሰው በጥበብ እንድትመርጥ ምን ሊረዳህ ይችላል? (በተጨማሪም “ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ ሳስብ ግምት ውስጥ ላስገባቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

11 እርግጥ ነው፣ ሁሉም የይሖዋ አገልጋይ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ይሆናል ማለት አይደለም። የማግባት ሐሳብ ካለህ በጠባዩ፣ ባሉት መንፈሳዊ ግቦችና ለአምላክ ባለው ፍቅር ከአንተ ጋር የሚጣጣም ሰው ለማግኘት ሞክር። ታማኝና ልባም ባሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጠቃሚ ሐሳብ ስለሰጠ እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች በጸሎት መመርመርህ አስተዋይነት ነው፤ እንዲህ ካደረግክ ይህንን ከባድ ውሳኔ ለማድረግ የአምላክ ቃል እንዲመራህ እንደምትፈልግ ታሳያለህ። *መዝሙር 119:105

12. በብዙ አገሮች ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ባሕል አለ? በዚህ ረገድ ትምህርት ሊሰጥ የሚችለው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው?

12 በብዙ አገሮች ወላጆች ለልጃቸው የትዳር ጓደኛ መምረጣቸው የተለመደ ነው። በእነዚህ ባሕሎች ወላጆች እንዲህ ያለውን ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል የተሻለ ብስለትና ተሞክሮ እንዳላቸው ይታመናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በወላጆች ምርጫ የሚመሠረት ጋብቻ ብዙውን ጊዜ የሰመረ ይሆናል። አብርሃም ለይስሐቅ ሚስት እንዲፈልግለት አገልጋዩን እንደላከ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በዛሬው ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ወላጆች ጥሩ ትምህርት ይሰጣል። አብርሃምን ያሳሰበው ገንዘብ ወይም የኑሮ ደረጃ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለልጁ ለይስሐቅ ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል ሚስት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። *ዘፍጥረት 24:3, 67

ጋብቻህ የተሳካ እንዲሆን አስቀድመህ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

13-15. (ሀ) በምሳሌ 24:27 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት የማግባት ሐሳብ ያለውን አንድ ወጣት የሚረዳው እንዴት ነው? (ለ) አንዲት ወጣት ሴት ለጋብቻ ዝግጁ ለመሆን ምን ልታደርግ ትችላለች?

13 ጋብቻ ስለ መመሥረት በቁም ነገር እያሰብክ ከሆነ ‘ጋብቻ ለመመሥረት ዝግጁ ነኝ?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል። ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ስለ ፍቅር፣ ስለ ጾታ ፍላጎት፣ ስለ ጓደኝነት ወይም ልጆች ስለ መውለድ ባለህ ስሜት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለማግባት የሚፈልጉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሊያስቡባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ።

14 ማግባት የሚፈልግ አንድ ወጣት ወንድ “በደጅ ያለውን ሥራህን ፈጽም፤ ዕርሻህን አዘጋጅ፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” ስለሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ማሰብ ይኖርበታል። (ምሳሌ 24:27) ይህ ጥቅስ ምን ትርጉም አለው? በዚያ ዘመን አንድ ሰው ‘ቤት ለመሥራት’ ወይም ሚስት አግብቶ ቤተሰብ ለመመሥረት ከፈለገ፣ ‘ሚስቴንና የምንወልዳቸውን ልጆች ለመንከባከብ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። አስቀድሞ እርሻውን ወይም ሰብሉን በመንከባከብ በውጭ መሥራት ይኖርበታል። ዛሬም ቢሆን ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። ለማግባት የሚፈልግ ሰው ጋብቻው የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆን ያስፈልገዋል። አቅሙ እስካለው ድረስ መሥራት ይኖርበታል። የአምላክ ቃል፣ ቤተሰቡ በቁሳዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ የሚያስፈልገውን ሁሉ የማያቀርብ ሰው እምነትን ከካደ ሰው የሚከፋ እንደሆነ ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

15 ለማግባት የወሰነች ሴትም በተመሳሳይ በርካታ ኃላፊነቶችን ለመሸከም ተስማምታለች ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ሚስት ባሏን በምታግዝበትና ቤተሰቧን በምትንከባከብበት ጊዜ ስለሚያስፈልጓት አንዳንድ ባሕርያትና ችሎታዎች ይናገራል። (ምሳሌ 31:10-31) ኃላፊነቶቻቸውን ለመሸከም የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት ሳያደርጉ ተቻኩለው ጋብቻ ውስጥ የሚገቡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የትዳር ጓደኛቸው ለሚሆነው ሰው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስላላሰቡ በእርግጥም ራስ ወዳዶች ናቸው። ከሁሉ በላይ ግን ለማግባት የሚያስቡ ሁሉ በመንፈሳዊ የተዘጋጁ መሆን ይገባቸዋል።

16, 17. ለማግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች በየትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰል አለባቸው?

16 ጋብቻ ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረግ አምላክ ለባልና ለሚስት በሰጠው የሥራ ድርሻ ላይ ማሰላሰልን ይጨምራል። አንድ ወንድ የአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ራስ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገዋል። ራስ መሆን አምባገነን መሆን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ወንድ ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበትን መንገድ መኮረጅ ይኖርበታል። (ኤፌሶን 5:23) በተመሳሳይም አንዲት ክርስቲያን ሴት፣ ሚስት ያላትን የተከበረ ቦታ መረዳት ያስፈልጋታል። ‘ለባሏ ሕግ’ ለመገዛት ፈቃደኛ ትሆናለች? (ሮሜ 7:2) መጀመሪያውኑም ቢሆን በይሖዋና በክርስቶስ ሕግ ሥር ነች። (ገላትያ 6:2) ባሏ በቤተሰቡ ውስጥ ያለው ሥልጣን ደግሞ ሌላ ሕግ ነው። ፍጽምና የሚጎድለውን ሰው ሥልጣን ለመደገፍና ለዚህ ሥልጣን ለመገዛት ፈቃደኛ ትሆናለች? ይህ የማይዋጥላት ከሆነ ባታገባ የተሻለ ነው።

17 ከዚህም በላይ የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው የሌላውን የተለየ ፍላጎት ለማሟላት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ጳውሎስ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል” ሲል ጽፏል። በአምላክ መንፈስ ተመርቶ ይህን ሐሳብ የጻፈው ጳውሎስ፣ ባል ሚስቱ በጥልቅ እንደምታከብረው እንዲሰማው እንደሚፈልግ ተገንዝቧል። ሚስትም በባሏ የመወደድ የተለየ ፍላጎት አላት።ኤፌሶን 5:21-33

ለጋብቻ በመጠናናት ላይ ያሉ ወንድና ሴት ብቻቸውን ከመሆን ይልቅ ሌላ ሰው አብሯቸው እንዲኖር ዝግጅት ያደርጋሉ

18. አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጠናኑበት ጊዜ ራሳቸውን መግዛት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

18 በዚህም ምክንያት አንድ ወንድና አንዲት ሴት በመጠናናት የሚያሳልፉት ጊዜ በጨዋታ ብቻ የሚያልፍ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ይህ ወቅት አንዳቸው ሌላውን እንዴት በአግባቡ መያዝ እንደሚችሉ የሚማሩበት፣ እንዲሁም መጋባታቸው የጥበብ እርምጃ መሆን አለመሆኑን የሚወስኑበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ነው! በጋብቻ ውስጥ ብቻ ሊኖር የሚገባው መቀራረብ እንዲኖራቸው መፈለግ ተፈጥሯዊ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ ከልብ የሚዋደዱ ወንድና ሴት የሚወዱትን ሰው መንፈሳዊነት የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ይርቃሉ። (1 ተሰሎንቄ 4:6) ስለዚህ በመጠናናት ላይ የምትገኝ ከሆነ ራስህን ግዛ። ራስን የመግዛት ባሕርይ ብታገባም ባታገባም ዕድሜህን በሙሉ የሚጠቅምህ ባሕርይ ነው።

ጋብቻህ ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

19, 20. አንድ ክርስቲያን ስለ ጋብቻ ያለው አመለካከት በዛሬው ጊዜ ካሉ በርካታ ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

19 አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጋብቻቸው ዘላቂ እንዲሆን ከፈለጉ፣ ስለ ጋብቻ ቃል ኪዳን ትክክለኛ የሆነ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። ልብ ወለድ መጻሕፍትና ፊልሞች በአብዛኛው የሚደመደሙት ሰዎች በሚፈልጉት መንገድ ይኸውም ባለታሪኮቹ ተጋብተው በደስታ እንደኖሩ በመግለጽ ነው። በገሃዱ ዓለም ግን ጋብቻ ፍጻሜ ወይም መደምደሚያ ሳይሆን ይሖዋ ዘላቂ ሆኖ እንዲኖር ያቀደው ነገር መጀመሪያ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) በዛሬው ጊዜ ግን ብዙዎች እንዲህ ያለው አመለካከት የሌላቸው መሆኑ ያሳዝናል። በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች ጋብቻን ከገመድ ቋጠሮ ጋር ያመሳስሉታል። እነዚህ ሰዎች ባያስተውሉትም እንኳ ይህ ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ሰዎች ለጋብቻ ያላቸውን አመለካከት በጥሩ ሁኔታ ይገልጻል። እንዴት? በደንብ የታሰረ ቋጠሮ እስከተፈለገበት ጊዜ ድረስ ጥብቅ አድርጎ መያዝ ያለበት ቢሆንም ሲፈለግ የሚታሰር ሲፈለግ ደግሞ በቀላሉ የሚፈታ መሆኑም አስፈላጊ ነው።

20 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጋብቻን ጊዜያዊ ትስስር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ፍላጎታቸውን የሚያሟላ እንደሆነ ስለተሰማቸው ብዙም ሳያስቡበት ትዳር ውስጥ ዘው ብለው ይገባሉ፤ ሆኖም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ወዲያው ትተውት መውጣት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ጋብቻ ያለውን ትስስር ከገመድ ጋር እንደሚያመሳስለው አስታውስ። ለመርከብ ጉዞ የሚያገለግሉ ገመዶች ኃይለኛ አውሎ ነፋስና ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ጊዜ እንኳ እንዳይፈቱ ወይም እንዳይበተኑ ሆነው የተገመዱ ናቸው። በተመሳሳይም አምላክ የጋብቻን ዝግጅት የመሠረተው ዘላቂ እንዲሆን አስቦ ነው። ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ሲል እንደተናገረ አስታውስ። (ማቴዎስ 19:6) አንተም ካገባህ ለጋብቻ ይህን የመሰለ አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። የጋብቻ ቃል ኪዳን ዕድሜ ልክ መዝለቅ ያለበት መሆኑ ጋብቻን ሸክም እንዲሆን ያደርገዋል? አያደርገውም።

21. ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? እንዲህ እንዲያደርጉስ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

21 ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ትክክለኛ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። አንደኛው ወገን ሌላው ባሉት በጎ ባሕርያትና በሚያደርገው ጥረት ላይ ትኩረት ቢያደርግ የትዳር ሕይወታቸው የደስታና የእርካታ ምንጭ ይሆንላቸዋል። ፍጽምና የሚጎድለውን ግለሰብ በዚህ መንገድ መመልከት ሊሆን የማይችል ወይም ከእውነታው የራቀ ነገር ነው? ይሖዋ ለሰዎች ያለው አመለካከት ከእውነታው የራቀ አይደለም፤ ቢሆንም የእኛን መልካም ጎን እንዲመለከት እንፈልጋለን። መዝሙራዊው “ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” ሲል ጠይቋል። (መዝሙር 130:3) በተመሳሳይም ባልና ሚስቶች አንዳቸው የሌላውን በጎ ባሕርይ መመልከትና ይቅር ባይ መሆን ያስፈልጋቸዋል።ቆላስይስ 3:13

22, 23. አብርሃምና ሣራ በዘመናችን ለሚኖሩ ባልና ሚስቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?

22 ጋብቻ ዓመታት ባስቆጠረ መጠን የበለጠ አስደሳች እየሆነ ይሄዳል። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምና ሣራ በስተርጅና ስለነበራቸው የትዳር ሕይወት ይነግረናል። ሕይወታቸው ከችግር ነፃ የሆነ አልነበረም። በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ትገኝ የነበረችው ሣራ ሀብታም በሆነችው በዑር ከተማ የነበራትን የሞቀ ቤት ትታ ቀሪውን የሕይወት ዘመኗን በድንኳን ውስጥ ስትኖር ምን ሊሰማት እንደሚችል አስብ። ቢሆንም ለባሏ የራስነት ሥልጣን ተገዝታለች። ለአብርሃም እውነተኛ ረዳትና ማሟያ በመሆን ውሳኔው የተሳካ ውጤት እንዲያስገኝ በአክብሮት ረድታዋለች። ትገዛለት የነበረውም ለይስሙላ ብቻ አልነበረም። “በልቧ” ሳይቀር ባሏን ጌታዬ ብላ ትጠራው ነበር። (ዘፍጥረት 18:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:6) በእርግጥም ሣራ ለአብርሃም የነበራት አክብሮት ከልብ የመነጨ ነበር።

23 እንዲህ ሲባል ግን አብርሃምና ሣራ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው ማለት አይደለም። ሣራ በአንድ ወቅት አብርሃምን ‘በእጅጉ ያስጨነቀውን’ ሐሳብ አቅርባ ነበር። ቢሆንም አብርሃም ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ሰምቶ ሚስቱ ያለችውን በትሕትና ተቀበለ፤ ይህም ለቤተሰቡ በረከት አስገኝቷል። (ዘፍጥረት 21:9-13) ዛሬም ባልና ሚስቶች፣ ከተጋቡ በርካታ ዓመታት ያሳለፉትም ቢሆኑ፣ ከእነዚህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ባልና ሚስት ብዙ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ።

24. ይሖዋን የሚያስከብሩ ትዳሮች እንዴት ያሉ ናቸው? ለምንስ?

24 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ፣ ደስታ የሰፈነበት የትዳር ሕይወት የሚመሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ባልና ሚስቶች አሉ። በእነዚህ ትዳሮች ውስጥ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታከብረዋለች፣ ባልም ሚስቱን ይወዳታል እንዲሁም ያከብራታል፣ ሁለቱም ከማንኛውም ነገር ይበልጥ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ይጥራሉ። ለማግባት ከወሰንክ የትዳር ጓደኛህን በጥበብ ምረጥ፣ ለጋብቻህ ጥሩ ዝግጅት አድርግ፣ ይሖዋ አምላክን የሚያስከብር እንዲሁም ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት ትዳር እንዲኖርህ ጥረት አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ጋብቻህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር እንደሚረዳህ ጥርጥር የለውም።

^ አን.11 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ተመልከት።

^ አን.12 አንዳንድ ታማኝ የእምነት አባቶች ከአንድ በላይ ሚስቶች ነበሯቸው። ይሖዋ ከእምነት አባቶችና ከእስራኤላውያን ጋር ግንኙነት በነበረው ዘመን ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን ፈቅዶ ነበር። እንዲህ ያለውን ልማድ ያቋቋመው እሱ ባይሆንም አለአግባብ እንዳይጠቀሙበት ገደብ አውጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ይሖዋ በዚህ ዘመን አምላኪዎቹ ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ይገነዘባሉ።—ማቴዎስ 19:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2