በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 2

ጥሩ ሕሊና ይዘህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

ጥሩ ሕሊና ይዘህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

“ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።”1 ጴጥሮስ 3:16

1, 2. ኮምፓስ በጣም አስፈላጊ መሣሪያ የሆነው ለምንድን ነው? ከሕሊና ጋር ሊመሳሰል የሚችለውስ እንዴት ነው?

አንድ መርከበኛ በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ ሞገዱን እየሰነጠቀ ይጓዛል፤ አንድ መንገደኛ ጭው ባለው በረሃ ላይ በእግሩ ይገሰግሳል፤ አንድ አውሮፕላን አብራሪ ደግሞ ከአድማስ አድማስ ከተዘረጋው ደመና በላይ ይበርራል። እነዚህን ግለሰቦች የሚያመሳስላቸው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ሦስቱም አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ መሣሪያ ባይኖራቸው በተለይ ደግሞ ሌሎች ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም ባይችሉ ከባድ ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።

2 ኮምፓስ፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚያመለክት ባለ ማግኔት ቀስት ያለው ውስብስብ ያልሆነ መሣሪያ ነው። በትክክል የሚሠራ ከሆነ በተለይ ደግሞ ትክክለኛ ከሆነ ካርታ ጋር ተቀናጅቶ አገልግሎት ላይ ከዋለ ሕይወት አድን ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ መንገዶች ኮምፓስ ይሖዋ ከሰጠን አንድ ውድ ስጦታ ማለትም ከሕሊና ጋር ይመሳሰላል። (ያዕቆብ 1:17) ሕሊና ባይኖረን ኖሮ ባዝነን እንጠፋ ነበር። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ደግሞ ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና እንድናገኝና ከዚያ እንዳንወጣ ሊረዳን ይችላል። ስለዚህ ሕሊና ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚሠራ እንመርምር። ከዚያም የሚከተሉትን ነጥቦች እንመለከታለን። (1) ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? (2) የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (3) ጥሩ ሕሊና ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

ሕሊና ምንድን ነው? የሚሠራውስ እንዴት ነው?

3. “ሕሊና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፍቺ ምንድን ነው? ሰዎች ያላቸውን የትኛውን ልዩ ችሎታ ያመለክታል?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሕሊና” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “አብሮ ያለ እውቀት ወይም ከራስ ጋር ያለ እውቀት” የሚል ፍቺ አለው። ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በተለየ እኛ ሰዎች ከአምላክ ያገኘነው ራሳችንን የማወቅ ችሎታ አለን። ቆም ብለን ራሳችንን ማየትና ከሥነ ምግባር አኳያ ያለንን አቋም መመዘን እንችላለን። ሕሊናችን በውስጣችን እንዳለ አንድ ምሥክር ወይም ዳኛ ሆኖ ድርጊታችንን፣ ዝንባሌያችንንና ውሳኔያችንን ይመረምራል። ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ወይም መጥፎ ውሳኔ እንዳናደርግ ሊያስጠነቅቀን ይችላል። በኋላም ጥሩ ውሳኔ ካደረግን ያመሰግነናል፣ መጥፎ ውሳኔ ካደረግን ደግሞ በጸጸት አለንጋ ይገርፈናል።

4, 5. (ሀ) አዳምና ሔዋን ሕሊና እንደነበራቸው እንዴት እናውቃለን? የአምላክን ሕግ በመተላለፋቸው ምን ደረሰባቸው? (ለ) ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ሕሊናቸውን ያዳምጡ እንደነበር የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ?

4 የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ሲፈጠሩ ጀምሮ ይህ ችሎታ አብሯቸው ነበር። አዳምም ሆነ ሔዋን ሕሊና እንዳላቸው አሳይተዋል። ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ማፈራቸውና መሸማቀቃቸው ሕሊና እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። (ዘፍጥረት 3:7, 8) የሚያሳዝነው ግን ሕሊናቸው በዚያ ሰዓት የረበሻቸው መሆኑ የሚፈይደው ነገር አልነበረም። ሆን ብለው የአምላክን ሕግ ተላልፈዋል። በዚህ መንገድ እያወቁ ዓመጸኞችና የይሖዋ አምላክ ተቃዋሚዎች ሆነዋል። ፍጹማን ስለነበሩ ምን እያደረጉ እንዳሉ ያውቁ ነበር፤ በመሆኑም ወደ አምላክ መመለስ አልቻሉም።

5 ከአዳምና ከሔዋን በተለየ ፍጹማን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ሕሊናቸው የሚነግራቸውን አዳምጠዋል። ለምሳሌ፣ ታማኙ ኢዮብ “ጽድቄን አጥብቄ እይዛለሁ፤ አልለቀውምም፤ በዘመኔም ሁሉ ኅሊናዬ አይወቅሰኝም” ለማለት ችሎ ነበር። (ኢዮብ 27:6) በእርግጥም ኢዮብ ማንኛውንም ነገር ሲያከናውንም ሆነ ውሳኔዎችን ሲያደርግ ሕሊናው የሚነግረውን በጥንቃቄ የሚያዳምጥ ሰው ነበር። በመሆኑም ሕሊናውን የሚወቅሰው ወይም በኀፍረትና በጥፋተኝነት ስሜት የሚያሠቃየው አንዳች ነገር እንደሌለ አፉን ሞልቶ መናገር ችሏል። በኢዮብና በዳዊት መካከል የነበረውን ልዩነት ልብ በል። ዳዊት ይሖዋ በቀባው ንጉሥ በሳኦል ላይ አክብሮት የጎደለው ድርጊት በፈጸመ ጊዜ “ልቡ በሐዘን ተመታ።” (1 ሳሙኤል 24:5) ዳዊት ሕሊናው የወቀሰው መሆኑ ጠቅሞታል፤ ከዚያ በኋላ እንደዚያ ያለ አክብሮት የጎደለው ተግባር እንዳይፈጽም ትምህርት አግኝቷል።

6. ሕሊና ለሁሉም ሰው የተሰጠ ስጦታ መሆኑን የሚያመለክተው ምንድን ነው?

6 ሕሊና ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች ብቻ ናቸው? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን እንመልከት:- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ሕግ ባይኖራቸውም እንኳ እነሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል።” (ሮም 2:14, 15) የይሖዋን ሕጎች ፈጽሞ የማያውቁ ሰዎች እንኳ አንዳንድ ጊዜ በውስጣቸው ያለው ይህ ምሥክር መለኮታዊ መመሪያዎችን እንዲያከብሩ ይገፋፋቸዋል።

7. ሕሊና አንዳንድ ጊዜ ሊሳሳት የሚችለው ለምንድን ነው?

7 ይሁን እንጂ ሕሊና አንዳንድ ጊዜ ሊሳሳት ይችላል። ለምን? አንድ ኮምፓስ በብረት ከተሠራ ዕቃ አጠገብ ቢቀመጥ ወደ ሰሜን ሳይሆን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያመለክት ይችላል። በተጨማሪም ኮምፓሱ ይበልጥ ጥቅም የሚኖረው ከትክክለኛ ካርታ ጋር ተቀናጅቶ ከተሠራበት ነው። በተመሳሳይም ሕሊናችን ለልባችን የራስ ወዳድነት ምኞት ከተሸነፈ ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይመራናል። ከዚህም በላይ ሕሊናችን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው አስተማማኝ መመሪያ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ ካላደረግን አስፈላጊ በሆኑ በርካታ ጉዳዮች ረገድ ትክክል የሆነውን ነገር ከስህተቱ መለየት ሊያቅተን ይችላል። በእርግጥም ሕሊናችን በትክክል እንዲሠራ ከተፈለገ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ አመራር ማግኘት ያስፈልገናል። ጳውሎስ ‘ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ከእኔ ጋር ሆኖ ይመሠክርልኛል’ በማለት ጽፏል። (ሮም 9:1) ታዲያ ሕሊናችን ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲስማማ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሕሊናችንን በማሠልጠን ነው።

ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

8. (ሀ) ልባችን በሕሊናችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ሕሊናው የማይወቅሰው መሆኑ ብቻውን በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

8 በሕሊናህ ተመርተህ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ስሜታቸው የሚላቸውን ብቻ አዳምጠው አንድ ነገር ለማድረግ ይወስናሉ። ያሰቡትን ካደረጉ በኋላም “ሕሊናዬን የሚቆረቁረኝ ነገር የለም” ይላሉ። ይሁንና የአንድ ሰው የልብ ምኞት በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ሕሊናውን ሊያዛባበት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” ይላል። (ኤርምያስ 17:9) ስለዚህ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ልባችን የሚፈልገው ነገር መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ከሁሉ በፊት ይሖዋ አምላክን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። *

9. አምላካዊ ፍርሃት ምንድን ነው? አምላካዊ ፍርሃት ያለን መሆኑ በሕሊናችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

9 ውሳኔ የምናደርገው በሠለጠነ ሕሊናችን ተመርተን ከሆነ ውሳኔያችን የግል ፍላጎታችንን የምንከተል ሳይሆን ፈሪሃ አምላክ ያለን ሰዎች መሆናችንን ያሳያል። ለዚህ ተስማሚ የሆነ አንድ ምሳሌ ተመልከት። የአይሁድ ገዥ የነበረው ታማኙ ነህምያ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አንዳንድ ክፍያዎችንና ግብር የመጠየቅ መብት ነበረው። ሆኖም እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል። ለምን? የአምላክን ሕዝቦች በመጨቆን ይሖዋን እንዳያሳዝን ስለፈራ ነበር። “[አምላክን] ከመፍራቴ የተነሣ እንዲህ ያለውን አላደረግሁም” ብሏል። (ነህምያ 5:15) አምላካዊ ፍርሃት ማሳየታችን ማለትም የሰማዩን አባታችንን እንዳናሳዝን ከልብ መፍራታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለው አምላካዊ ፍርሃት ውሳኔ ማድረግ በሚኖርብን ጊዜ ከአምላክ ቃል መመሪያ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይገፋፋናል።

10, 11. የአልኮል መጠጦችን ከመጠጣት ጋር ግንኙነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ረገድ የአምላክን አመራር ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ለምሳሌ ከአልኮል መጠጦች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነጥቦችን ተመልከት። ብዙዎቻችን በግብዣ ላይ በምንገኝበት ጊዜ የአልኮል መጠጥ ልጠጣ ወይስ አልጠጣ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብናል። በመጀመሪያ ይህን በሚመለከት እውቀት ያስፈልገናል። ከዚህ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጦችን በልክ መጠጣትን አያወግዝም። እንዲያውም ይሖዋን የወይን ጠጅ ስለሰጠን ያወድሰዋል። (መዝሙር 104:14, 15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ መጠጣትንና መረን የለቀቀ ፈንጠዝያን ያወግዛል። (ሉቃስ 21:34፤ ሮም 13:13) ከዚህም በላይ ስካርን እንደ ዝሙትና ምንዝር ካሉት ከባድ ኃጢአቶች ጋር ይፈርጀዋል። *1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

11 አንድ ክርስቲያን ሕሊናውን የሚያሠለጥነውና የሚገራው እንደነዚህ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመማር ነው። በግብዣ ላይ ተገኝተን አልኮል መጠጣት ይኖርብኛል ወይስ አይኖርብኝም የሚል ጥያቄ ሲደቀንብን ራሳችንን እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች እንጠይቃለን:- ‘የተዘጋጀው ግብዣ እንዴት ያለ ነው? ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ መረን ወደለቀቀ ፈንጠዝያ ሊያመራ ይችላል? የእኔስ ዝንባሌ ምንድን ነው? የአልኮል መጠጥ ያምረኛል? የአልኮል መጠጥ ጥገኛ ነኝ? ሲጫጫነኝና ስሜቴ ሲለዋወጥ መፍትሔ አድርጌ የምወስደው አልኮል መጠጣትን ነው? ከልክ በላይ እንዳልጠጣ ራሴን የመግዛት ችሎታ አለኝ?’ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና እነዚህን በመሰሉት ጥያቄዎች ላይ በምናሰላስልበት ጊዜ ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ እንዲመራን መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 139:23, 24) ይህን ስናደርግ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ እንዲመራን ፈቃደኛ መሆናችንን እየገለጽን ነው። በተጨማሪም ሕሊናችን በመለኮታዊ ሥርዓቶች እንዲቃኝ እያሠለጠንነው ነው። ይሁንና ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ በጥንቃቄ ልናስብበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ።

የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት እንድትወስን ይረዳሃል

12, 13. የአንዱ ክርስቲያን ሕሊና ከሌላው ሊለይ የሚችልባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? እንዲህ ያለ ልዩነት ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 አንዳንድ ጊዜ የአንድ ክርስቲያን ሕሊና ከሌላው ክርስቲያን የተለየ መሆኑ ያስገርምህ ይሆናል። አንድ ሰው አንድ ዓይነት ድርጊት ወይም ልማድ ትክክል እንዳልሆነ ሲሰማው ሌላው ግን ምንም ችግር እንደሌለው አድርጎ ያስባል። አልኮል መጠጣትን እንደ ምሳሌ ብናነሳ፣ አንድ ክርስቲያን ከጥቂት ወዳጆቹ ጋር ሆኖ ምሽት ላይ ሲዝናና አንድ ብርጭቆ መጠጣት ያስደስተዋል፤ ሌላው ግን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማዋል። እንዲህ ያለ ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? ልዩነቶቹ በምናደርገው ውሳኔ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባል?

13 ሰዎች የተለያየ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚያነሳሷቸው ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። የሰዎች አስተዳደግ ይለያያል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ለበርካታ ዓመታት እየወደቁ እየተነሱ የታገሏቸው ድክመቶች ከአእምሯቸው አልወጣ ይሏቸዋል። (1 ነገሥት 8:38, 39) እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች በአልኮል መጠጥ ረገድ በጣም ጠንቃቆች መሆን እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ሊጠይቅህ ቤትህ ቢመጣና የአልኮል መጠጥ ብትጋብዘው ግብዣውን ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ታዲያ ግብዣህን ስላልተቀበለ ይከፋሃል? ካልጠጣህ ብለህ ትወተውተዋለህ? እንዲህ ማድረግ የለብህም። ግብዣውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት ብታውቅም ባታውቅም (በዚህ ወቅት ምክንያቱን መናገር አስፈላጊ ሆኖ ላይታየው ይችላል) ለእሱ ያለህ ፍቅር አሳቢነት እንድታሳየው ሊያነሳሳህ ይገባል።

14, 15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ሕሊናቸው የተለያየው በምን ጉዳይ ላይ ነው? ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምክር ሰጠ?

14 በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያኖች ሕሊና በጣም ይለያይ እንደነበረ ተገንዝቧል። በዚያ ዘመን አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጣዖታት የተሠዉ ምግቦችን መመገብ ይቀፋቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:25) ጳውሎስ ግን ለጣዖት ከተሠዉ በኋላ በሥጋ ገበያ ይሸጡ የነበሩትን ምግቦች መመገብ ሕሊናውን አልረበሸውም። ለጳውሎስ ጣዖታት በድን ናቸው፤ ይሖዋ የፈጠራቸውና የእሱ የሆኑት ምግቦች የጣዖታቱ ሊሆኑ አይችሉም። ቢሆንም ጳውሎስ ሌሎች እንደ እሱ ዓይነት አመለካከት እንደሌላቸው ያውቅ ነበር። አንዳንዶች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት በጣዖት አምልኮ ተተብትበው የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለእነዚህ ሰዎች ከጣዖት አምልኮ ጋር ንክኪ የነበረውን ማንኛውንም ነገር መጠቀም ይቀፋቸዋል። ታዲያ ጳውሎስ ሁኔታውን የፈታው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “እኛ ብርቱዎች የሆንን ብርቱ ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም። ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም።” (ሮም 15:1, 3) ጳውሎስ ልክ ክርስቶስ እንዳደረገው የወንድሞቻችንን ፍላጎት ከራሳችን እንድናስቀድም አሳስቦናል። ጳውሎስ ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ባነሳበት ሌላ ቦታ ላይ፣ ክርስቶስ ሕይወቱን የሠዋለትን አንድ ውድ የይሖዋ በግ ከሚያሰናክል ከነጭራሹ ሥጋ መብላት ቢቀርበት እንደሚሻል ተናግሯል።1 ቆሮንቶስ 8:13፤ 10:23, 24, 31-33

16. የማያፈናፍን ሕሊና ያላቸው ክርስቲያኖች ከእነሱ የተለየ ሕሊና ባላቸው ላይ መፍረድ የማይገባቸው ለምንድን ነው?

16 በሌላ በኩል ደግሞ፣ የማያፈናፍን ሕሊና ያላቸው ክርስቲያኖች ሌሎችን መተቸትም ሆነ ሁሉም ሰው የእነሱ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው መወትወት የለባቸውም። (ሮም 14:10) እንደ እውነቱ ከሆነ ሕሊናችንን ልንጠቀምበት የሚገባን በራሳችን ላይ ለመፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ ለመፍረድ አይደለም። ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ” ሲል የተናገረውን አስታውስ። (ማቴዎስ 7:1) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ በሕሊናው ተመርቶ ሊወስናቸው በሚገቡ የግል ጉዳዮች ላይ መከራከር የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችን የምንጎዳዳበትን ሳይሆን የምንተናነጽበትን ነገር በማድረግ ፍቅርና አንድነት ማስፈን የምንችልበትን መንገድ እንፈልጋለን።ሮም 14:19

ጥሩ ሕሊና ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

ጥሩ ሕሊና በሕይወት ጎዳና ላይ ሊመራን ብሎም ደስታና ውስጣዊ ሰላም ሊያስገኝልን ይችላል

17. በዘመናችን የብዙ ሰዎች ሕሊና ምን ሆኗል?

17 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:16) በይሖዋ አምላክ ዓይን ንጹሕ ሕሊና ይዞ መገኘት መቻል ትልቅ በረከት ነው። ይህ ዓይነቱ ሕሊና በዘመናችን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ካላቸው ሕሊና ፈጽሞ የተለየ ነው። ጳውሎስ የእነዚህ ሰዎች ሕሊና ‘በጋለ ብረት የተተኮሰ ያክል የደነዘዘ’ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) የጋለ ብረት ቆዳ ላይ ሲያርፍ ሥጋውን ስለሚያቃጥለው ጠባሳ ይተዋል እንዲሁም ቦታው ስሜት አልባ ይሆናል። ብዙዎች ሕሊናቸው የሞተ ያክል ደንዝዟል። በመሆኑም ማስጠንቀቂያ አይሰጣቸውም፣ አይቃወማቸውም፤ ወይም ምንም ዓይነት ጥፋት ቢሠሩ የሃፍረትና የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አያደርግም። በዘመናችን ብዙ ሰዎች ሕሊናቸው የሚያሰማውን የጥፋተኝነት ስሜት ለማዳመጥ አይፈልጉም።

18, 19. (ሀ) የበደለኝነት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል? (ለ) ሕሊናችን ለሠራነው ኃጢአት ንስሐ ከገባን በኋላም በጥፋተኝነት ስሜት የሚያሠቃየን ከሆነ ምን ልናደርግ እንችላለን?

18 እንደ እውነቱ ከሆነ የጥፋተኝነት ስሜት ሕሊናችን ስህተት እንደሠራን የሚናገርበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ኃጢአት የሠራ አንድ ሰው እንዲህ ባለው ስሜት ተገፋፍቶ ንስሐ ከገባ ኃጢአቱ በጣም ከባድ ቢሆንም እንኳ ይቅር ሊባልለት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት ሠርቶ የነበረ ቢሆንም በዋነኝነት ይቅርታ ያገኘው ከልቡ ንስሐ ስለገባ ነው። ክፉ ድርጊቱን አጥብቆ መጥላቱና ዳግመኛ የይሖዋን ሕጎች ላለመጣስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉ ይሖዋ “ቸርና ይቅር ባይ” መሆኑን በራሱ ሕይወት ለማየት አስችሎታል። (መዝሙር 51:1-19፤ 86:5) ይሁን እንጂ ንስሐ ከገባንና ይቅርታ ካገኘን በኋላም የጥፋተኝነትና የበደለኝነት ስሜት ቢያሠቃየንስ?

19 ኃጢአት የሠራ ሰው የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማው መሆኑ ጠቃሚ የሚሆንበት ወቅት ቢኖርም ግለሰቡ ንስሐ ከገባ ከረጅም ጊዜ በኋላም ሕሊናው በጸጸት ስሜት ከልክ በላይ ሊያሠቃየው ይችላል። እንደዚህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን አምላክ ስለ ራሳችን ከሚሰማን ከማንኛውም ዓይነት ስሜት እንደሚበልጥ በጥፋተኝነት ስሜት ለሚኮንነን ልባችን መንገር ይኖርብናል። ሌሎች እንዲያደርጉ እንደምናበረታታቸው ሁሉ እኛም ይሖዋ እንደሚወደንና ይቅርታ እንደሚያደርግልን አምነን መቀበል ያስፈልገናል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሕ ሕሊና በዚህ ዓለም እምብዛም የማይገኘውን ውስጣዊ ሰላም፣ መረጋጋትና ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል። በአንድ ወቅት ከባድ ኃጢአት ሠርተው የነበሩ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ እፎይታ አግኝተው በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሕሊና ይሖዋ አምላክን ማገልገል ችለዋል።1 ቆሮንቶስ 6:11

20, 21. (ሀ) ይህ መጽሐፍ ምን ለማድረግ እንዲረዳህ ታስቦ የተዘጋጀ ነው? (ለ) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ምን ዓይነት ነፃነት አለን? ሆኖም እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

20 ይህ መጽሐፍ በዚህ መከራ በበዛበት የሰይጣን ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ውስጥ ጥሩ ሕሊና ይዘህ እንድትኖርና በዚህም የሚገኘውን ደስታ እንድታጣጥም አንተን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እርግጥ ነው፣ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ልትሠራባቸውና ልታስብባቸው የሚገቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች እንዲሁም መሠረታዊ ሥርዓቶች በሙሉ ሊዳስስ እንደማይችል የታወቀ ነው። ከዚህም በላይ፣ ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ግልጽ የሆነ አድርግ አታድርግ የሚል መመሪያ አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ፣ የአምላክን ቃል በዕለት ተዕለት ሕይወትህ እንዴት ሥራ ላይ እንደምታውል በመማር ሕሊናህን ማሠልጠንና መግራት እንድትችል መርዳት ነው። ‘የክርስቶስ ሕግ’ ከሙሴ ሕግ በተለየ መልኩ ተከታዮቹ በተጻፉ ሕጎች ሳይሆን በሕሊናቸውና በመሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመሩ ያበረታታል። (ገላትያ 6:2) ስለሆነም ይሖዋ ለክርስቲያኖች በጣም አስደናቂ የሆነ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ቃሉ ይህን ነፃነት “ለክፋት መሸፈኛ” እንዳናደርገው ያሳስበናል። (1 ጴጥሮስ 2:16) ከዚህ ይልቅ ይህ ነፃነት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እንድናሳይ ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል።

21 ሕይወትህን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት መምራት እንደምትችል በጸሎት ስታስብበትና ውሳኔዎችህን በሥራ ላይ ስታውል፣ ይሖዋን ባወቅክበት ጊዜ የጀመርከውን ወሳኝ ሂደት ይኸውም ‘የማስተዋል ችሎታህን በማሠራት ማሠልጠንህን’ ትቀጥላለህ። (ዕብራውያን 5:14) በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናህ በእያንዳንዱ ቀን በረከት ያስገኝልሃል። መንገደኛውን እንደሚመራው ኮምፓስ ሕሊናህም የሰማዩን አባትህን የሚያስደስት ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል። ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ ለመኖር ከዚህ የተሻለ መንገድ ሊኖር አይችልም።

^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ ሕሊናችን የማይወቅሰን መሆኑ ብቻ ሁልጊዜ በቂ እንደማይሆን ይጠቁማል። ለምሳሌ ጳውሎስ “እኔ ሕሊናዬን የሚወቅሰኝ ምንም ነገር የለም። ሆኖም ይህ ጻድቅ መሆኔን ያረጋግጣል ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እኔን የሚመረምረኝ ይሖዋ ነው” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 4:4) ጳውሎስ በአንድ ወቅት ያደርግ እንደነበረው ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱ ሰዎች እንኳ ድርጊታቸውን አምላክ የሚቀበለው ስለሚመስላቸው ንጹሕ ሕሊና ሊኖራቸው ይችላል። ሕሊናችን በራሳችንም ሆነ በአምላክ ዓይን ንጹሕ መሆኑ አስፈላጊ ነው።የሐዋርያት ሥራ 23:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:3

^ አን.10 ብዙ ዶክተሮች የአልኮል ሱስ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ተቆጣጥረው በልክ መጠጣት አይችሉም እንደሚሉ ልብ ማለት ያስፈልጋል። እንደነዚህ ላሉት ሰዎች “ልካቸው” ፈጽሞ አለመጠጣት ነው።