ተመልሶ የተቋቋመ ገነት!
ምዕራፍ ሃያ ስምንት
ተመልሶ የተቋቋመ ገነት!
1. ብዙ ሃይማኖቶች በገነት ስለሚገኘው ሕይወት ተስፋ የሚናገሩት ለምንድን ነው?
“የሰው ልጅ ከሚጓጓላቸውና በእጅጉ ቀልቡን ከሚስቡት ነገሮች አንዱ የገነት ተስፋ ነው። ሰዎች ከሚጓጉላቸው ነገሮች ሁሉ ይበልጥ ኃይል ያለውና ብዙ ዘመናት ያስቆጠረው ይህ የገነት ናፍቆት ሳይሆን አይቀርም። ሃይማኖታዊ ሕይወታቸው በማንኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰዎች ገነትን እንደሚናፍቁ የሚያሳዩበት የተለያየ መንገድ አለ” ሲል ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጅን ዘግቧል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ሕይወት የጀመረው በገነት ማለትም ከሕመምና ሞት ነፃ በሆነ ውብ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንደሆነ ስለሚናገር እንዲህ ያለው ጠንካራ ፍላጎት ተፈጥሮአዊ ነገር ነው። (ዘፍጥረት 2:8-15) በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሃይማኖቶች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ወደፊት በገነት ውስጥ ስለሚገኘው ሕይወት መናገራቸው ምንም አያስገርምም።
2. ስለ ወደፊቱ ገነት እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምንችለው የት ነው?
2 እውነተኛውን የገነት ተስፋ በተመለከተ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ኢሳይያስ 51:3) ለምሳሌ ያህል በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የትንቢቱ ክፍል በረሃማ አካባቢዎች ገነት መሰል መናፈሻና ፍሬያማ ሜዳ እንደሚሆኑ ይገልጻል። ዓይነ ስውር የሆነው ብርሃኑ ይመለስለታል፣ ድዳው መናገር ይችላል፣ ደንቆሮውም ይሰማል። ተስፋ በተሰጠበት በዚህ ገነት ውስጥ ኃዘን ወይም ትካዜ አይኖርም። ይህም ሞት እንኳ ሳይቀር እንደሚወገድ የሚያሳይ ነው። እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው! እነዚህን ቃላት ልንረዳቸው የሚገባው እንዴት ነው? ዛሬ ላለነው ሰዎች የሚሆን ተስፋ ይዘዋልን? ይህንን የኢሳይያስ ምዕራፍ በመመርመር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።
ባድማ የሆነው ምድር ደስ ይለዋል
3. በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት ምድሪቱ ምን ዓይነት ለውጥ ታደርጋለች?
3 ተመልሶ ስለተቋቋመው ገነት ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረው ትንቢት እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፣ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።”—ኢሳይያስ 35:1, 2
4. የአይሁዳውያኑ የትውልድ አገር ምድረ በዳ የሆነችው መቼና እንዴት ነው?
4 ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በ732 ከዘአበ ገደማ ነው። ከዚህ በኋላ 125 ዓመታት ቆይቶ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በማጥፋት የይሁዳን ሕዝብ በምርኮ አግዘዋል። ትውልድ አገራቸው ሰው አልባና ባድማ ሆና ቀርታለች። (2 ነገሥት 25:8-11, 21-26) የእስራኤል ሕዝብ የታመነ ሆኖ ሳይገኝ ከቀረ በምርኮ እንደሚወሰድ ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው ማስጠንቀቂያ በዚህ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘዳግም 28:15, 36, 37፤ 1 ነገሥት 9:6-8) የዕብራውያኑ ብሔር በባዕድ አገር በምርኮ በቆየባቸው 70 ዓመታት ወቅት በመስኖ ለምተው የነበሩት ማሳዎቻቸውና የጓሮ አትክልቶቻቸው ተንከባካቢ አጥተው ምድረ በዳ ሆነው ነበር።—ኢሳይያስ 64:10፤ ኤርምያስ 4:23-27፤ 9:10-12
5. (ሀ) ምድሪቱ ወደ ገነታዊ ሁኔታ የተመለሰችው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎች ‘የይሖዋን ክብር የሚያዩት’ በምን መንገድ ነው?
5 ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት ምድሪቱ ለዘላለም ባድማ ሆና እንደማትቀር ይተነብያል። ገነታዊ ሁኔታ ይኖራታል። ‘የሊባኖስን ክብር’ እና ‘የቀርሜሎስን ግርማ’ ትላበሳለች። * እንዴት? አይሁዳውያኑ ከምርኮ ሲመለሱ መሬታቸውን በእህል መሸፈንና በመስኖ ማልማት ስለሚችሉ ምድራቸው ቀደም ሲል ወደነበራት ፍሬያማነት ትመለሳለች። ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። አይሁዳውያኑ እንዲህ ያለ ገነታዊ ሁኔታ ሊያገኙ የሚችሉት በእርሱ ፈቃድ፣ ድጋፍና በረከት ነው። አስገራሚ በሆነው የምድሪቱ ለውጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት የሚገነዘቡ ሰዎች ‘የይሖዋን ክብር የአምላካቸውንም ግርማ ያያሉ።’
6. የበለጠ ትርጉም ያለው የትኛው የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ እውን ሆኗል?
6 የሆነ ሆኖ ተመልሳ በምትቋቋመው በእስራኤል ምድር የኢሳይያስ ቃላት ከዚህ የበለጠ ትርጉም ያለው ፍጻሜም ይኖራቸዋል። እስራኤል በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ለብዙ ዓመታት እንደ በረሃ ደረቅ ሆና ቆይታለች። ግዞተኞቹ በባቢሎን በቆዩባቸው ጊዜያት ንጹሕ አምልኮ በእጅጉ ተዳፍኖ ነበር። ቤተ መቅደስ፣ መሠዊያ ወይም የተደራጀ የክህነት አገልግሎት አልነበረም። በየዕለቱ የሚቀርበው መሥዋዕት ቀርቶ ነበር። አሁን ግን ኢሳይያስ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ እንደሚመጣ በትንቢት ተናግሯል። እንደ ዘሩባቤል፣ ዕዝራና ነህምያ በመሳሰሉት ሰዎች መሪነት ከ12ቱም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን በመገንባት ይሖዋን በነፃነት ያመልካሉ። (ዕዝራ 2:1, 2) ይህ በእርግጥም መንፈሳዊ ገነት ነው!
በመንፈስ መቃጠል
7, 8. አይሁዳውያኑ ግዞተኞች አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነበር? የኢሳይያስ ቃላት ማበረታቻ የሚሰጡትስ እንዴት ነው?
7 በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ የሚገኙት ቃላት ደስታ የተንጸባረቀባቸው ናቸው። ነቢዩ ንስሐ የገባው ብሔር ብሩህ ጊዜ እንደሚጠብቀው እየተናገረ ነው። በእርግጥም ደግሞ የሚናገረው ጽኑ እምነትና አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ነው። ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ተመልሰው የሚቋቋሙበት ጊዜ ሲዳረስም ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ተመሳሳይ የሆነ ጽኑ እምነትና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት እንደሚከተለው ሲል ከወዲሁ አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “የደከሙትን እጆች አበርቱ፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው:- እነሆ፣ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፣ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፣ አትፍሩ በሉአቸው።”—ኢሳይያስ 35:3, 4
8 ረጅሙ የግዞት ዘመን ማብቂያ እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ይሆናል። 2 ዜና መዋዕል 36:22, 23) ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገውን አደገኛ ጉዞ ለመያያዝ በሺህ የሚቆጠሩ ዕብራውያን ቤተሰቦች መደራጀት ይጠበቅባቸው ነበር። እዚያ እንደደረሱ በቂ የመኖሪያ ቤቶችን መቀለስና ቤተ መቅደሱንና ከተማዋን ለመገንባቱ ግዙፍ ሥራ ራሳቸውን ማዘጋጀት ነበረባቸው። በባቢሎን ለነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ይህ ሁሉ የማይቻል መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እጃቸው የሚዝልበት ወይም የሚሰጉበት ጊዜ አይደለም። አይሁዳውያኑ እርስ በርሳቸው መበረታታትና በይሖዋ መታመን ነበረባቸው። ይሖዋ እንደሚድኑ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።
ይሖዋ ባቢሎንን ለመበቀል እንደ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ የይሖዋ አምልኮ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንደሚቋቋም ተናግሯል። (9. ተመላሾቹ አይሁዳውያን ምን ታላቅ ተስፋ ነበራቸው?
9 ከባቢሎን ምርኮ ነፃ የወጡት ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ እጅግ አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸው ስለነበር የሚደሰቱበት በቂ ኢሳይያስ 35:5, 6ሀ
ምክንያት ነበራቸው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ይተነብያል:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ [“በደስታ፣” NW] ይዘምራል።”—10, 11. ለተመላሾቹ አይሁዳውያን የኢሳይያስ ቃላት መንፈሳዊ ትርጉም ሊኖራቸው ይገባል የምንለው ለምንድን ነው? የሚያመለክቱትስ ምንድን ነው?
10 ይሖዋ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሁኔታ በአእምሮው ይዞ እንደነበር ግልጽ ነው። ቀደም ሲል ለፈጸሙት ክህደት 70 ዓመታት በግዞት እንዲቆዩ በማድረግ ቀጥቷቸዋል። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ለመቅጣት ብሎ ሕዝቡን ዓይነ ስውር፣ ደንቆሮ፣ አንካሳ ወይም ዲዳ አላደረጋቸውም። በመሆኑም የእስራኤልን ብሔር መልሶ ማቋቋም ከአካላዊ ችግሮቻቸው መፈወስን የሚጠይቅ አልነበረም። ይሖዋ የሚመልስላቸው አጥተውት የነበረውን መንፈሳዊ ጤና ነው።
11 ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን መንፈሳዊ ስሜቶቻቸውን በማግኘት ስለሚፈወሱ በመንፈሳዊ ሁኔታ የማየትና የመስማት እንዲሁም የመታዘዝና የይሖዋን ቃል የመናገር ችሎታቸውን መልሰው ያገኛሉ። ወደ ይሖዋ ተጠግተው መኖራቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በመልካም ምግባራቸውም አምላካቸውን በደስታ ‘መዝሙር’ ያወድሳሉ። ካሁን ቀደም “አንካሳ” የነበረው ሰው በጉጉትና በጋለ ስሜት በይሖዋ አምልኮ ይካፈላል። በምሳሌያዊ አነጋገር ‘እንደ ሚዳቋ ይዘልላሉ።’
ይሖዋ የሕዝቡን መንፈስ ያድሳል
12. ይሖዋ ምድሪቱን በውኃ የሚባርከው እስከ ምን ድረስ ነው?
12 ውኃ የሌለበት ገነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። በኤድን የነበረችው የመጀመሪያዋ ገነት በብዙ የውኃ ፈሳሾች የተከበበች ነበረች። (ዘፍጥረት 2:10-14) ለእስራኤላውያንም ተሰጥቷቸው የነበረው “ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም” ያሉበት ምድር ነው። (ዘዳግም 8:7) ስለሆነም ኢሳይያስ የሚከተለውን አስደሳች ተስፋ መስጠቱ ተገቢ ነው:- “በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።” (ኢሳይያስ 35:6ለ, 7) እስራኤላውያን እንደገና ምድሪቱን መንከባከብ ሲጀምሩ በአንድ ወቅት ቀበሮዎች ይፈነጩበት የነበረው ባድማ ቦታ ለምለም በሆኑና በተመቻቸው ዕፅዋት ይሸፈናል። ደረቅና አቧራማ የነበረው መሬት ደንገልና ሌሎችም በውኃ አቅራቢያ የሚበቅሉ ሸንበቆዎች የሚበቅሉበት “ረግረግ” ቦታ ይሆናል።—ኢዮብ 8:11
13. ተመልሶ የተቋቋመው ምድር የሚያገኘው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ውኃ ምንድን ነው?
13 ይሁን እንጂ የበለጠ ግምት የሚሰጠው ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን የሚያገኙት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ የእውነት ውኃ ነበር። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት እውቀት፣ ማበረታቻና ማጽናኛ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ በዕድሜ ጠና ያሉት የታመኑ ወንዶችና መሳፍንት ‘በጥም ቦታ እንዳለ የወንዝ ፈሳሽ’ ይሆናሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2) እውነተኛውን አምልኮ ያራምዱ የነበሩት እንደ ዕዝራ፣ ሐጌ፣ ኢያሱ፣ ነህምያ፣ ዘካርያስ እና ዘሩባቤል ያሉት ወንዶች የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን ለማግኘቱ ሕያው ምሥክሮች ናቸው።—ዕዝራ 5:1, 2፤ 7:6, 10፤ ነህምያ 12:47
“የተቀደሰ መንገድ”
14. ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገው ጉዞ ምን መልክ እንዳለው ግለጽ።
14 ይሁን እንጂ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ እንዲህ ያለውን ገነታዊ ሁኔታ ከማግኘታቸው በፊት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ረጅምና አደገኛ የሆነውን ጉዞ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ቀጥተኛውን መንገድ ተከትለው ከሄዱ ደረቅና ጠፍ መሬት የሆነውን 800 ኪሎ ሜትር አቋርጠው መሄድ ነበረባቸው። እምብዛም አስቸጋሪ ያልሆነውን መንገድ ከመረጡ ደግሞ 1,600 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም አቅጣጫ ቢሆን አስቸጋሪ የሆነውን የአየር ጠባይ እንዲሁም ቃል በቃል አውሬዎችንና አውሬ መሰል ሰዎችን ተጋፍጦ ለወራት መጓዝን የሚጠይቅ ነበር። ያም ሆኖ ግን በኢሳይያስ ትንቢት ላይ እምነት የነበራቸው ሰዎች ከልክ በላይ አልተጨነቁም። ለምን?
15, 16. (ሀ) የታመኑት አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው በሚያደርጉት ጉዞ ይሖዋ ምን ጥበቃ ያደርግላቸዋል? (ለ) ይሖዋ ለአይሁዳውያኑ አስተማማኝ ጎዳና የሚያዘጋጅላቸው በምን ሌላ መልኩ ነው?
15 በኢሳይያስ አማካኝነት ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፣ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አንበሳም አይኖርበትም፣ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፣ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት [“ዳግም የተዋጁት፣” NW] ግን በዚያ ይሄዳሉ።” (ኢሳይያስ 35:8, 9) ይሖዋ ሕዝቡን ታድጓል! ‘ዳግም የዋጃቸው’ ሰዎች በመሆናቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ በመንገድ ላይ ችግር እንደማይገጥማቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስድ ቃል በቃል የተነጠፈ፣ የተደለደለና ዳርዳሩን የታጠረ መንገድ አለ? የለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያደርግላቸው ጥበቃ ፍጹም አስተማማኝ ከመሆኑ የተነሣ እንዲህ ባለ አውራ ጎዳና ላይ የሚሄዱ ያህል ነው።—ከመዝሙር 91:1-16 ጋር አወዳድር።
16 አይሁዳውያኑ ከመንፈሳዊ አደጋዎችም ጥበቃ ያገኛሉ። ይህ ምሳሌያዊ ጎዳና “የተቀደሰ መንገድ” ነው። ቅዱስ ነገሮችን የሚያቃልሉ ዕዝራ 1:1-3
ወይም በመንፈሳዊ ንጹህ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ጎዳና ላይ ለመጓዝ ብቁ አይሆኑም። ተመልሳ በምትቋቋመው ምድር ውስጥ ቦታ አይኖራቸውም። ተቀባይነት የሚያገኙት በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የተነሳሱት ሰዎች ናቸው። ወደ ይሁዳና ኢየሩሳሌም የሚመለሱት በብሔራዊ የኩራት መንፈስ ተገፋፍተው ወይም የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ አይደለም። መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው አይሁዳውያን የሚመለሱበት ዋነኛ ዓላማ በምድሪቱ ንጹህ አምልኮ ለማቋቋም እንደሆነ ይገነዘባሉ።—የይሖዋ ሕዝብ ደስ ይለዋል
17. የኢሳይያስ ትንቢት በግዞት በቆዩባቸው ረጅም ዓመታት ለታመኑት አይሁዳውያን መጽናኛ የሆነው እንዴት ነው?
17 የኢሳይያስ ትንቢት 35ኛ ምዕራፍ የሚደመደመው በሚከተለው አስደሳች ሐሳብ ነው:- “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።” (ኢሳይያስ 35:10) በምርኮ ሳሉ በዚህ ትንቢት ይጽናኑና ተስፋ ያደርጉ የነበሩት አይሁዳውያን የትንቢቱ የተለያዩ ዝርዝር ሁኔታዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ይሆን እያሉ ሳያስቡ አይቀሩም። ብዙዎቹን የትንቢቱን ዘርፎች እንዳልተረዷቸው እሙን ነው። ያም ሆኖ ግን ‘ተመልሰው ወደ ጽዮን’ መምጣታቸው ፍጹም የማያሻማ ነበር።
18. በባቢሎን የነበረው ኃዘንና ትካዜ ተመልሳ በተቋቋመችው ምድር ውስጥ በሐሴትና በደስታ የተተካው በምን መንገድ ነው?
18 በመሆኑም በ537 ከዘአበ (ከ7,000 የሚበልጡትን ባሪያዎች ጨምሮ) 50,000 ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በመጣል አራት ወር የፈጀ ጉዞ በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። (ዕዝራ 2:64, 65) ከጥቂት ወራት በኋላ የይሖዋ መሠዊያ እንደገና የተገነባ ሲሆን ይህም ቤተ መቅደሱ እንደ አዲስ እንዲሠራ መሠረት የሚጥል እርምጃ ነበር። ሁለት መቶ ዓመታት ያስቆጠረውም የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። ብሔሩ በባቢሎን ያሳለፈው ኃዘንና ትካዜ ተመልሳ በተቋቋመችው ምድር ውስጥ በሐሴትና ደስታ ተለውጧል። ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል። ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ገነት ተመልሶ ተቋቁሟል!
የአዲስ ብሔር መወለድ
19. በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኢሳይያስ ትንቢት ያገኘው ፍጻሜ ውስን ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
19 እርግጥ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ያገኘው ፍጻሜ ውስን ነበር። ወደ ምድራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን በመንፈሳዊ መንገድ ያገኙት ገነታዊ ሁኔታ አልዘለቀም። ከጊዜ በኋላ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ብሔራዊ ስሜት ንጹሑን አምልኮ በክለዋል። በመንፈሳዊ ሁኔታ አይሁዳውያኑ ወደ ኃዘንና ትካዜ ተመልሰዋል። በመጨረሻም ይሖዋ እንደ ሕዝቡ አድርጎ መመልከቱን ተወ። (ማቴዎስ 21:43) እንደገና በማመፃቸው ደስታቸው ሳይዘልቅ ቀርቷል። ይህ ሁሉ ደግሞ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ሌላ ተጨማሪ ፍጻሜ እንዳለው የሚጠቁም ነው።
20. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ብቅ ያለው አዲስ እስራኤል የትኛው ነው?
20 ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሌላ እስራኤል ማለትም መንፈሳዊ እስራኤል ወደ ሕልውና መጥቷል። (ገላትያ 6:16) ኢየሱስ በምድር ባከናወነው አገልግሎት ወቅት ለዚህ አዲስ እስራኤል መወለድ ሁኔታውን አመቻችቷል። ንጹሕ አምልኮን መልሶ ያቋቋመ ሲሆን በትምህርቶቹ አማካኝነትም የእውነት ውኃ እንደገና መፍሰስ ጀምሯል። በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ የታመሙትን ፈውሷል። የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሲታወጅም የደስታ ዝማሬ ተሰምቷል። ሞቶ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ሰባት ሳምንታት ያህል ቆይቶ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን ማለትም በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ተዋጅተው የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችና የኢየሱስ ወንድሞች በመሆን በመንፈስ ቅዱስ ከተቀቡ አይሁዶችና ሌሎች ሰዎች የተውጣጣውን መንፈሳዊ እስራኤል አቋቁሟል።—ሥራ 2:1-4፤ ሮሜ 8:16, 17፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19
21. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር በተያያዘ መንገድ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት ክንውኖች የትኞቹ ናቸው?
21 ሐዋርያው ጳውሎስ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ለሆኑት ሰዎች ሲጽፍ የኢሳይያስ 35:3ን ቃላት በመጥቀስ “የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጒልበቶች አቅኑ” ብሏል። (ዕብራውያን 12:12) እንግዲያው በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተፈጻሚነት ነበራቸው። ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ የዕውራን ዓይን እንዲያይ የደንቆሮዎች ጆሮ እንዲሰማ አድርገዋል። ‘አንካሶች’ በእግራቸው እንዲሄዱና መናገር የተሳናቸው እንዲናገሩ አድርገዋል። (ማቴዎስ 9:32፤ 11:5፤ ሉቃስ 10:9) ከዚህ ይበልጥ ትርጉም ያለው ግን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ ወጥተው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመንፈሳዊ ገነት መካከል ለመገኘት መብቃታቸው ነው። (ኢሳይያስ 52:11፤ 2 ቆሮንቶስ 6:17) ከባቢሎን እንደተመለሱት አይሁዳውያን ሁሉ ከሐሰት ሃይማኖት ያመለጡት እነዚህ ሰዎችም አዎንታዊ አመለካከትና የድፍረት መንፈስ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነበር።—ሮሜ 12:11
22. ቅን ልብ ያላቸው እውነትን የሚፈልጉ ክርስቲያኖች በዘመናችን በባቢሎናዊ ምርኮ ተይዘው ነበር ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?
22 ስለ ዘመናችንስ ምን ለማለት ይቻላል? የኢሳይያስ ትንቢት ዛሬ ያለውን የክርስቲያን ጉባኤ የሚመለከት የበለጠ ሰፊ ተፈጻሚነት ይኖረዋልን? አዎን፣ ይኖረዋል። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የእውነተኛዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር በእጅጉ ሲመናመን የሐሰት ክርስትና ማለትም ‘እንክርዳዱ’ ተንሠራፍቶ ብቅ ብሏል። (ማቴዎስ 13:36-43፤ ሥራ 20:30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3) ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ከሌሎች በመለየት እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት ይጣጣሩ በነበረበት በ19ኛው መቶ ዘመን እንኳ የነበራቸው እውቀት ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ትምህርቶች የተበከለ ነበር። ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በ1914 ቢሾምም ብዙም ሳይቆይ የታየው ሁኔታ እውነትን የሚፈልጉትን የእነዚህን ቅን ሰዎች ተስፋ ያጨለመው ይመስል ነበር። በትንቢት በተነገረው መሠረት አሕዛብ ‘ከእነርሱ ጋር ተዋግተው ስላሸነፏቸው’ እነዚህ ቅን ክርስቲያኖች ምሥራቹን ለመስበክ ያደረጉት የነበረው ጥረት ተስተጓጉሏል። በባቢሎን ምርኮ የተያዙ ያህል ሆነው ነበር።—ራእይ 11:7, 8
23, 24. ከ1919 ጀምሮ የኢሳይያስ ቃላት በአምላክ ሕዝብ መካከል ፍጻሜያቸውን ያገኙት በምን መንገዶች ነው?
23 ይሁን እንጂ በ1919 ሁኔታዎች ተለወጡ። ይሖዋ ሕዝቡን ከምርኮ ነፃ አወጣቸው። ቀደም ሲል አምልኳቸውን በክለውባቸው የነበሩትን የሐሰት ትምህርቶች ማስወገድ ጀመሩ። ከዚህ የተነሳ ፈውስ አገኙ። ዛሬም ጭምር በምድር ዙሪያ እየተስፋፋ ባለው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ለመገኘት በቅተዋል። ለአምላክ ቅዱስ መንፈስ አሠራር ንቁ በመሆንና ዘወትር ወደ ይሖዋ ተጠግቶ መኖር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘብ በመንፈሳዊ ሁኔታ ዕውራን የነበሩት ማየት ችለዋል እንዲሁም ደንቆሮ የነበሩት መስማት ችለዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:6 NW፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5 NW) አፋቸው የተፈታው ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማወጅ ‘ዝማሬያቸውን’ ለማሰማት ይጓጓሉ። (ሮሜ 1:15 የ1980 ትርጉም) በመንፈሳዊ ደካማ ወይም “አንካሳ” የነበሩት ሰዎች አሁን ቀናተኞችና ደስተኞች ሆነዋል። በምሳሌያዊ አነጋገር ‘እንደ ሚዳቋ ይዘልላሉ።’
24 እነዚህ ተመልሰው የተቋቋሙት ክርስቲያኖች ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ ይሄዳሉ። ከታላቂቱ ባቢሎን ወደ መንፈሳዊው ገነት የሚወስደው ይህ “መንገድ” በመንፈሳዊ ንጹሕ ለሆኑት አምላኪዎች ሁሉ ክፍት ነው። (1 ጴጥሮስ 1:13-16) ይሖዋ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኞች ሊሆኑና ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ ለማጥፋት የሚሰነዝራቸው አውሬያዊ ጥቃቶች እንደማይሰምሩ ሙሉ ትምክህት ሊኖራቸው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ታዛዥ ያልሆነ እንዲሁም በቃኝን የማያውቅ አውሬ የሚያሳየውን ዓይነት ጠባይ የሚያንጸባርቅ ማንኛውም ሰው በአምላክ የተቀደሰ ጎዳና ላይ የሚሄዱትን ሰዎች እንዲበክል አይፈቀድለትም። (1 ቆሮንቶስ 5:11) በይሖዋ ጥበቃ ሥር ባለው በዚህ አካባቢ እርሱ የተቤዣቸው ማለትም ቅቡዓኑና “ሌሎች በጎች” ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ በማገልገል ይደሰታሉ።—ዮሐንስ 10:16
25. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ቃል በቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? አብራራ።
25 ስለ ወደፊቱስ ጊዜ ምን ለማለት ይቻላል? የኢሳይያስ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያከናወኗቸው ተዓምራዊ ፈውሶች ይሖዋ ወደፊት እንዲህ ያሉ ፈውሶችን በሰፊው ለማከናወን ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ እንዳለው አመልክተዋል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው መዝሙር በምድር ላይ ሰላማዊ ሁኔታ ስለሚሰፍንበት ዘላለማዊ ሕይወት ይናገራል። (መዝሙር 37:9, 11, 29) ኢየሱስ ሰዎች በገነት ውስጥ እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 23:43) ቃል በቃል ስለምትቋቋመው ገነት የሚገልጸው ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። በዚያ ወቅት ዓይነ ስውራን፣ ደንቆሮዎች፣ አንካሶችና መናገር የተሳናቸው ሰዎች ቃል በቃል ዘላቂ ፈውስ ያገኛሉ። ሐዘንና ትካዜ ከሰዎች ፊት ይሸሻሉ። ለዘላለም ዓለም ደስታና ሐሴት ይሰፍናል።—ራእይ 7:9, 16, 17፤ 21:3, 4
26. የኢሳይያስ ቃላት ዛሬ ያሉትን ክርስቲያኖች የሚያበረታቷቸው እንዴት ነው?
26 እውነተኛ ክርስቲያኖች ቃል በቃል ገነት በምድር ላይ ተመልሳ የምትቋቋምበትን ጊዜ የሚጠብቁ ቢሆንም ዛሬም የመንፈሳዊውን ገነት በረከቶች እያጣጣሙ ነው። የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችና መከራዎች አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ይጋፈጣሉ። በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት በመጣል ከሚከተለው ማሳሰቢያ ጋር በሚስማማ መንገድ እርስ በርሳቸው ይበረታታሉ። “የደከሙትን እጆች አበርቱ፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው:- . . . በርቱ፣ አትፍሩ በሉአቸው።” እንዲሁም “እነሆ፣ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፣ መጥቶም ያድናችኋል” በሚለው ትንቢታዊ ማረጋገጫ ላይ ሙሉ እምነት አላቸው።—ኢሳይያስ 35:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ቅዱሳን ጽሑፎች የጥንቷ ሊባኖስ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችና ትላልቅ የዝግባ ዛፎች የነበሩባት ከኤድን ገነት ጋር የምትነጻጸር ለም ምድር እንደነበረች ይገልጻሉ። (መዝሙር 29:5፤ 72:16፤ ሕዝቅኤል 28:11-13) ሳሮን በውኃ ፈሳሾቿና የተለያዩ ዛፎች ባሉት ደኗ የምትታወቅ ሲሆን ቀርሜሎስ ደግሞ በወይን ቦታዎቿና በአትክልት ስፍራዎቿ እንዲሁም አበባ የተነጠፈባቸው በሚመስሉት ኮረብታዎቿ ትታወቃለች።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 370 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 375 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በረሃማ ቦታዎች ሸንበቆና ደንገል የሚበቅልባቸው ውኃማ ቦታዎች ይሆናሉ
[በገጽ 378 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የታመሙትን ሰዎች ፈውሷል