ሕይወት የሚያድን ደም
ሕይወት የሚያድን ደም
እስካሁን የተመለከትናቸው መረጃዎች አንዳንድ ነጥቦችን ግልጽ አድርገውልናል። አንዳንድ ሰዎች ደም መውሰድ ሕይወት አድን ነው ብለው ቢያምኑም ብዙ አደጋዎችን ያስከትላል። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ደም በመውሰድ ምክንያት ሲሞቱ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ በክፉ ደዌ ተይዘው ለረጅም ጊዜ ይሠቃያሉ። ስለዚህ በሥጋዊ አመለካከት እንኳን ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕግ መታዘዝ ጥበብ ነው።—ሥራ 15:28, 29
በሽተኞች ደም አልባ ሕክምና እንዲሰጣቸው ቢጠይቁ ከብዙ አደጋ ይድናሉ። እንዲህ ያለውን ሕክምና በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ለመሞከር ፈቃደኛ የሆኑ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች በበርካታ
የሕክምና ሪፖርቶች እንደተረጋገጠው ውጤታማ የሆነና አደጋ የማያስከትል የሕክምና ዘዴ ሊያዳብሩ ችለዋል። አለምንም ደም ጥራት ያለው ሕክምና የሚሰጡ ሐኪሞች ይህን የሚፈጽሙት መሠረታዊ የሕክምና ሥርዓቶችን ጥሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሽተኛው የሚያገኘውን ጥቅምና ሊደርስበት የሚችለውን አደጋ አውቆ በአካሉና በሕይወቱ ላይ ምን እንደሚደረግ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ የማድረግ መብት እንዳለው በማወቃቸው ነው።ይህን የምንለው ጉዳዩ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም፤ በዚህ አመለካከት የሚስማሙት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ እናውቃለን። ሰዎች በሕሊናቸው፣ በሚያምኑበት ግብረ ገብና ስለ ሕክምና ባላቸው አመለካከት ይለያያሉ። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች፣ አንዳንድ ዶክተሮች ጭምር፣ አንድ በሽተኛ ከደም ለመራቅ ያደረገውን ውሳኔ መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። በኒው ዮርክ የሚገኙ አንድ ቀዶ ሐኪም እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “ከ15 ዓመት በፊት ገና ወጣት ሰልጣኝ ሐኪም ሳለሁ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሆነ በሽተኛ በአንጀት ቁስለት ምክንያት ደሙ ፈስሶ አልቆ ሲሞት ያየሁትን ፈጽሞ ልረሳ አልችልም። የበሽተኛው ፈቃድ ተከብሮለት ስለነበረ ምንም ደም አልተሰጠውም። ይሁን እንጂ ሐኪም እንደመሆኔ የተሰማኝ ብስጭት አሁንም ትዝ ይለኛል።”
ደም የዚህን ሰው ሕይወት ሊያድን እንደሚችል አምነው እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይህን ከጻፉ ከአንድ ዓመት በኋላ ዘ ብሪትሽ ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ (ጥቅምት 1986) ደም መስጠት ከመጀመሩ በፊት በጨጓራና አንጀት መድማት ምክንያት “የሚሞቱ ሰዎች 2.5 በመቶ” እንደነበሩ ሪፖርት አደረገ። ደም መስጠት የተለመደ ሕክምና ከሆነ በኋላ ግን ‘የሟቾቹ ቁጥር 10 በመቶ እንደሆነ አብዛኞቹ ጥናቶች ሪፖርት አድርገዋል።’ የሟቾች ቁጥር በአራት እጥፍ ያደገው ለምን ነበር? ተመራማሪዎቹ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል:- “ደም መስጠት ደም እንዲረጋ የሚያደርገውን የሰውነት እንቅስቃሴ ስለሚገታ ቁስሉ እንደገና መድማት ይጀምራል።” የሚደማ የአንጀት ቁስል የነበረው ይህ ምሥክር ደም አልወስድም ማለቱ የመዳን ዕድሉን ከፍ ሊያደርግለት የሚችል ነበር ማለት ነው።
እኚሁ ቀዶ ሐኪም በማከል እንዲህ ብለዋል:- “በርካታ ጊዜ በሕክምና ሞያ ማሳለፍና ብዙ በሽተኞችን ማከም የአንድን ሐኪም አመለካከት ይለውጣል። በአሁኑ ጊዜ በዙሪያችን ካለው አዲስ የሕክምና ቴክኖሎጂ ይልቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው በበሽተኛና በሐኪም መካከል ያለው መተማመንና የበሽተኛውን ፍላጎት የማክበር ግዴታ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። . . . ዛሬ በዚያ በሽተኛ ምክንያት የተሰማኝ ብስጭት ይህ በሽተኛ ላሳየው ጽኑ እምነት ባለኝ አድናቆትና አክብሮት ተተክቷል።” ሐኪሙ በመደምደሚያቸው ላይ ‘የማልስማማበትና መጥፎ ውጤት የሚያስከትል ቢሆን እንኳን የአንድን በሽተኛ ግላዊና ሃይማኖታዊ ፈቃድ ማክበር እንደሚኖርብኝ ያሳስበኛል’ ብለዋል።
አንተም ብዙ ሐኪሞች ‘በርካታ ዓመታት በሕክምና ዓለም ካሳለፉና ብዙ በሽተኞችን ካከሙ በኋላ’ የሚገነዘቡትን ነገር አስቀድመህ ተገንዝበህ ይሆናል። ሰዎች አሉ ከሚባሉት ሆስፒታሎች በሙሉ በሚበልጠው ሆስፒታል ከሁሉ የተሻለ ሕክምና ቢሰጣቸው እንኳን አንድ ደረጃ ላይ ሲደርሱ መሞታቸው አይቀርም። ደም ተሰጣቸውም አልተሰጣቸው ይሞታሉ። ሁላችንም እናረጃለን፣ የሕይወታችንም ፍጻሜ ፈጥኖ ይደርሳል። እንዲህ ስንል ያለውን እውነታ መቀበላችን እንጂ የዕድል አማኞች መሆናችን አይደለም። ሞት፣ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም ነገር ነው።
አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ የማያከብሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ጉዳት ይደርስባቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ በወሰዱት ደም ምክንያት ይሞታሉ። ድነው የወጡትም ቢሆኑ ያገኙት ሕይወት ዘላለማዊ አይደለም። ስለዚህ ደም መውሰድ ዘላቂ የሆነ ሕይወት አያስገኝም።
በሃይማኖታቸው ምክንያትም ሆነ ለጤናቸው በማሰብ ደም አንወስድም ብለው ሌላ አማራጭ ሕክምና ከሚወስዱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ይድናሉ። ይህን በማድረጋቸውም ሕይወታቸውን ለተወሰኑ ዓመታት ያስረዝሙ ይሆናል። ግን የሚያገኙት ሕይወት ዘላለማዊ አይደለም።
ሰዎች ሁሉ ፍጹማን አለመሆናቸውና ውሎ አድሮ ሟቾች መሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም ወደሚናገረው ማዕከላዊ እውነት ይመራናል። ይህን እውነት ከተረዳንና ከተገነዘብን ደም ሕይወትን፣ አዎን፣ የራሳችንን ሕይወት እንዴት ለዘላለም እንደሚያድን ለመመልከት እንችላለን።
ሕይወት አዳኝ የሆነው ብቸኛ ደም
ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ሰዎች ሁሉ ደም እንዳይበሉ አምላክ አዝዟል። ለምን? ደም ሕይወትን ስለሚወክል ነው። (ዘፍጥረት 9:3-6) ይህንንም ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ በይበልጥ አብራርቷል። ይህ ሕግ በጸደቀበት ጊዜ ለመሥዋዕት የታረዱ ከብቶች ደም በመሠዊያ ላይ ቀርቦ ነበር። (ዘጸአት 24:3-8) በዚህ ሕግ ውስጥ የተካተቱት ዝርዝር ትእዛዛት መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደላቸው መሆናቸውን የሚያመለክቱ ነበሩ። እስራኤላውያን የእንስሳት መሥዋዕቶች ማቅረባቸው የኃጢአት ሥርየት እንደሚያስፈልጋቸው አምነው መቀበላቸውን የሚያሳይ መሆኑን አምላክ ነግሯቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 4:4-7, 13-18, 22-30) አምላክ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ያዘዘው የጥንት አምላኪዎቹን እንጂ የዘመናችንን እውነተኛ አምላኪዎች እንዳልሆነ አይካድም። ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ላለነውም በጣም አስፈላጊ የሆነ ትርጉም አለው።
አምላክ ራሱ ከእነዚህ መሥዋዕቶች በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፣ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች:- ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፣ . . . አልሁ።”—የሥርየት ቀን በሚባለው የጥንት በዓል የእስራኤላውያን ሊቀ ካህናት የተሠዋውን እንስሳ ደም የአምላክ አምልኮ ማዕከል ወደ ሆነው የመቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ይወስድ ነበር። ይህን የሚያደርገው አምላክ የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር እንዲል መጠየቁን ለማመልከት ነበር። (ዘሌዋውያን 16:3-6, 11-16) እነዚህ መሥዋዕቶች ኃጢአትን ጨርሶ የማስተሰረይ ችሎታ ስላልነበራቸው በየዓመቱ መቅረብ ነበረባቸው። ቢሆንም ይህ የደም አጠቃቀም ትልቅ ትርጉም ያለው ምሳሌነት ነበረው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ትምህርት አምላክ በተወሰነው ጊዜ የአማኞችን ሁሉ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ የሚያስተሰርይ ፍጹም የሆነ አንድ መሥዋዕት የሚያስገኝ መሆኑን የሚገልጽ ነው። ይህም ቤዛ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትንቢት በተነገረለት መሲሕ ወይም ክርስቶስ ላይ የሚያተኩር ትምህርት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑ የሚፈጽመውን ሥራ በሥርየት ቀን ይደረግ ከነበረው ነገር ጋር ያወዳድራል:- “ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች . . . ድንኳን፣ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት [ሰማይ] በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፣ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።”—ዕብራውያን 9:11, 12, 22
ስለዚህ አምላክ ለደም ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ አመለካከት እንዲኖረን ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ ነው። አምላክ ፈጣሪ በመሆኑ የደም ብቸኛ አገልግሎት ምን ሊሆን እንደሚገባ ወስኗል። የጥንቶቹ እስራኤላውያን የእንስሳም ሆነ የሰው ደም ባለመውሰዳቸው በጤንነት ረገድ ያገኙት ጥቅም ሊኖር ቢችልም ዋናው አስፈላጊ ነጥብ ጤንነታቸው አልነበረም። (ኢሳይያስ 48:17) ሕይወታቸውን በደም አማካኝነት ከማቆየት ተግባር የሚርቁበት መሠረታዊ ምክንያት በጤናቸው ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ሳይሆን በአምላክ ዘንድ እርኩስ የሆነ ተግባር ስለሆነ ነበር። ከደም መራቅ የነበረባቸው ደም የተበከለ ነገር ስለሆነ ሳይሆን ሥርየት በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ስለነበረው ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ቤዛው አብራርቷል:- “በውድ ልጁም [በክርስቶስ] እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን። እርሱም የበደላችን ሥርየት።” (ኤፌሶን 1:7 ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ የሚገኘው የግሪክኛ ቃል “ደም” ተብሎ መተርጎሙ ትክክል ነው። ይሁን እንጂ በርካታ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ደም ከማለት ይልቅ “ሞት” ብለው በመተርጎም ስህተት ሠርተዋል። በዚህ ምክንያት አንባቢዎች ፈጣሪ ለደምና ደም ስላለው መሥዋዕታዊ ዋጋ ያለውን አመለካከት ሳይረዱ ሊቀሩ ይችላሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ክርስቶስ ፍጹም ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ እንደሞተና ሞቶ እንዳልቀረ በሚገልጸው ሐቅ ዙሪያ ያጠነጥናል። አምላክ በሥርየት ቀን እንዲደረግ ባዘዘው ሥርዓት ጥላነት መሠረት ኢየሱስ ወደ ሰማይ አርጎ ‘በእግዚአብሔር ፊት በሰማይ ስለ እኛ ቀረበ።’ በዚያም የመሥዋዕታዊ ደሙን ዋጋ አቀረበ። (ዕብራውያን 9:24) መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአምላክን ልጅ እንደ መርገጥ ከሚያስቆጥርና ደሙን እንደ ተራ ነገር እንደቆጠርን’ አድርጎ ሊያሳይ ከሚችል ተግባር እንድንርቅ አጠንክሮ ያዝዛል። ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድናና ሰላም ሊኖረን የሚችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—ዕብራውያን 10:29፤ ቆላስይስ 1:20
በደም አማካኝነት በተገኘ ሕይወት ተደሰት
አምላክ ስለ ደም የሚናገረውን በምንረዳበት ጊዜ ደም ላለው ሕይወት የማዳን ጠቀሜታ ከፍተኛ አክብሮት ይኖረናል። ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቶስ ‘የወደደን፣ ከኃጢአታችንም በደሙ ያጠበን’ እንደሆነ ይገልጻሉ። (ራእይ 1:5፤ ዮሐንስ 3:16) አዎን፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ለኃጢአታችን የተሟላና ዘላቂ የሆነ ሥርየት ልናገኝ እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቁጣው እንድናለን” ሲል ጽፏል። በደም አማካኝነት ዘለቄታ ያለው ሕይወት ሊገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።—ሮሜ 5:9፤ ዕብራውያን 9:14
ይሖዋ አምላክ ከብዙ ዘመናት በፊት በክርስቶስ አማካኝነት ‘የምድር ቤተሰቦች በሙሉ ራሳቸውን ሊባርኩ እንደሚችሉ’ ቃል ገብቷል። (ዘፍጥረት 22:18 NW) ይህ በረከት ምድርን ወደ ገነትነት መመለስን ይጨምራል። በዚያ ጊዜ አማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በበሽታ፣ በእርጅና ወይም በሞት አይቀሰፉም። በአሁኑ ጊዜ የሕክምና ባለሞያዎች ሊሰጡን ከሚችሉት ጊዜያዊ የሆነ የሕክምና እርዳታ በጣም የላቀ በረከት ያገኛሉ። “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፏልና” የሚል ታላቅ ተስፋ ተሰጥቶናል።—ራእይ 21:4
ስለዚህ አምላክ የሚፈልግብንን ነገሮች በሙሉ ልብ ብንል እንዴት ያለ ጥበብ ይሆናል! ይህም ስለ ደም የሰጠውን ትእዛዝ ማክበርንና ለሕክምና እንኳን በደም አለመጠቀምን ይጨምራል። እንዲህ ብናደርግ ለአሁኑ ሕይወት ብቻ አንኖርም። ከዚህ ይልቅ በሰብዓዊ ፍጽምና ወደፊት የምናገኘውን ዘላለማዊ ሕይወት ጨምሮ ለሕይወት ከፍተኛ ከበሬታ ያለን መሆኑን እናሳያለን።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ ሕዝቦች ሕይወታቸውን በደም አማካኝነት ለማቆየት ፈቃደኞች ያልሆኑት ጤናቸውን የሚጎዳ ድርጊት ስለሆነ ሳይሆን ርኩስ ነገር መፈጸም ስለሚሆንባቸው ነበር። በተጨማሪም ይህን ያደረጉት ደም የተበከለ ነገር ስለሆነ ሳይሆን ውድ ነገር ስለሆነ ነበር።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በውድ ልጁም [በኢየሱስ] እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን። እርሱም የበደላችን ሥርየት።”—ኤፌሶን 1:7
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕይወትን በኢየሱስ ደም አማካኝነት ማዳን በምድራዊ ገነት ለሚገኝ ጤናማና ዘላለማዊ ሕይወት መንገድ ይጠርጋል