በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደም:- መከበር ያለበት የማን ምርጫና ሕሊና ነው?

ደም:- መከበር ያለበት የማን ምርጫና ሕሊና ነው?

ተጨማሪ ክፍል

ደም:- መከበር ያለበት የማን ምርጫና ሕሊና ነው?

የሕክምና ዶክተር በሆኑት ጄ ሎወል ዲክሰን የተጠናቀረ

በኒው ዮርክ ስቴት ጆርናል ኦቭ ሜዲስን ፈቃድ በድጋሚ የታተመ፣ 1988፤ 88:​463-464,

ሐኪሞች እውቀታቸውን፣ ችሎታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን በሽታንና ሞትን ለመዋጋት የሠዉ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ በሽተኛ ይበጅሃል የተባለውን ሕክምና አልቀበልም ቢልስ? በሽተኛው የይሖዋ ምሥክር ከሆነና የሚሰጠው ሕክምና ደግሞ ሙሉ ደም፣ የታመቁ ቀይ የደም ህዋሳት፣ ፕላዝማ ወይም ፕሌትሌት ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም።

በደም አጠቃቀም ረገድ አንድ ሐኪም፣ በሽተኛው ደም አልባ የሆነ ሕክምና ብቻ እንዲሰጠው መምረጡ ሞያቸውን የሚያከብሩትን የሕክምና ባለሞያዎች እጀ ሰባራ ያደርጋቸዋል ብሎ ሊያስብ ይችላል። ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ በሽተኞችም ብዙ ጊዜ ዶክተሮቻቸው የሚሰ ጧቸውን ምክር ላለመከተል እንደሚመርጡ መዘንጋት አይገባም። አፐልባውም እና ሮት1 ባደረጉት ጥናት መሠረት በማስተማሪያ ሆስፒታሎች ከጠቅላላዎቹ በሽተኞች መካከል 19 በመቶ የሚሆኑት አንድን ዓይነት ሕክምና ወይም ዘዴ አንቀበልም ብለዋል፤ ከእነዚህ መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩት ሕክምናውን አለመቀበላቸው “በሕይወታቸው ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል” ሆኖ እያለም ነበር።

አብዛኞቹ በሽተኞች “የሚበጀውን የሚያውቀው ዶክተሩ ነው” የሚል አጠቃላይ አመለካከት ስለሚኖራቸው ምርጫቸውንና ፈቃዳቸውን ለሐኪማቸው ችሎታና ፈቃድ ያስገዛሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሐኪም ይህን እውነታ ሳይንሳዊ ሐቅ አድርጎ ቢቀበልና በሽተኞቹንም በዚህ እምነቱ ላይ ተመስርቶ ቢያክም በጣም አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ያገኘነው የሕክምና ሥልጠና፣ ፈቃድና ተሞክሮ በሕክምናው መድረክ በቀላሉ የማይገመት ሥልጣን እንዳጎናጸፈን የማይካድ ነው። ይሁን እንጂ በሽተኞቻችን ደግሞ የራሳቸው መብት አላቸው። ሁላችንም እንደምናውቀው ደግሞ ሕጉ (እንዲያውም ሕገ መንግሥቱ) የበለጠ ክብደት የሚሰጠው ለመብት ነው።

በአብዛኞቹ ሆስፒታሎች ግድግዳ ላይ “የበሽተኛ መብት” የሚል ተጽፎ ይታያል። ከእነዚህ መብቶች አንዱ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የመስማማት መብት ነው። ይህ መብት በመረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ የማድረግ መብት ቢባል ይበልጥ ትክክል ይሆናል። የተለያዩ ሕክምናዎች (ወይም ሕክምናውን አለመቀበል) ስለሚያስከትሉት ውጤት ከተነገረው በኋላ የትኛውን እንደሚቀበል መምረጥ የበሽተኛው ፋንታ ነው። በብሮንክስ፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ደም መስጠትንና የይሖዋ ምሥክሮችን አስመልክቶ የወጣ አንድ ረቂቅ ፖሊሲ እንዲህ ይላል:- “አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ በሽተኛ ውሳኔ የማድረግ አካላዊ ብቃት ካለው በጤንነቱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የሚያስከትልበት ቢሆን አንድን ዓይነት ሕክምና አልቀበልም የማለት መብት አለው።”2

ሐኪሞች የሞያ ግብረ ገብ ወይም የሕግ ተጠያቂነት ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ቢናገሩም ፍርድ ቤቶች ከዚህ ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ለበሽተኛው ምርጫ እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል።3 የኒው ዮርክ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚከተለው ብሏል:- “በሽተኛው የሚሰጠውን ሕክምና ለመምረጥ ያለው መብት ከማንኛውም ጉዳይ ይበልጥ ቅድሚያ ይሰጠዋል . . . [አንድ] ሐኪም፣ አካላዊና አእምሮአዊ ብቃት ያለው በሽተኛ ሊደረግለት የታሰበውን ሕክምና ያለመቀበል መብቱን ካከበረለት ሕጋዊ ወይም ሞያዊ ግዴታውን አልተወጣም ተብሎ ሊጠየቅ አይችልም።”4 በተጨማሪም ይኸው ፍርድ ቤት “የሕክምና ባለሞያዎች የግብረ ገብ አቋም በጣም አስፈላጊ መሆኑ ባይካድም እዚህ ላይ ከተረጋገጠው የግለሰቦች መሠረታዊ መብቶች የበለጠ ክብደት ሊሰጠው አይችልም። ቅድሚያ የሚሰጠው ለግለሰቦች ፍላጎትና ፈቃድ እንጂ ለሕክምና ተቋሞች ፍላጎት አይደለም” የሚል ብይን ሰጥቷል።5

አንድ ምሥክር ደም አልወስድም በሚልበት ጊዜ ሐኪሞች ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ እንዳልቻሉ ሆኖ ሊሰማቸውና ሕሊናቸው ሊወቅሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ምሥክሩ የጠየቀው ሞያቸውን የሚያከብሩ ዶክተሮች ሁኔታው የሚፈቅድላቸውን ማንኛውንም የተሻለ አማራጭ ሕክምና እንዲሰጡት ነው። እንደ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች አለርጂ እንደመሆን ወይም አንዳንድ ውድ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች እንዳለማግኘት ባሉ ምክንያቶች የተነሣ የምንሰጠውን ሕክምና ለመለወጥ የምንገደድባቸው ሁኔታዎች ብዙ ናቸው። ምሥክሮች በሆኑ በሽተኞች ረገድ ሐኪሞች የሚቀርብላቸው ጥያቄ ከበሽተኛው ምርጫና ሕሊና ማለትም በሽተኛው ከደም ለመራቅ ባደረገው ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ ውሳኔ ጋር የሚስማማ የሕክምና እርዳታ እንዲያደርጉ ነው።

በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለተደረጉ ከባድ ኦፕራስዮኖች የቀረቡ በርካታ ሪፖርቶች ብዙ ሐኪሞች ደም እንዳይሰጡ ከቀረበላቸው ጥያቄ ጋር በመስማማት ሕሊናቸውን ሳይጥሱ የተሳካ ሕክምና መስጠት እንደቻሉ አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል በ1981 ኩሊ 1, 026 የሚያክሉ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ውጤት ተከታትለው ነበር። ከእነዚህ መካከል 22 በመቶ የሚያክሉት የተደረጉት ለአቅመ አዳም ባልደረሱ ልጆች ላይ ነበር። “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተደረገው ቀዶ ሕክምና በሌሎች በሽተኞች ላይ ከታየው የበለጠ አደጋ” እንዳላስከተለ በጥናታቸው አረጋግጠዋል።6 ካምቡሪስ7 በምሥክሮቹ ላይ ስለተደረጉ ከባድ ኦፕራስዮኖች ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህ አፕራስዮኖች መካከል አንዳንዶቹ የተደረጉት “ደም አንወስድም በማለታቸው ምክንያት በአጣዳፊ ሊደረግላቸው የሚገባ ቀዶ ሕክምና” ተከልክሏቸው በነበሩ በሽተኞች ላይ ነበር። እንደሚከተለው ብለዋል:- “ለሁሉም በሽተኞች ከሕክምናው በፊት በኦፕራስዮን ክፍል ውስጥ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥም ሃይማኖታዊ እምነታቸው እንደሚከበርላቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር። በዚህ አሠራር ምክንያት ያጋጠመ አንድም አስቸጋሪ ሁኔታ አልነበረም።”

በሽተኛው የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ ጉዳዩ የምርጫ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ይቀርና የሕሊና ጉዳይ ይመጣል። ስለ ሐኪሙ ሕሊና ብቻ ማሰብ አይቻልም። የበሽተኛውስ ሕሊና? የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት የአምላክ ስጦታ እንደሆነና ይህም ሕይወት በደም እንደሚወከል ያምናሉ። ለክርስቲያኖች የተሰጠውን “ከደም ራቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያከብራሉ (ሥራ 15:​28, 29)።8 ስለዚህ አንድ ሐኪም የግለሰቦቹን መብት ተዳፍሮ እንዲህ ያለውን የበሽተኞች ጽኑ ሃይማኖታዊ እምነት ቢጥስ ውጤቱ በጣም አሳዛኝ ሊሆን ይችላል። ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ አንድን ሰው ሕሊናውን እንዲጥስ ከማስገደድ “የበለጠ የሚያሳምም በሰብዓዊ ክብር ላይ የሚፈጸም በደል አይኖርም። እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ነፍስ ከመግደል ይከፋል” ብለዋል።9

የይሖዋ ምሥክሮች ደም አንወስድም የሚሉት በሃይማኖታዊ ምክንያት ቢሆንም ደም መውሰድ ኤድስ፣ ነን ኤ ነን ቢ የተባለውን ሄፓታይተስ ሊያስከትል፣ የሰውነትን መድህን ሊያቃውስና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ችግሮችን ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ምክንያት ደም አንወስድም የሚሉ በሽተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። እነዚህ አደጋዎች ደም መውሰዳቸው ከሚያስገኝላቸው ጥቅም ጋር ሲነጻጸር ግምት ውስጥ የሚገባ መሆን አለመሆኑን ልንገልጽላቸው እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር እንደገለጸው “ሐኪሙ ይበጅሃል ያለውን ሕክምናና ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት መቀበል ወይም ሕክምናውን አልቀበልም ብሎ በሕይወቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መምረጥ ያለበት” በሽተኛው ነው። “ይህ የሕግ እውቅና ያገኘ የግለሰቦች የተፈጥሮ መብት ነው።”10

ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ማክሊን11 “ደም አልወስድም በማለቱ ደሙ ፈስሶ አልቆ የመሞት አደጋ የተደቀነበትን” ምሥክር በሽተኛ አስመልክተው ጥቅሙንና ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ስለማመዛዘን ሐሳብ ሰጥተዋል። አንድ የሕክምና ተማሪ እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል:- “የማመዛዘን ችሎታው ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነበር። የአንድ በሽተኛ ሃይማኖታዊ እምነት ሊሰጠው ከሚችለው ብቸኛ የሕክምና አማራጭ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ምን ያደርጋሉ?” ማክሊን ሲመልሱ እንዲህ አሉ:- “ይህ ሰው እንደተሳሳተ ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይችላል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ደም መውሰድ . . . ዘላለማዊ ኩነኔ ሊያስከትል [እንደሚችል] ያምናሉ። በሕክምና ሞያችን ጥቅሙንና ጉዳቱን በማመዛዘን ለመወሰን የሚያስችል ሥልጠና ተሰጥቶናል። ታዲያ ዘላለማዊ ኩነኔን በምድር ላይ ከሚኖረው ጥቂት ዘመን ጋር ስታወዳድር ሚዛኑ ወደ ሌላ አቅጣጫ ማጋደሉ አይቀርም።”11

ቨርቺሎ እና ዱፕሬይ12 በዚሁ የጆርናል እትም በወላጆቻቸው ሥር የሚተዳደሩ ልጆችን ደህንነት የመጠበቅን አስፈላጊነት ለማጉላት በፍርድ ቤት የታየውን የኦስቦርንን (In re Osborne) ጉዳይ ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ የተቋጨው እንዴት ነበር? ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት የደረሰበትንና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሁለት ልጆች ያሉትን አንድ አባት የሚመለከት ጉዳይ ነበር። ፍርድ ቤቱ ይህ ሰው ቢሞት ዘመዶቹ ለልጆቹ ቁሳዊና መንፈሳዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ወሰነ። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ከወሰናቸው ሌሎች ጉዳዮች13 በተለየ የበሽተኛው የሕክምና ምርጫ እንዳይከበር የሚያስገድድ ምክንያት አላገኘም። በሽተኛው ፈጽሞ የማይቀበለውን ሕክምና እንዲቀበል የሚያስገድድ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ማውጣት ሕጋዊ አልነበረም።14 በሽተኛው በተሰጠው አማራጭ ሕክምና ተሽሎት ቤተሰቦቹን መንከባከብ ቀጥሏል።

ሐኪሞች ከሚያጋጥሟቸው ወይም ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉት ሁኔታዎች አብዛኛዎቹ አለምንም ደም ሊታከሙ የሚችሉ አይደሉምን? የተማርናቸውና አጣርተን የምናውቃቸው ነገሮች የሕክምና ችግሮችን የሚመለከቱ ናቸው። ቢሆንም በሽተኞች የየግል እምነታቸውና ግባቸው ችላ ሊባልባቸው የማይገቡ ሰብዓዊ ፍጥረቶች ናቸው። በየግላቸው ቅድሚያ ሊሰጧቸው ስለሚገቡ ነገሮች፣ ስለ ሕሊናቸውና ስለ ሥነ ምግባራቸው ከማንም ሰው ይበልጥ የሚያውቁት እነርሱ ናቸው። ለሕይወታቸው ትርጉም የሚሰጧቸው ነገሮች ደግሞ እነዚህ ናቸው።

ምሥክሮች የሆኑ በሽተኞችን ሃይማኖታዊ ሕሊና ማክበር ችሎታችንን ሊፈታተንብን ይችላል። ይህን ፈተና በመጋፈጣችን ግን ሁላችንም እንደ ውድ ነገር ለምናያቸው መብቶችና ነጻነቶች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጥ መሆናችንን እናሳያለን። ጆን ስትዋርት ሚል የጻፉት የሚከተለው ሐሳብ ነጥቡን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል:- “እነዚህ መብቶችና ነጻነቶች ሙሉ በሙሉ የማይከበሩበት ማንኛውም ኀብረተሰብ ምንም ዓይነት መንግሥት ቢኖረው ነጻ ነው ሊባል አይችልም። . . . የየራሱን አካላዊ፣ አእምሮአዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነት የመንከባከብ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ግለሰብ ድርሻ ነው። የሰው ልጆች ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያገኙት እያንዳንዳቸው እንደመረጡት ሲኖሩ እንጂ፣ አንዱ ሌላው እንደመሰለው እንዲኖር ሲገደድ አይደለም።”15

[የማመሳከሪያ ጽሑፎች]

1. Appelbaum PS, Roth LH: Patients who refuse treatment in medical hospitals. JAMA 1983; 250:1296-1301.

2. Macklin R: The inner workings of an ethics committee: Latest battle over Jehovah’s Witnesses. Hastings Cent Rep 1988; 18(1):​15-20.

3. Bouvia v Superior Court, 179 Cal App 3d 1127, 225 Cal Rptr 297 (1986); In re Brown, 478 So 2d 1033 (Miss 1985).

4. In re Storar, 438 NYS 2d 266, 273, 420 NE 2d 64, 71 (NY 1981).

5. Rivers v Katz, 504 NYS 2d 74, 80 n 6, 495 NE 2d 337, 343 n 6 (NY 1986).

6. Dixon JL, Smalley MG: Jehovah’s Witnesses. The surgical/ethical challenge. JAMA 1981; 246:2471-2472.

7. Kambouris AA: Major abdominal operations on Jehovah’s Witnesses. Am Surg 1987; 53:​350-356.

8. Jehovah’s Witnesses and the Question of Blood. Brooklyn, NY, Watchtower Bible and Tract Society, 1977, pp 1-64.

9. Pope denounces Polish crackdown. NY Times, January 11, 1982, p A9.

10. Office of the General Counsel: Medicolegal Forms with Legal Analysis. Chicago, American Medical Association, 1973, p 24.

11. Kleiman D: Hospital philosopher confronts decisions of life. NY Times, January 23, 1984, pp B1, B3.

12. Vercillo AP, Duprey SV: Jehovah’s Witnesses and the transfusion of blood products. NY State J Med 1988; 88:​493-494.

13. Wons v Public Health Trust, 500 So 2d 679 (Fla Dist Ct App) (1987); Randolph v City of New York, 117 AD 2d 44, 501 NYS 2d 837 (1986); Taft v Taft, 383 Mass 331, 446 NE 2d 395 (1983).

14. In re Osborne, 294 A 2d 372 (DC Ct App 1972).

15. Mill JS: On liberty, in Adler MJ (ed): Great Books of the Western World. Chicago, Encyclopaedia Britannica, Inc, 1952, vol 43, p 273.