ክፍል 1
ትዳራችሁ አስደሳች እንዲሆን የአምላክን መመሪያ ተከተሉ
‘ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።’—ማቴዎስ 19:4
የመጀመሪያውን ትዳር የመሠረተው ይሖዋ a አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ የመጀመሪያዋን ሴት ከፈጠረ በኋላ ‘ወደ አዳም አመጣት።’ አዳምም በጣም በመደሰቱ “እንግዲህ እሷ የአጥንቶቼ አጥንት፣ የሥጋዬም ሥጋ ናት” ብሎ ተናገረ። (ዘፍጥረት 2:22, 23) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ባለትዳሮች ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል።
ትዳር ስትመሠርቱ የቤተሰብ ሕይወታችሁ ምንም እንከን የሌለበት እንደሚሆን ጠብቃችሁ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከልብ የሚዋደዱ ባልና ሚስትም እንኳ አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) እናንተም በዚህ ብሮሹር ውስጥ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሥራ ላይ ካዋላችሁ ትዳራችሁም ሆነ የቤተሰብ ሕይወታችሁ አስደሳች ይሆናል። b—መዝሙር 19:8-11
1 ይሖዋ የሰጣችሁን የሥራ ድርሻ ተቀበሉ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ባል የቤተሰብ ራስ ነው።—ኤፌሶን 5:23
ባል ከሆንክ፣ ይሖዋ ሚስትህን እንድትንከባከብ ይጠብቅብሃል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይሖዋ ሚስትህን የፈጠራት ለአንተ ረዳት ወይም ማሟያ እንድትሆን አድርጎ ሲሆን በአክብሮትና በፍቅር እንድትይዛት ይፈልጋል። (ዘፍጥረት 2:18) የእሷን ፍላጎት ከራስህ ለማስቀደም ፈቃደኛ እስከ መሆን ድረስ ሚስትህን በጥልቅ ልትወድዳት ይገባል።—ኤፌሶን 5:25-29
ሚስት ከሆንሽ፣ ይሖዋ ባልሽን በጥልቅ እንድታከብሪና የሥራ ድርሻውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት እንድታግዢው ይጠብቅብሻል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:33) ባልሽ የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች ደግፊ፤ እንዲሁም በሙሉ ልብሽ ተባበሪው። (ቆላስይስ 3:18) እንዲህ ስታደርጊ በባልሽ እንዲሁም በይሖዋ ፊት ውብ ትሆኛለሽ።—1 ጴጥሮስ 3:1-6
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
የተሻላችሁ ባሎች ወይም ሚስቶች ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባችሁ የትዳር ጓደኛችሁን ጠይቁ። ከዚያም በትኩረት አዳምጡ፤ እንዲሁም ራሳችሁን ለማሻሻል፣ የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ
-
ታጋሾች ሁኑ። አንዳችሁ ሌላውን ማስደሰት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ሁለታችሁም ብትሆኑ ጊዜ ያስፈልጋችኋል
2 አንዳችሁ ለሌላው ስሜት ከልብ እንደምታስቡ አሳዩ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ለትዳር ጓደኛችሁ ፍላጎት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋችኋል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ “ለሰው ሁሉ ገር” እንዲሆኑ የሚፈልግ መሆኑን በማስታወስ የትዳር ጓደኛችሁን እንደ ውድ ንብረት አድርጋችሁ ተመልከቱ። (2 ጢሞቴዎስ 2:24) “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።” በመሆኑም የምትጠቀሙባቸውን ቃላት በጥንቃቄ ምረጡ። (ምሳሌ 12:18) አነጋገራችሁ ደግነትና ፍቅር የተላበሰ እንዲሆን የይሖዋ መንፈስ ይረዳችኋል።—ገላትያ 5:22, 23፤ ቆላስይስ 4:6
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ከበድ ባሉ ጉዳዮች ላይ መወያየት ከመጀመራችሁ በፊት ይሖዋ ተረጋግታችሁና አእምሯችሁን ክፍት አድርጋችሁ ለማዳመጥ እንዲረዳችሁ ጸልዩ
-
ምን እንደምትናገሩና እንዴት ብትናገሩት እንደሚሻል ቆም ብላችሁ አስቡ
3 አንድ እንደሆናችሁ አስታውሱ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ስታገባ ከትዳር ጓደኛህ ጋር “አንድ ሥጋ” ትሆናለህ። (ማቴዎስ 19:5) ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሁለት ግለሰቦች ስለሆናችሁ የተለያየ አመለካከት ሊኖራችሁ ይችላል። ስለዚህ አንድ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። (ፊልጵስዩስ 2:2) ውሳኔዎች በምታደርጉበት ጊዜ አንድ መሆናችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መመካከር ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል” ይላል። (ምሳሌ 20:18) አንድ ላይ ሆናችሁ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በምታደርጉበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመሩ።—ምሳሌ 8:32, 33
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
ለትዳር ጓደኛችሁ አንዳንድ ሐሳቦችን ወይም አመለካከታችሁን ብቻ ሳይሆን ስሜታችሁንም ግለጹ
-
አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከመግባታችሁ በፊት የትዳር ጓደኛችሁን አማክሩ