መሳፍንት 12:1-15

  • ከኤፍሬማውያን ጋር የተፈጠረ ግጭት (1-7)

    • “እስቲ ሺቦሌት በል” (6)

  • መሳፍንቱ ኢብጻን፣ ኤሎን እና አብዶን (8-15)

12  ከዚያም የኤፍሬም ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ወደ ጻፎን* በመሻገር ዮፍታሔን “አሞናውያንን ለመውጋት ስትሻገር አብረንህ እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምንድን ነው?+ ቤትህን በላይህ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን” አሉት። 2  ዮፍታሔ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እኔና ሕዝቤ ከአሞናውያን ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ተጋጭተን ነበር። እኔም እንድትረዱኝ ጠርቻችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ከእጃቸው አላዳናችሁኝም። 3  እኔም እንደማታድኑኝ ስመለከት ሕይወቴን አደጋ ላይ ጥዬ* በአሞናውያን ላይ ለመዝመት ወሰንኩ፤+ ይሖዋም እነሱን በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው። ታዲያ ዛሬ ልትወጉኝ የወጣችሁት ለምንድን ነው?” 4  ከዚያም ዮፍታሔ የጊልያድን+ ሰዎች ሁሉ አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋር ተዋጋ፤ የጊልያድም ሰዎች ኤፍሬማውያንን ድል አደረጓቸው፤ ኤፍሬማውያን የጊልያድን ሰዎች “በኤፍሬምና በምናሴ የምትኖሩ እናንተ የጊልያድ ሰዎች፣ እናንተ እኮ ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ያመለጣችሁ ስደተኞች ናችሁ” ይሏቸው ነበር። 5  ጊልያዳውያንም ከኤፍሬማውያን ፊት ለፊት የሚገኘውን የዮርዳኖስን+ መልካ* ተቆጣጠሩ፤ የኤፍሬምም ሰዎች ለማምለጥ በሚሞክሩበት ጊዜ “እንድሻገር ፍቀዱልኝ” ይላሉ፤ በዚህ ጊዜ የጊልያድ ሰዎች እያንዳንዱን ሰው “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ እሱም “አይ፣ አይደለሁም” ብሎ ሲመልስላቸው 6  “እስቲ ሺቦሌት በል” ይሉታል። እሱ ግን ቃሉን በትክክል መጥራት ስለማይችል “ሲቦሌት” ይላል። እነሱም ይዘው እዚያው ዮርዳኖስ መልካ ላይ ይገድሉታል። በመሆኑም በዚያን ጊዜ 42,000 ኤፍሬማውያን አለቁ። 7  ዮፍታሔም በእስራኤል ውስጥ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ፤ ከዚያም ጊልያዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ በጊልያድ በምትገኘው ከተማውም ተቀበረ። 8  ከእሱም በኋላ የቤተልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+ 9  ኢብጻን 30 ወንዶችና 30 ሴቶች ልጆች ነበሩት። እሱም ሴቶች ልጆቹን ከጎሳው ውጭ የሆኑ ሰዎችን እንዲያገቡ ላካቸው፤ እንዲሁም ከወንዶች ልጆቹ ጋር እንዲጋቡ ከጎሳው ውጭ የሆኑ 30 ሴቶችን አስመጣ። በእስራኤልም ውስጥ ለሰባት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 10  ከዚያም ኢብጻን ሞተ፤ በቤተልሔምም ተቀበረ። 11  ከእሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። እሱም በእስራኤል ውስጥ ለአሥር ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 12  ከዚያም ዛብሎናዊው ኤሎን ሞተ፤ በዛብሎን ምድር በአይሎንም ተቀበረ። 13  ከእሱም በኋላ የጲራቶናዊው የሂሌል ልጅ አብዶን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 14  እሱም በ70 አህዮች የሚጋልቡ 40 ወንዶች ልጆችና 30 የልጅ ልጆች ነበሩት። በእስራኤልም ውስጥ ለስምንት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 15  ከዚያም የጲራቶናዊው የሂሌል ልጅ አብዶን ሞተ፤ በአማሌቃውያን+ ተራራ በኤፍሬም ምድር በምትገኘው በጲራቶንም ተቀበረ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ወደ ሰሜን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴን በእጄ ይዤ።”
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።