መሳፍንት 20:1-48

  • እስራኤላውያን ከቢንያማውያን ጋር ተዋጉ (1-48)

20  በመሆኑም ከዳን+ አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እንዲሁም በጊልያድ ምድር+ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ አንድ ላይ* በመውጣት በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት ተሰበሰቡ። 2  የሕዝቡና የእስራኤል ነገዶች አለቆች ሁሉ በእውነተኛው አምላክ ሕዝብ ጉባኤ መካከል ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ፤ ሰይፍ የታጠቁት እግረኛ ወታደሮች 400,000 ነበሩ።+ 3  ቢንያማውያንም የእስራኤል ሰዎች ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች “ይህ ክፉ ነገር እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ እስቲ ንገሩን?”+ አሏቸው። 4  በዚህ ጊዜ የተገደለችው ሴት ባል የሆነው ሌዋዊ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔና ቁባቴ የቢንያም በሆነችው በጊብዓ ለማደር ወደዚያ መጥተን ነበር።+ 5  የጊብዓ ነዋሪዎችም* በእኔ ላይ ተነሱብኝ፤ በሌሊት መጥተውም ቤቱን ከበቡ። ለመግደል ያሰቡት እኔን ነበር፤ ሆኖም ቁባቴን ደፈሯት፤ እሷም ሞተች።+ 6  እኔም የቁባቴን አስከሬን ወስጄ ቆራረጥኩት፤ ከዚያም ወደ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ላክሁት፤+ ምክንያቱም እነሱ በእስራኤል ውስጥ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመዋል። 7  እንግዲህ እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያላችሁን ሐሳብና አስተያየት ስጡ።”+ 8  ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ አንድ ላይ* ሆኖ በመነሳት እንዲህ አለ፦ “ከመካከላችን ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም ወይም ወደ ቤቱ አይመለስም። 9  እንግዲህ በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፦ ዕጣ እናወጣና እንዘምትባታለን።+ 10  የቢንያም ግዛት የሆነችው የጊብዓ ነዋሪዎች በእስራኤል ውስጥ በፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊት የተነሳ በእሷ ላይ ዘምቶ ተገቢውን እርምጃ ለሚወስደው ሠራዊት ስንቅ እንዲያዘጋጁ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ከ100ው 10፣ ከ1,000ው 100፣ ከ10,000ው ደግሞ 1,000 ሰዎችን እንወስዳለን።” 11  በዚህ መንገድ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ግንባር በመፍጠር በከተማዋ ላይ በአንድነት* ወጡ። 12  ከዚያም የእስራኤል ነገዶች ወደ ቢንያም ነገድ መሪዎች ሁሉ እንዲህ በማለት መልእክተኞችን ላኩ፦ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ዘግናኝ ድርጊት ምንድን ነው? 13  በሉ አሁን በጊብዓ ያሉትን እነዚያን ጋጠወጥ ሰዎች+ እንድንገድላቸውና ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል እንድናስወግድ ሰዎቹን አሳልፋችሁ ስጡን።”+ ቢንያማውያን ግን ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም። 14  ከዚያም ቢንያማውያን ከእስራኤል ሰዎች ጋር ለመዋጋት ከየከተሞቹ ወጥተው በጊብዓ ተሰባሰቡ። 15  ከተመረጡት 700 የጊብዓ ሰዎች በተጨማሪ በዚያ ቀን ሰይፍ የታጠቁ 26,000 ቢንያማውያን ከየከተሞቻቸው ተሰባሰቡ። 16  በሠራዊቱም መካከል የተመረጡ 700 ግራኞች ነበሩ። እያንዳንዳቸውም ድንጋይ ወንጭፈው ፀጉር እንኳ የማይስቱ ነበሩ። 17  የእስራኤል ሰዎች ደግሞ ቢንያምን ሳይጨምር ሰይፍ የታጠቁ 400,000 ሰዎች አሰባሰቡ፤+ እያንዳንዳቸውም ልምድ ያላቸው ተዋጊዎች ነበሩ። 18  እነሱም አምላክን ለመጠየቅ ተነስተው ወደ ቤቴል ወጡ።+ ከዚያም የእስራኤል ሰዎች “ከቢንያማውያን ጋር ለሚደረገው ውጊያ ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። ይሖዋም “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ሲል መለሰ። 19  ከዚያም እስራኤላውያን በማለዳ ተነስተው ጊብዓን ከበቡ። 20  የእስራኤል ሰዎችም ቢንያምን ለመውጋት ወጡ፤ የእስራኤል ሰዎች እነሱን ጊብዓ ላይ ለመውጋት የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ። 21  ቢንያማውያንም ከጊብዓ በመውጣት በዚያን ቀን ከእስራኤላውያን መካከል 22,000 ሰዎችን ገደሉ። 22  ሆኖም የእስራኤላውያን ሠራዊት ልክ እንደ መጀመሪያው ቀን የጦርነት አሰላለፍ ይዞ አሁንም እዚያው ቦታ ላይ በድፍረት ቆመ። 23  ከዚያም እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በይሖዋ ፊት አለቀሱ፤ ይሖዋንም “ከወንድሞቻችን ከቢንያም ሰዎች ጋር ለመዋጋት እንደገና እንውጣ?” በማለት ጠየቁ።+ ይሖዋም “አዎ፣ በእነሱ ላይ ውጡ” አላቸው። 24  በመሆኑም እስራኤላውያን በሁለተኛው ቀን ወደ ቢንያማውያን ተጠጉ። 25  ቢንያማውያንም በሁለተኛው ቀን እነሱን ለመግጠም ከጊብዓ ወጡ፤ ከእስራኤላውያንም መካከል ሰይፍ የታጠቁ ተጨማሪ 18,000 ሰዎችን ገደሉ።+ 26  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ወደ ቤቴል ወጡ። በዚያም እያለቀሱ በይሖዋ ፊት ተቀመጡ፤+ እንዲሁም በዚያ ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤+ በይሖዋም ፊት የሚቃጠሉ መባዎችንና+ የኅብረት መባዎችን+ አቀረቡ። 27  ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ይሖዋን ጠየቁ፤+ ምክንያቱም በዚያ ዘመን የእውነተኛው አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት የሚገኘው እዚያ ነበር። 28  የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስም+ በዚያ ዘመን በታቦቱ ፊት ያገለግል* ነበር። እነሱም “ወንድሞቻችንን የቢንያምን ሰዎች ለመውጋት እንደገና እንውጣ ወይስ እንቅር?” ሲሉ ጠየቁ።+ ይሖዋም “በነገው ዕለት እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ስለምሰጣችሁ ውጡ” በማለት መለሰላቸው። 29  ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ አድፍጠው የሚጠባበቁ+ ሰዎች አስቀመጡ። 30  በሦስተኛውም ቀን እስራኤላውያን ቢንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ።+ 31  ቢንያማውያንም ሠራዊቱን ለመግጠም በወጡ ጊዜ ከከተማዋ ራቁ።+ ከዚያም እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ በአውራ ጎዳናዎቹ ማለትም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስዱት አውራ ጎዳናዎች ላይ በነበሩት ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተወሰኑ ሰዎችን ገደሉ፤ ወደ 30 ገደማ የሚሆኑ የእስራኤል ሰዎችን በሜዳው ላይ ገደሉ።+ 32  በመሆኑም ቢንያማውያን “እንደ በፊቱ ሁሉ አሁንም ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ።+ እስራኤላውያን ግን “እየሸሸን ከከተማው ርቀው ወደ አውራ ጎዳናዎቹ እንዲመጡ እናድርጋቸው” አሉ። 33  ስለሆነም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ከነበሩበት ተነስተው በመሄድ በዓልታማር ላይ የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ፤ በዚህ ጊዜ አድፍጠው የነበሩት እስራኤላውያን ተደብቀውበት ከነበረው ከጊብዓ አቅራቢያ ተንደርድረው ወጡ። 34  በዚህ መንገድ ከመላው እስራኤል የተውጣጡ 10,000 የተመረጡ ወንዶች ወደ ጊብዓ ፊት ለፊት መጡ፤ ከባድ ውጊያም ተካሄደ። ሆኖም ቢንያማውያን ጥፋት እያንዣበበባቸው መሆኑን አላወቁም ነበር። 35  ይሖዋ ቢንያምን በእስራኤል ፊት ድል አደረገው፤+ በዚያም ቀን እስራኤላውያን ሰይፍ የታጠቁ 25,100 ቢንያማውያንን ገደሉ።+ 36  ይሁንና ቢንያማውያን የእስራኤል ሰዎች ከእነሱ ሲያፈገፍጉ ድል እያደረጓቸው ያሉ መስሏቸው ነበር፤+ ሆኖም እስራኤላውያን ያፈገፈጉት በጊብዓ ላይ ባደፈጡት ሰዎች ተማምነው ነበር።+ 37  አድፍጠው የነበሩትም ሰዎች በፍጥነት እየተንደረደሩ ወደ ጊብዓ ሄዱ። ከዚያም በየቦታው ተሰራጭተው ከተማዋን በሙሉ በሰይፍ መቱ። 38  የእስራኤልም ሰዎች አድፍጠው በከተማዋ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩት ተዋጊዎች ከከተማዋ ጭስ እንዲወጣ በማድረግ ምልክት እንዲያሳዩአቸው ተስማምተው ነበር። 39  እስራኤላውያንም ከውጊያው ሲያፈገፍጉ የቢንያም ሰዎች ጥቃት በመሰንዘር ከእስራኤላውያን መካከል ወደ 30 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ገደሉ፤+ እነሱም “ልክ እንደ መጀመሪያው ውጊያ ሁሉ አሁንም ድል እያደረግናቸው መሆኑ ግልጽ ነው” ይሉ ነበር።+ 40  ሆኖም ምልክት ሆኖ የሚያገለግለው ጭስ እንደ ዓምድ በመሆን ከከተማዋ ይወጣ ጀመር። የቢንያምም ሰዎች ዞር ብለው ሲመለከቱ የመላ ከተማዋ ነበልባል ወደ ሰማይ ሲንቀለቀል አዩ። 41  ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ የቢንያምም ሰዎች መጥፊያቸው እንደቀረበ ስላወቁ ተደናገጡ። 42  በመሆኑም ከእስራኤል ሰዎች በመሸሽ ወደ ምድረ በዳው ሄዱ፤ ሆኖም ከከተሞቹ የወጡትም ሰዎች በእነሱ ላይ ጥቃት መሰንዘር ስለጀመሩ ከውጊያው ማምለጥ አልቻሉም። 43  እነሱም ቢንያማውያኑን ከበቧቸው፤ ያለእረፍትም አሳደዷቸው። ከዚያም ጊብዓ ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ባለው ስፍራ ደመሰሷቸው። 44  በመጨረሻም 18,000 የቢንያም ሰዎች ረገፉ፤ ሁሉም ኃያል ተዋጊዎች ነበሩ።+ 45  የቢንያም ሰዎችም ዞረው በምድረ በዳው ወደሚገኘው የሪሞን ዓለት+ ሸሹ፤ እስራኤላውያንም 5,000 ሰዎችን በአውራ ጎዳናዎቹ ላይ ገደሉባቸው፤* እስከ ጊድኦምም ድረስ አሳደዷቸው፤ በመሆኑም ተጨማሪ 2,000 ሰዎችን ገደሉ። 46  በዚያ ቀን የተገደሉት ሰይፍ የታጠቁ ቢንያማውያን ቁጥር በአጠቃላይ 25,000 ደረሰ፤+ ሁሉም ኃያል ተዋጊዎች ነበሩ። 47  ሆኖም 600 ሰዎች በምድረ በዳው ወደሚገኘው የሪሞን ዓለት ሸሹ፤ በሪሞን ዓለትም ለአራት ወር ተቀመጡ። 48  የእስራኤልም ሰዎች በቢንያማውያን ላይ ተመልሰው በመምጣት ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በከተማዋ ውስጥ የቀረውን ሁሉ በሰይፍ መቱ። በተጨማሪም በመንገዳቸው ላይ ያገኟቸውን ከተሞች በሙሉ በእሳት አቃጠሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው ሆነው።”
“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው።”
ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው ሆነው።”
ቃል በቃል “ይቆም።”
ቃል በቃል “ቃረሙ።”