መዝሙር 73:1-28
የአሳፍ+ ማህሌት።
73 አምላክ ለእስራኤል፣ ልባቸው ንጹሕ ለሆነ ሁሉ በእርግጥ ጥሩ ነው።+
2 እኔ ግን እግሮቼ ከመንገድ ሊወጡ ተቃርበው ነበር፤አዳልጦኝ ልወድቅ ምንም አልቀረኝም።+
3 ክፉ ሰዎች ያላቸውን ሰላም በተመለከትኩ ጊዜ፣እብሪተኛ በሆኑ ሰዎች* ቀንቼ ነበርና።+
4 ሳይሠቃዩ ይሞታሉና፤ሰውነታቸው ጤናማ* ነው።+
5 እንደ ሌሎች ሰዎች ችግር አያጋጥማቸውም፤+እንደ ሌሎች ሰዎችም መከራ አይደርስባቸውም።+
6 ስለዚህ ትዕቢት የአንገት ጌጣቸው ነው፤+ዓመፅም እንደ ልብስ ይሸፍናቸዋል።
7 ከብልጽግናቸው* የተነሳ ዓይናቸው ፈጧል፤ልባቸው ካሰበው በላይ አግኝተዋል።
8 በሌሎች ላይ ያፌዛሉ፤ ክፉ ነገርም ይናገራሉ፤+
ሌሎችን ለመጨቆን በእብሪት ይዝታሉ።+
9 የሰማይን ያህል ከፍ ያሉ ይመስል በእብሪት ይናገራሉ፤በአንደበታቸው እንዳሻቸው እየተናገሩ በምድር ላይ ይንጎራደዳሉ።
10 በመሆኑም ሕዝቡ ወደ እነሱ ይሄዳል፤ከእነሱ የተትረፈረፈ ውኃም ይጠጣል።
11 እነሱም “አምላክ እንዴት ያውቃል?+
ልዑሉ አምላክ በእርግጥ እውቀት አለው?” ይላሉ።
12 አዎ፣ ክፉዎች እንደዚህ ናቸው፤ ሁልጊዜ ሳይጨናነቁ ይኖራሉ።+
የሀብታቸውንም መጠን ያሳድጋሉ።+
13 በእርግጥም ልቤን ያነጻሁት፣ንጹሕ መሆኔንም ለማሳየት እጄን የታጠብኩት በከንቱ ነው።+
14 ቀኑን ሙሉም ተጨነቅኩ፤+በየማለዳውም ተቀጣሁ።+
15 እነዚህን ነገሮች ተናግሬ ቢሆን ኖሮ፣ሕዝብህን* መክዳት ይሆንብኝ ነበር።
16 ይህን ለመረዳት በሞከርኩ ጊዜ፣የሚያስጨንቅ ሆነብኝ፤
17 ይኸውም ወደ ታላቁ የአምላክ መቅደስ እስክገባናየወደፊት ዕጣቸውን እስክረዳ ድረስ ነበር።
18 በእርግጥም በሚያዳልጥ መሬት ላይ ታስቀምጣቸዋለህ።+
ለጥፋት እንዲዳረጉም ትጥላቸዋለህ።+
19 እንዴት በቅጽበት ጠፉ!+
በአስደንጋጭ ሁኔታ ተደመሰሱ! የደረሰባቸው ጥፋት ቅጽበታዊ ነው!
20 ይሖዋ ሆይ፣ ሰው ከእንቅልፉ ሲነሳ እንደሚረሳው ሕልም፣አንተም በምትነሳበት ጊዜ ምስላቸውን ታስወግዳለህ።*
21 ሆኖም ልቤ ተመሯል፤+ውስጤንም* ውጋት ቀስፎ ይዞታል።
22 እኔም ማመዛዘን የማልችልና ማስተዋል የጎደለኝ ሆኜ ነበር፤በአንተ ፊት ማሰብ እንደማይችል እንስሳ ሆንኩ።
23 አሁን ግን ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ነኝ፤አንተም ቀኝ እጄን ይዘሃል።+
24 በምክርህ ትመራኛለህ፤+በኋላም ክብር ታጎናጽፈኛለህ።+
25 በሰማይ ማን አለኝ?
በምድርም ላይ ከአንተ ሌላ የምሻው የለም።+
26 ሰውነቴም ሆነ ልቤ ሊዝል ይችላል፤አምላክ ግን ለዘላለም የልቤ ዓለትና ድርሻዬ ነው።+
27 ከአንተ የሚርቁ በእርግጥ ይጠፋሉ።
አንተን በመተው ብልሹ ምግባር የሚፈጽሙትን* ሁሉ ትደመስሳቸዋለህ።*+
28 እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል።+
ሥራዎቹን ሁሉ እንዳውጅ+ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ጉራቸውን በሚነዙ ሰዎች።”
^ ወይም “ቦርጫቸው የሰባ።”
^ ቃል በቃል “ከስባቸው።”
^ ቃል በቃል “የወንዶች ልጆችህን ትውልድ።”
^ ቃል በቃል “ምስላቸውን ትንቃለህ።”
^ ቃል በቃል “ኩላሊቴንም።”
^ ወይም “ታማኞች ሳይሆኑ የሚቀሩትን።”
^ ቃል በቃል “ዝም ታሰኛቸዋለህ።”