የማቴዎስ ወንጌል 4:1-25
4 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ+ ይፈትነው+ ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው።
2 እሱም 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።
3 ፈታኙም+ ቀርቦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።
4 እሱ ግን “‘ሰው ከይሖዋ* አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰ።+
5 ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ+ ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት* ላይ አቁሞ+
6 እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’”+
7 ኢየሱስም “‘አምላክህን ይሖዋን* አትፈታተነው’ ተብሎም ተጽፏል” አለው።+
8 እንደገናም ዲያብሎስ በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።+
9 ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።
10 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ* አምላክህን ብቻ አምልክ፤+ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’+ ተብሎ ተጽፏልና” አለው።
11 ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤+ እነሆም፣ መላእክት መጥተው ያገለግሉት ጀመር።+
12 ኢየሱስ፣ ዮሐንስ እንደታሰረ+ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ።+
13 ከዚያም ከናዝሬት ወጥቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃዎች፣ በባሕሩ* አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም+ መጥቶ መኖር ጀመረ፤
14 ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው የሚከተለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦
15 “ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ወደ ባሕሩ* በሚወስደው መንገድ አጠገብ ያላችሁ የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድርና የአሕዛብ ገሊላ ሆይ!
16 በጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ታላቅ ብርሃን አዩ፤ ሞት በሰዎች ላይ ባጠላበት ምድር ላሉም ብርሃን+ ወጣላቸው።”+
17 ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ ይሰብክ ጀመር።+
18 በገሊላ ባሕር* አጠገብ ሲሄድ ሁለቱን ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን+ እና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው፤ እነሱም ዓሣ አጥማጆች+ ስለነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕሩ እየጣሉ ነበር።
19 እሱም “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+
20 እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+
21 ከዚያ እልፍ እንዳለ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾችን ማለትም የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አያቸው።+ እነሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረቦቻቸውን እየጠገኑ ነበር፤ ኢየሱስም ጠራቸው።+
22 እነሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
23 ከዚያም በምኩራቦቻቸው+ እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ+ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+
24 ስለ እሱም የተወራው ወሬ በመላዋ ሶርያ ተዳረሰ፤ ሰዎችም በተለያየ በሽታና ከባድ ሕመም የሚሠቃዩትን፣+ ጋኔን የያዛቸውን፣+ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና+ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሳቸው።
25 ከዚህም የተነሳ ከገሊላ፣ ከዲካፖሊስ፣* ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በቤተ መቅደሱ ጣሪያ ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ።”
^ ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።
^ ሜድትራንያን ባሕር ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ግን ገሊላ ባሕር ነው ይላሉ።
^ በመሠረቱ ባሕር ሳይሆን ሐይቅ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌንሴሬጥ ሐይቅ፣ ገሊላ ባሕር እንዲሁም ጥብርያዶስ ባሕር ተብሎ ተጠርቷል።
^ ወይም “አሥሩ ከተሞች ከሚገኙበት ክልል።”