ምሳሌ 2:1-22
2 ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበልናትእዛዛቴን እንደ ውድ ሀብት ብታስቀምጥ፣+
2 ይህን ለማድረግ ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣+ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ልብህን ብታዘነብል፣+
3 ደግሞም ማስተዋልን ብትጣራና+ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ድምፅህን ብታሰማ፣+
4 እንደ ብር ተግተህ ብትፈልጋት፣+እንዲሁም እንደተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣+
5 ያን ጊዜ ይሖዋን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ትረዳለህ፤+ደግሞም ስለ አምላክ እውቀት ትቀስማለህ።+
6 ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣልና፤+ከአፉ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ይወጣል።
7 ለቅኖች ጥበብን* እንደ ውድ ሀብት ያከማቻል፤ንጹሕ አቋማቸውን* ጠብቀው ለሚመላለሱት ጋሻ ነው።+
8 የፍትሕን ጎዳና ይከታተላል፤የታማኞቹንም መንገድ ይጠብቃል።+
9 በዚህ ጊዜ ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገርይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ ትረዳለህ።+
10 ጥበብ ወደ ልብህ ስትገባና+እውቀት ነፍስህን* ደስ ስታሰኝ፣+
11 የማመዛዘን ችሎታ ምንጊዜም ይጠብቅሃል፤+ጥልቅ ግንዛቤም ይጋርድሃል፤
12 ይህም አንተን ከክፉ መንገድ ለማዳንእንዲሁም ጠማማ ነገር ከሚናገር ሰው፣+
13 በጨለማ መንገድ ለመጓዝቀናውን ጎዳና ከሚተዉ፣+
14 መጥፎ ድርጊት በመፈጸም ሐሴት ከሚያደርጉ፣ጠማማ በሆኑ ክፉ ነገሮች ከሚደሰቱ፣
15 መንገዳቸው ጠማማ ከሆነናአካሄዳቸው በተንኮል ከተሞላ ሰዎች አንተን ለመታደግ ነው።
16 ጋጠወጥ* ከሆነች ሴት፣ባለጌ* ሴት ከምትናገረው የሚያባብል* ቃል ያድንሃል፤+
17 ይህች ሴት በወጣትነቷ የነበራትን የቅርብ ወዳጇን*+ የምትተውእንዲሁም ከአምላኳ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን የምትረሳ ናት፤
18 ቤቷ ሰውን ይዞ ወደ ሞት ይወርዳልና፤አካሄዷም* በሞት ወደተረቱት ይወስዳል።+
19 ከእሷ ጋር ግንኙነት ያላቸው* ሁሉ አይመለሱም፤የሕይወትንም መንገድ ዳግመኛ አያገኙም።+
20 በመሆኑም የጥሩ ሰዎችን መንገድ ተከተል፤እንዲሁም ከጻድቃን ጎዳና አትውጣ፤+
21 በምድር ላይ የሚኖሩት ቅኖች ብቻ ናቸውና፤በእሷም ላይ የሚቀሩት ነቀፋ የሌለባቸው* ናቸው።+
22 ክፉዎች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፤+ከዳተኞችም ከእሷ ይወገዳሉ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብን።”
^ እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል የሥነ ምግባር ንጽሕናን፣ ሁለት ልብ አለመሆንንና እንከን የለሽ መሆንን ያመለክታል።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “እንግዳ።” ከምትከተለው የሥነ ምግባር አቋም የተነሳ ከአምላክ ጋር የተቆራረጠችን ሴት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ ቃል በቃል “ባዕድ።” ከምትከተለው የሥነ ምግባር አቋም የተነሳ ከአምላክ የራቀችን ሴት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ ወይም “የሚያማልል።”
^ ወይም “ባሏን።”
^ ቃል በቃል “መንገዷም።”
^ ቃል በቃል “ወደ እሷ የሚገቡ።”
^ ወይም “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ።”