ሩት 2:1-23

  • ሩት ወደ ቦዔዝ እርሻ ገብታ ቃረመች (1-3)

  • ሩትና ቦዔዝ ተዋወቁ (4-16)

  • ሩት፣ ቦዔዝ ስላሳያት ደግነት ለናኦሚ ነገረቻት (17-23)

2  ናኦሚ በባሏ በኩል ሀብታም የሆነ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ ይህ ሰው ቦዔዝ+ የሚባል ሲሆን የኤሊሜሌክ ቤተሰብ ነበር። 2  ሞዓባዊቷም ሩት ናኦሚን “እባክሽ ወደ እርሻ ቦታዎቹ ልሂድና ሞገስ የሚያሳየኝ ሰው ካገኘሁ እህል ልቃርም”+ አለቻት። ናኦሚም “ልጄ ሆይ፣ ሂጂ” አለቻት። 3  ሩትም ሄደች፤ በማሳውም ውስጥ ከአጫጆቹ ኋላ እየተከተለች መቃረም ጀመረች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የገባችው የኤሊሜሌክ ቤተሰብ+ ወደሆነው ወደ ቦዔዝ+ እርሻ ነበር። 4  በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፤ አጫጆቹንም “ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነሱም “ይሖዋ ይባርክህ” ብለው መለሱለት። 5  ከዚያም ቦዔዝ የአጫጆቹ አለቃ የሆነውን ወጣት “ይህች ወጣት የማን ነች?” ሲል ጠየቀው። 6  የአጫጆቹ አለቃ የሆነው ወጣትም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “ወጣቷ፣ ናኦሚ ከሞዓብ ምድር+ ስትመለስ አብራት የመጣች ሞዓባዊት+ ነች። 7  እሷም ‘እባክህ፣ ከአጫጆቹ ኋላ እየተከተልኩ የወደቁትን ዛላዎች* መቃረም+ እችላለሁ?’ አለችኝ። ይኸው ወደዚህ ከመጣችበት ከጠዋት አንስቶ ወደ ዳሱ ገብታ ጥቂት አረፍ እስካለችበት እስካሁን ድረስ አንዴም እንኳ ቁጭ አላለችም።” 8  ከዚያም ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ ስሚኝ። ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፤ የትም አትሂጂ፤ ከወጣት ሴት ሠራተኞቼም አትራቂ።+ 9  የሚያጭዱበትን ማሳ እያየሽ አብረሻቸው ሂጂ። ወጣቶቹም ወንዶች እንዳይነኩሽ* አዝዣቸዋለሁ። ውኃ ሲጠማሽ ወደ እንስራዎቹ ሄደሽ ወጣቶቹ ቀድተው ካስቀመጡት ጠጪ።” 10  እሷም መሬት ላይ በግንባሯ ተደፍታ በመስገድ “እኔ የባዕድ አገር ሰው ሆኜ+ ሳለሁ በፊትህ ሞገስ ላገኝ የበቃሁትና ትኩረት ልትሰጠኝ የቻልከው እንዴት ነው?” አለችው። 11  ቦዔዝም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ ለአማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ እንዲሁም አባትሽን፣ እናትሽንና ዘመዶችሽ የሚኖሩበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንዴት እንደመጣሽ በሚገባ ሰምቻለሁ።+ 12  ላደረግሽው ሁሉ ይሖዋ ብድራትሽን ይመልስልሽ፤+ በክንፎቹ ሥር ለመጠለል+ ብለሽ ወደ እሱ የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሙሉ ዋጋሽን* ይክፈልሽ።” 13  እሷም መልሳ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ከሴት አገልጋዮችህ አንዷ ባልሆንም እንኳ ስላጽናናኸኝና እኔን አገልጋይህን በሚያበረታታ መንገድ ስላነጋገርከኝ* ምንጊዜም በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለችው። 14  የምግብ ሰዓትም ሲደርስ ቦዔዝ “ወደዚህ ቀረብ በይ፤ ዳቦ ወስደሽ ብዪ፤ የቆረስሽውንም ሆምጣጤ ውስጥ አጥቅሺ” አላት። በመሆኑም ከአጫጆቹ ጋር ተቀመጠች። እሱም ቆሎ ዘግኖ ሰጣት፤ እሷም እስክትጠግብ ድረስ በላች፤ የተወሰነም ተረፋት። 15  ለመቃረም+ በተነሳች ጊዜም ቦዔዝ ወጣቶቹን ወንዶች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ከታጨዱት ዛላዎች* ላይ እንኳ ሳይቀር ትቃርም፤ ምንም እንዳትበድሏት።+ 16  ከታሰረው ነዶ ላይም የተወሰኑ ዛላዎችን እየመዘዛችሁ ጣሉላትና ትቃርም፤ ማንም እንዳይከለክላት።” 17  እሷም እስከ ማታ ድረስ ስትቃርም ቆየች።+ የቃረመችውንም ገብስ በወቃችው ጊዜ አንድ የኢፍ* መስፈሪያ ያህል ሆነ። 18  እህሉንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ አማቷም ምን ያህል እንደቃረመች አየች። በተጨማሪም ሩት በልታ ከጠገበች በኋላ አስተርፋ ያመጣችውን ምግብ+ አውጥታ ለአማቷ ሰጠቻት። 19  በዚህ ጊዜ አማቷ “ዛሬ የቃረምሽው የት ነው? የትስ ስትሠሪ ዋልሽ? ትኩረት የሰጠሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት።+ እሷም “ዛሬ ስሠራ የዋልኩት ቦዔዝ በተባለ ሰው እርሻ ውስጥ ነው” በማለት ከማን ጋር ስትሠራ እንደዋለች ለአማቷ ነገረቻት። 20  ናኦሚም ምራቷን “ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ታማኝ ፍቅሩን ከማሳየት ወደኋላ የማይለው ይሖዋ ይባርከው” አለቻት።+ አክላም “ሰውየው ዘመዳችን ነው።+ ከሚቤዡን ሰዎች አንዱ ነው”* አለች።+ 21  ከዚያም ሞዓባዊቷ ሩት “ደግሞም ‘ወጣቶቹ ሠራተኞቼ አዝመራዬን በሙሉ ሰብስበው እስኪጨርሱ ድረስ ከእነሱ አትራቂ’ ብሎኛል” አለቻት።+ 22  ናኦሚም ምራቷን ሩትን “ልጄ ሆይ፣ ወደ ሌላ እርሻ ብትሄጂ ሊተናኮሉሽ ስለሚችሉ ከእሱ ሴት ሠራተኞች ጋር አብረሽ መሆን ይሻልሻል” አለቻት። 23  ስለዚህ ሩት የገብሱ አዝመራና+ የስንዴው አዝመራ ተሰብስቦ እስኪያልቅ ድረስ ከቦዔዝ ሴት ሠራተኞች ሳትርቅ ስትቃርም ቆየች። ከአማቷም ጋር መኖሯን ቀጠለች።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ነዶዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንዳይተናኮሉሽ።”
ወይም “ሙሉ ወሮታሽን።”
ቃል በቃል “ለእኔ ለአገልጋይህ ልብ ስለተናገርክ።”
“ነዶዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የመቤዠት (የመዋጀት) መብት ካላቸው ዘመዶቻችን አንዱ ነው።”