ነህምያ 4:1-23

  • ተቃውሞ ቢኖርም ሥራው ወደፊት ገፋ (1-14)

  • ሠራተኞቹ የጦር መሣሪያ ታጥቀው የግንባታ ሥራውን ማከናወን ቀጠሉ (15-23)

4  ሳንባላጥ+ ቅጥሩን መልሰን እየገነባን መሆናችንን ሲሰማ በጣም ተናደደ፤ እጅግም ተበሳጨ፤ በአይሁዳውያንም ላይ ያፌዝ ነበር። 2  በወንድሞቹና በሰማርያ ጦር ሠራዊት ፊትም እንዲህ ይል ጀመር፦ “እነዚህ አቅመ ቢስ አይሁዳውያን ምን እያደረጉ ነው? ለመሆኑ ይህን ሥራ ራሳቸው ሊሠሩት ነው? መሥዋዕትስ ሊያቀርቡ ነው? ደግሞስ በአንድ ቀን ሠርተው ሊጨርሱ ያስባሉ? በእሳት ተቃጥለው የአመድ ቁልል የሆኑትን ድንጋዮች ሕይወት ሊዘሩባቸው ነው?”+ 3  በዚህ ጊዜ አጠገቡ ቆሞ የነበረው አሞናዊው+ ጦብያ+ “የሚገነቡት የድንጋይ ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ቢወጣበት ይፈርሳል” አለ። 4  አምላካችን ሆይ፣ መሳለቂያ ሆነናልና+ ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤+ እንዲበዘበዙና ተማርከው ወደ ሌላ አገር እንዲወሰዱ አድርጋቸው። 5  የግንባታውን ሥራ የሚሠሩትን ሰዎች ስለተሳደቡ በደላቸውን አትሸፍን፤+ ኃጢአታቸውም ከፊትህ እንዲደመሰስ አታድርግ። 6  እኛም ቅጥሩን መገንባታችንን ቀጠልን፤ ዙሪያውን ያለው ቅጥርም ክፍተቱ እየተደፈነ እስከ ቁመቱ እኩሌታ ድረስ ተጠገነ፤ ሕዝቡም ሥራውን ከልቡ መሥራቱን ቀጠለ። 7  ሳንባላጥ፣ ጦብያ፣+ ዓረቦች፣+ አሞናውያንና አሽዶዳውያን+ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች የመጠገኑ ሥራ እየተፋጠነና ክፍተቶቹም እየተደፈኑ መሆናቸውን ሲሰሙ እጅግ ተናደዱ። 8  እነሱም መጥተው ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና በውስጧ ሁከት ለመፍጠር በአንድነት አሴሩ። 9  እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ ከእነሱ ጥቃት ሌት ተቀን የሚጠብቁን ጠባቂዎችም አቆምን። 10  የይሁዳ ሰዎች ግን እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የሠራተኞቹ* አቅም እየተሟጠጠ ነው፤ ፍርስራሹ ደግሞ በጣም ብዙ ነው፤ ፈጽሞ ቅጥሩን መገንባት አንችልም።” 11  ጠላቶቻችንም “ምንም ሳያውቁ ወይም ሳያዩን መካከላቸው ገብተን እንገድላቸዋለን፤ ሥራውንም እናስቆማለን” ይሉ ነበር። 12  በእነሱ አቅራቢያ የሚኖሩት አይሁዳውያንም በመጡ ቁጥር “በሁሉም አቅጣጫ ይዘምቱብናል” እያሉ ደጋግመው* ይነግሩን ነበር። 13  ስለዚህ ከቅጥሩ ጀርባ በሚገኘው ገላጣ በሆነው ዝቅተኛ ቦታ ላይ ሰዎችን አቆምኩ፤ እነሱም ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን ይዘው በየቤተሰቦቻቸው እንዲቆሙ አደረግኩ። 14  ሰዎቹ መፍራታቸውን ሳይም ወዲያውኑ ተነስቼ የተከበሩትን ሰዎች፣+ የበታች ገዢዎቹንና የቀረውን ሕዝብ እንዲህ አልኳቸው፦ “አትፍሯቸው።+ ታላቁንና የተፈራውን ይሖዋን አስቡ፤+ ለወንድሞቻችሁ፣ ለወንዶች ልጆቻችሁ፣ ለሴቶች ልጆቻችሁ፣ ለሚስቶቻችሁና ለቤታችሁ ተዋጉ።” 15  ጠላቶቻችንም ሴራቸውን እንዳወቅንባቸውና እውነተኛው አምላክ ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ሰሙ፤ ከዚያም ሁላችንም ቅጥሩን ወደ መገንባቱ ሥራችን ተመለስን። 16  ከዚያን ቀን ጀምሮ አብረውኝ ካሉት ሰዎች መካከል ግማሾቹ ሥራውን ሲሠሩ+ ግማሾቹ ደግሞ ጦር፣ ጋሻና ቀስት ይዘው እንዲሁም ጥሩር ለብሰው ይቆሙ ነበር። መኳንንቱ+ ከአይሁዳውያኑ ኋላ ቆመው ድጋፍ ሲሰጧቸው 17  እነሱ ደግሞ ቅጥሩን ይገነቡ ነበር። ሸክም የሚሸከሙት ሰዎች እያንዳንዳቸው በአንድ እጃቸው ሥራውን ሲሠሩ በሌላ እጃቸው ደግሞ የጦር መሣሪያ* ይይዙ ነበር። 18  የግንባታውን ሥራ የሚሠራ እያንዳንዱ ሰው ግንባታውን የሚያከናውነው ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ነበር፤ ቀንደ መለከት የሚነፋውም+ ሰው አጠገቤ ይቆም ነበር። 19  ከዚያም የተከበሩትን ሰዎች፣ የበታች ገዢዎቹንና የቀረውን ሕዝብ እንዲህ አልኳቸው፦ “ሥራው እንደምታዩት ብዙና ሰፊ ነው፤ ቅጥሩንም የምንገነባው አንዳችን ከሌላው ተራርቀን ነው። 20  በመሆኑም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ እኛ ወዳለንበት ቦታ ተሰብሰቡ። አምላካችን ራሱ ይዋጋልናል።”+ 21  ስለዚህ ግማሾቻችን ሥራውን ስናከናውን ግማሾቹ ደግሞ ጎህ ከሚቀድበት አንስቶ ከዋክብት እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ ጦር ይዘው ይቆሙ ነበር። 22  በዚህ ጊዜ ሕዝቡን እንዲህ አልኳቸው፦ “እያንዳንዱ ሰው ከአገልጋዩ ጋር ሆኖ ሌሊቱን በኢየሩሳሌም ውስጥ ያሳልፍ፤ እነሱም ሌሊቱን ይጠብቁናል፤ ቀን ላይ ደግሞ ይሠራሉ።” 23  እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ+ እንዲሁም ይከተሉኝ የነበሩት ጠባቂዎች ፈጽሞ ልብሳችንን አናወልቅም ነበር፤ የጦር መሣሪያችንም ከቀኝ እጃችን አይለይም ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የተሸካሚዎቹ።”
ቃል በቃል “አሥር ጊዜ።”
ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያ።”