አስቴር 6:1-14
-
ንጉሡ መርዶክዮስን ከፍ ከፍ አደረገው (1-14)
6 በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ እንቢ አለው።* በመሆኑም በዘመኑ የነበረውን የታሪክ መጽሐፍ+ እንዲያመጡለት አዘዘ። መጽሐፉም በንጉሡ ፊት ተነበበ።
2 በዚህ ጊዜ ንጉሥ አሐሽዌሮስን ለመግደል* አሲረው የነበሩትን የንጉሡን ሁለት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ማለትም በር ጠባቂዎቹን ቢግታናን እና ቴሬሽን አስመልክቶ መርዶክዮስ የተናገረው ነገር ተጽፎ ተገኘ።+
3 ንጉሡም “ታዲያ መርዶክዮስ ይህን በማድረጉ ምን ክብርና እውቅና አገኘ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች “ምንም አልተደረገለትም” አሉ።
4 ንጉሡም “በግቢው ውስጥ ያለው ማን ነው?” አለ። ሃማም ባዘጋጀው እንጨት ላይ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለንጉሡ ለመናገር+ ወደ ንጉሡ ቤት* ውጨኛ ግቢ+ ገብቶ ነበር።
5 የንጉሡ አገልጋዮችም “ሃማ+ ግቢው ውስጥ ቆሟል” አሉት። ንጉሡም “ግባ በሉት” አለ።
6 ንጉሡም ሃማ በገባ ጊዜ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው ምን ሊደረግለት ይገባል?” አለው። ሃማም በልቡ “ንጉሡ ከእኔ በላይ ሊያከብረው የሚወደው ሰው ማን አለ?” ሲል አሰበ።+
7 በመሆኑም ሃማ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው፣
8 ንጉሡ የሚጎናጸፈውን ልብሰ መንግሥት+ እንዲሁም ንጉሡ የሚቀመጥበትንና በራሱ ላይ አክሊል የተደረገለትን ፈረስ ያምጡለት።
9 ከዚያም ልብሱና ፈረሱ ከንጉሡ ታላላቅ መኳንንት መካከል ለአንዱ በኃላፊነት ይሰጥ፤ እነሱም ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፤ እንዲሁም በፈረሱ ላይ አስቀምጠው በከተማው አደባባይ እንዲያልፍ ያድርጉ። በፊቱም ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል!’ ይበሉ።”+
10 ንጉሡም ወዲያውኑ ሃማን እንዲህ አለው፦ “ፈጠን በል! ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡ በር ላይ ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስም ልክ እንዳልከው አድርግለት። ከተናገርከው ውስጥ አንዱም ሳይፈጸም እንዳይቀር።”
11 ስለዚህ ሃማ ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፤ መርዶክዮስንም+ አለበሰው፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጦ በከተማው አደባባይ እንዲያልፍ አደረገ፤ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል!” እያለ በፊቱ ያውጅ ነበር።
12 ከዚያም መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ፤ ሃማ ግን ራሱን ተከናንቦ እያዘነ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ።
13 ሃማ ያጋጠመውን ነገር ሁሉ ለሚስቱ ለዜሬሽና+ ለጓደኞቹ በሙሉ ሲነግራቸው ጥበበኛ አማካሪዎቹና ሚስቱ ዜሬሽ “በፊቱ መውደቅ የጀመርክለት መርዶክዮስ የአይሁዳውያን ዘር ከሆነ ልታሸንፈው አትችልም፤ ያለምንም ጥርጥር በፊቱ ትወድቃለህ” አሉት።
14 እነሱም ገና ከእሱ ጋር እየተነጋገሩ ሳሉ የንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ደርሰው ሃማን አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ እያጣደፉ ወሰዱት።+