ዘዳግም 19:1-21

  • የደም ዕዳና የመማጸኛ ከተሞች (1-13)

  • ወሰን አትግፋ (14)

  • ዳኛ ፊት ቀርቦ መመሥከር (15-21)

    • ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች ያስፈልጋሉ (15)

19  “አምላክህ ይሖዋ ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥህን ብሔራት፣ ይሖዋ በሚያጠፋቸውና አንተም እነሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው መኖር በምትጀምርበት ጊዜ+ 2  አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ሦስት ከተሞችን ለይ።+ 3  አምላክህ ይሖዋ እንድትወርሳት የሚሰጥህን ምድር ሦስት ቦታ ከፋፍላት፤ እንዲሁም ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ እንዲችል መንገድ አዘጋጅ። 4  “እዚያ ለመኖር ሸሽቶ የሄደን፣ ነፍስ ያጠፋ ሰው በተመለከተ መደረግ ያለበት ነገር ይህ ነው፦ ለባልንጀራው የቆየ ጥላቻ የሌለው አንድ ሰው ሳያስበው ባልንጀራውን መትቶ ቢገድለው፣+ 5  ለምሳሌ ከባልንጀራው ጋር እንጨት ለመቁረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉንም ለመቁረጥ መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ላይ ወልቆ ባልንጀራውን ቢመታውና ቢገድለው ነፍሰ ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።+ 6  አለዚያ በንዴት የበገነው* ደም ተበቃይ+ ከተማዋ ሩቅ ከመሆኗ የተነሳ ነፍሰ ገዳዩን አሳዶ ሊደርስበትና ሊገድለው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ለባልንጀራው የቆየ ጥላቻ ስለሌለው መሞት አይገባውም።+ 7  ‘ሦስት ከተሞችን ለይ’ በማለት ያዘዝኩህ ለዚህ ነው። 8  “አምላክህ ይሖዋ ለአባቶችህ በማለላቸው መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህና+ ለእነሱ ለመስጠት ቃል የገባላቸውን ምድር በሙሉ ሲሰጥህ+ 9  ይኸውም አምላክህን ይሖዋን እንድትወድና ዘወትር በመንገዶቹ እንድትሄድ እኔ ዛሬ የማዝህን ይህን ትእዛዝ ሁሉ በመጠበቅህ+ ግዛትህን ሲያሰፋልህ ከእነዚህ ሦስት ከተሞች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትለያለህ።+ 10  ይህም አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ንጹሕ ደም እንዳይፈስና+ በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳትሆን ነው።+ 11  “ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣+ አድብቶም ለሞት የሚያበቃ ጉዳት ቢያደርስበትና ሰውየው ቢሞት፣ ገዳዩም ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ ቢሸሽ 12  የሚኖርበት ከተማ ሽማግሌዎች ሰውየውን ከዚያ በማስመጣት ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት፤ ይህ ሰው ሞት ይገባዋል።+ 13  አትዘንለት፤* መልካም እንዲሆንልህ ንጹሕ ደም በማፍሰስ የሚመጣን በደል ከእስራኤል አስወግድ።+ 14  “አምላክህ ይሖዋ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ርስትህን በምትቀበልበት ጊዜ የቀድሞ አባቶችህ የከለሉትን ወሰን በማለፍ የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንካ።+ 15  “አንድ ሰው የትኛውንም ስህተት ወይም የትኛውንም ኃጢአት ቢፈጽም ግለሰቡን ጥፋተኛ ለማድረግ አንድ ምሥክር አይበቃም።+ ጉዳዩ የሚጸናው ሁለት ምሥክሮች ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል* ነው።+ 16  ተንኮል ያሰበ አንድ ምሥክር አንድን ግለሰብ የሆነ በደል ፈጽሟል በማለት ቢመሠክርበት+ 17  ክርክር የገጠሙት ሁለቱ ሰዎች በይሖዋ ፊት፣ በካህናቱና በዚያን ጊዜ ዳኛ ሆነው በሚያገለግሉት ሰዎች ፊት ይቆማሉ።+ 18  ዳኞቹም ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤+ ምሥክሩ ሐሰተኛ ምሥክር ከሆነና ወንድሙን የወነጀለው በሐሰት ከሆነ 19  በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያቀደውን ነገር በራሱ ላይ አድርጉበት፤+ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+ 20  ሌሎችም ይህን ሲሰሙ ይፈራሉ፤ በመካከልህም እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ፈጽሞ ዳግመኛ አያደርጉም።+ 21  አዘኔታ አታሳይ፤+ ሕይወት* ስለ ሕይወት፣* ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ልቡ የነደደው።”
ቃል በቃል “ዓይንህ አይዘንለት።”
ቃል በቃል “በሁለት ምሥክሮች ወይም በሦስት ምሥክሮች አፍ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”