ዘዳግም 22:1-30
22 “የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ካየህ እንዳላየ ሆነህ አትለፍ።+ ከዚህ ይልቅ ወደ ወንድምህ መልሰህ ልትወስደው ይገባል።
2 ሆኖም ወንድምህ በአቅራቢያህ የማይኖር ወይም እሱን የማታውቀው ከሆነ እንስሳውን ወደ ቤትህ አምጣው፤ ወንድምህ እሱን ፈልጎ እስኪመጣም ድረስ አንተ ጋ ይቆይ። ከዚያም መልስለት።+
3 አህያውንም ሆነ ልብሱን ወይም ወንድምህ ጠፍቶበት ያገኘኸውን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ እንዲሁ ማድረግ ይኖርብሃል። አይተህ ዝም ብለህ ማለፍ የለብህም።
4 “የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታይ እንዳላየ ሆነህ አትለፍ። ከዚህ ይልቅ እንስሳው ተነስቶ እንዲቆም በማድረግ ሰውየውን ልትረዳው ይገባል።+
5 “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድ ደግሞ የሴት ልብስ አይልበስ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።
6 “መንገድ ላይ ስትሄድ ጫጩቶች ወይም እንቁላሎች ያሉበት የወፍ ጎጆ፣ ዛፍ ላይ ወይም መሬት ላይ ብታገኝና እናትየው ጫጩቶቹን ወይም እንቁላሎቹን ታቅፋ ቢሆን እናትየውን ከጫጩቶቿ ጋር አብረህ አትውሰድ።+
7 እናትየውን ልቀቃት፤ ጫጩቶቹን ግን መውሰድ ትችላለህ። ይህን የምታደርገው መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ እንዲረዝም ነው።
8 “አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ አንድ ሰው ከጣሪያህ ላይ ወድቆ በቤትህ ላይ የደም ዕዳ እንዳታመጣ በጣሪያህ ዙሪያ መከታ ሥራ።+
9 “በወይን እርሻህ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ።+ እንዲህ ካደረግክ ከዘራኸው ዘር የሚገኘው ምርትም ሆነ የወይን እርሻህ ምርት በሙሉ ተወርሶ ለቤተ መቅደሱ ገቢ ይደረጋል።
10 “በሬና አህያ አንድ ላይ ጠምደህ አትረስ።+
11 “ከሱፍና ከበፍታ ተቀላቅሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ።+
12 “በምትለብሰው ልብስ ላይ በአራቱም ማዕዘን ዘርፍ አድርግ።+
13 “አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ከእሷ ጋር ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ ቢጠላት፣
14 መጥፎ ምግባር እንዳላት አድርጎ ቢከሳትና ‘ይህችን ሴት አግብቼ ነበር፤ ሆኖም ከእሷ ጋር ግንኙነት ስፈጽም የድንግልናዋን ማስረጃ አላገኘሁም’ በማለት መጥፎ ስም ቢሰጣት
15 የልጅቷ አባትና እናት ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በከተማዋ በር ወደሚገኙት ሽማግሌዎች ይምጡ።
16 የልጅቷም አባት ሽማግሌዎቹን እንዲህ ይበላቸው፦ ‘ልጄን ለዚህ ሰው ድሬለት ነበር፤ እሱ ግን ጠላት፤
17 እንዲሁም “ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም” በማለት መጥፎ ምግባር እንዳላት አድርጎ እየከሰሳት ነው። እንግዲህ የልጄ የድንግልና ማስረጃ ይኸውላችሁ።’ እነሱም ልብሱን በከተማዋ ሽማግሌዎች ፊት ይዘርጉት።
18 የዚያች ከተማ ሽማግሌዎችም+ ሰውየውን ወስደው ይቅጡት።+
19 እነሱም 100 የብር ሰቅል* ያስከፍሉታል፤ ከዚያም ገንዘቡን ለልጅቷ አባት ይስጡት፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የአንዲትን እስራኤላዊት ድንግል ስም አጥፍቷል፤+ እሷም ሚስቱ ሆና ትኖራለች። በሕይወት ዘመኑም ሁሉ እንዲፈታት አይፈቀድለትም።
20 “ሆኖም ክሱ እውነት ከሆነና ልጅቷ ድንግል እንደነበረች የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካልተገኘ
21 ልጅቷን ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያውጧት፤ በአባቷ ቤት የፆታ ብልግና በመፈጸም በእስራኤል ውስጥ አስነዋሪ ድርጊት ስለፈጸመች+ የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት።+ በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+
22 “አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ ከሴትየዋ ጋር የተኛው ሰውም ሆነ ሴትየዋ ሁለቱም ይገደሉ።+ በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል አስወግድ።
23 “አንድ ሰው ለሌላ ሰው የታጨችን አንዲት ድንግል ከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእሷ ጋር ቢተኛ
24 ልጅቷ በከተማው ውስጥ ስላልጮኸች፣ ሰውየው ደግሞ የባልንጀራውን ሚስት ስላዋረደ ሁለቱንም ወደ ከተማዋ በር አውጥታችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው።+ በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።
25 “ይሁንና ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ያገኛት ሜዳ ላይ ቢሆንና በጉልበት አስገድዶ አብሯት ቢተኛ እሱ ብቻ ይገደል፤
26 በልጅቷ ላይ ምንም አታድርግ። ልጅቷ ሞት የሚገባው ኃጢአት አልሠራችም። ይህ ጉዳይ በባልንጀራው ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ከሚገድል* ሰው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።+
27 ምክንያቱም ሰውየው ልጅቷን ያገኛት ሜዳ ላይ ሲሆን የታጨችው ልጅ ብትጮኽም እንኳ ማንም አልደረሰላትም።
28 “አንድ ሰው ያልታጨችን አንዲት ድንግል አግኝቶ ቢይዛትና አብሯት ቢተኛ፣ በኋላም ቢጋለጡ+
29 ሰውየው ለልጅቷ አባት 50 የብር ሰቅል ይስጥ፤ እሷም ሚስቱ ትሆናለች።+ ስላዋረዳትም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲፈታት አይፈቀድለትም።
30 “ማንም ሰው አባቱን እንዳያዋርድ* የአባቱን ሚስት አያግባ።+