ዘፍጥረት 33:1-20

  • ያዕቆብ ከኤሳው ጋር ተገናኘ (1-16)

  • ያዕቆብ ወደ ሴኬም ተጓዘ (17-20)

33  ያዕቆብም ቀና ብሎ ሲመለከት ኤሳው ሲመጣ አየ፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች ነበሩ።+ በመሆኑም ልጆቹን ለሊያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ ሴት አገልጋዮች+ አከፋፈላቸው። 2  እሱም ሴት አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን ከፊት፣+ ሊያንና ልጆቿን ከእነሱ ቀጥሎ፣+ ራሔልንና ዮሴፍን+ ደግሞ ከእነሱ በኋላ እንዲሆኑ አደረገ። 3  ከዚያም እሱ ቀድሟቸው ሄደ፤ ወደ ወንድሙ ሲቀርብም ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ። 4  ሆኖም ኤሳው ወደ እሱ እየሮጠ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5  ኤሳውም ቀና ብሎ ሴቶቹንና ልጆቹን ሲያይ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” እሱም “አምላክ በቸርነቱ ለአገልጋይህ የሰጣቸው ልጆች ናቸው”+ አለው። 6  በዚህ ጊዜ ሴት አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ፤ 7  ሊያና ልጆቿም ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ። ከዚያም ዮሴፍና ራሔል ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ።+ 8  ኤሳውም “ቀደም ሲል ያገኘኋቸውን ሰዎችና እንስሳት የላክሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።+ እሱም “በጌታዬ ፊት ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።+ 9  ከዚያም ኤሳው “ወንድሜ ሆይ፣ እኔ ከበቂ በላይ አለኝ።+ የአንተ የሆነው ለራስህ ይሁን” አለው። 10  ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፦ “የለም፣ እንዲህማ አይሆንም። በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ስጦታዬን ከእጄ መውሰድ አለብህ፤ ምክንያቱም ስጦታውን የላክሁት ፊትህን እንዳይ ብዬ ነው። እንዲህ በደስታ ተቀብለኸኝ የአንተን ፊት ማየቴ ራሱ ለእኔ የአምላክን ፊት የማየት ያህል ነው።+ 11  አምላክ ሞገስ ስላሳየኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ስላለኝ+ የመልካም ምኞት መግለጫ እንዲሆን ያመጣሁልህን ይህን ስጦታ እባክህ ተቀበለኝ።”+ ያዕቆብም አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ ስጦታውን ወሰደ። 12  በኋላም ኤሳው “በል እንነሳና ጉዟችንን እንቀጥል፤ እኔም ከፊት ከፊትህ እሄዳለሁ” አለው። 13  እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “ልጆቹ አቅም እንደሌላቸው+ እንዲሁም የሚያጠቡ በጎችና ከብቶች እንዳሉኝ ጌታዬ ያውቃል። እንስሳቱ ለአንድ ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ መንጋው በሙሉ ያልቃል። 14  ስለዚህ ጌታዬ ከአገልጋዩ ቀድሞ ይሂድ፤ እኔ ግን ከጌታዬ ጋር እዚያው ሴይር እስከምንገናኝ+ ድረስ በምነዳቸው ከብቶች ፍጥነትና እንደ ልጆቹ እርምጃ ቀስ እያልኩ ላዝግም።” 15  ኤሳውም “እባክህ ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። እሱም “ለምን ብለህ? በጌታዬ ፊት ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው። 16  በመሆኑም በዚያ ቀን ኤሳው ወደ ሴይር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። 17  ያዕቆብም ወደ ሱኮት+ ሄደ፤ በዚያም ለራሱ ቤት፣ ለመንጎቹም ዳስ ሠራ። የቦታውንም ስም ሱኮት* ያለው ለዚህ ነበር። 18  ያዕቆብ ከጳዳንአራም+ ተነስቶ በመጓዝ በከነአን+ ምድር ወደምትገኘው ወደ ሴኬም+ ከተማ በሰላም ደረሰ፤ በከተማዋም አቅራቢያ ሰፈረ። 19  ከዚያም ድንኳኑን የተከለበትን ቦታ ከሴኬም አባት ከኤሞር ወንዶች ልጆች እጅ በ100 ጥሬ ገንዘብ ገዛ።+ 20  በዚያም መሠዊያ አቆመ፤ መሠዊያውንም አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ ብሎ ጠራው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ዳሶች፤ መጠለያዎች” የሚል ትርጉም አለው።