የዮሐንስ ወንጌል 17:1-26
17 ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤+
2 ይህም በሥጋ ለባሽ* ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው+ ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው+ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው።+
3 ብቸኛው* እውነተኛ አምላክ+ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ*+ የዘላለም ሕይወት+ ነው።
4 እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ+ በምድር ላይ አከበርኩህ።+
5 ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ+ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።
6 “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ።*+ እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል።*
7 የሰጠኸኝ ነገር ሁሉ ከአንተ የተገኘ መሆኑን አሁን አውቀዋል፤
8 ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤+ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤+ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል።+
9 ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤
10 ደግሞም የእኔ የሆነው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤+ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ እኔም በእነሱ መካከል ከብሬአለሁ።
11 “ከእንግዲህ እኔ በዓለም ውስጥ አልኖርም፤ እነሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤+ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን* ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣*+ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው።+
12 እኔ ከእነሱ ጋር ሳለሁ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስል ስጠብቃቸው ቆይቻለሁ፤+ ደግሞም ጠብቄአቸዋለሁ፤ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ ከጥፋት ልጅ በቀር+ አንዳቸውም አልጠፉም።+
13 አሁን ግን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ደስታዬ በውስጣቸው ሙሉ እንዲሆን+ አሁን በዓለም ላይ እያለሁ እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ።
14 ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ ሆኖም እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው።+
15 “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው* እንድትጠብቃቸው ነው።+
16 እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ+ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።+
17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤*+ ቃልህ እውነት ነው።+
18 አንተ ወደ ዓለም እንደላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ።+
19 እነሱም በእውነት እንዲቀደሱ እኔ ራሴም ስለ እነሱ ስል ቅድስናዬን እጠብቃለሁ።
20 “የምለምንህ ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው፤
21 ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤+ ይኸውም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ ያምን ዘንድ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ+ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው።
22 እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ+ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ።
23 እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት አለኝ፤ አንተም ከእኔ ጋር አንድነት አለህ፤ ይህ ደግሞ እነሱም ፍጹም አንድ እንዲሆኑ* ነው፤ በተጨማሪም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው።
24 አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤+ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው።+
25 ጻድቅ አባት ሆይ፣ በእርግጥ ዓለም አላወቀህም፤+ እኔ ግን አውቅሃለሁ፤+ እነዚህ ደግሞ አንተ እንደላክኸኝ አውቀዋል።
26 እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ+ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሰው ዘር፤ በሰዎች።”
^ እውነተኛው አምላክ እሱ ብቻ መሆኑን ያመለክታል።
^ ወይም “እውቀት መቅሰም።” እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታል።
^ ወይም “አሳውቄአቸዋለሁ።”
^ ወይም “ታዘዋል።”
^ ወይም “አንድነት እንዲኖራቸው።”
^ ወይም “አንድነት እንዳለን።”
^ ሰይጣንን ያመለክታል።
^ ወይም “ለያቸው።”
^ ወይም “ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው።”
^ ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።