አንደኛ ዜና መዋዕል 27:1-34

  • ንጉሡን የሚያገለግሉ ባለሥልጣናት (1-34)

27  የእስራኤላውያን ቁጥር ይኸውም የአባቶች ቤቶች መሪዎች፣ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆችና+ ዓመቱን ሙሉ በየወሩ የሚገቡትንም ሆነ የሚወጡትን ምድቦች በመምራት ንጉሡን የሚያገለግሉት+ አለቆቻቸው ቁጥር ይህ ነው፤ በእያንዳንዱ ምድብ 24,000 ነበሩ። 2  በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያው ምድብ አዛዥ የዛብድኤል ልጅ ያሾብአም+ ነበር፤ በእሱም ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 3  እሱ ከፋሬስ+ ወንዶች ልጆች መካከል በመጀመሪያው ወር እንዲያገለግሉ የተመደቡት የቡድኖቹ አለቆች ሁሉ መሪ ነበር። 4  አሆሐያዊው+ ዶዳይ+ የሁለተኛው ወር ምድብ አዛዥ ነበር። መሪው ሚቅሎት ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 5  በሦስተኛው ወር እንዲያገለግል የተመደበው የሦስተኛው ቡድን አዛዥ የካህናት አለቃው የዮዳሄ+ ልጅ በናያህ+ ነበር፤ በእሱም ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 6  በናያህ ከሠላሳዎቹ ኃያላን ተዋጊዎች አንዱ የነበረ ሲሆን የሠላሳዎቹ አለቃ ነበር፤ ልጁ አሚዛባድም በእሱ ምድብ ውስጥ የበላይ ነበር። 7  በአራተኛው ወር፣ አራተኛው አዛዥ የኢዮዓብ ወንድም+ አሳሄል+ ሲሆን ልጁ ዘባድያህ የእሱ ተተኪ ነበር፤ በምድቡም ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 8  በአምስተኛው ወር፣ አምስተኛው አዛዥ ይዝራሃዊው ሻምሁት ነበር፤ በእሱም ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 9  በስድስተኛው ወር፣ ስድስተኛው አዛዥ የተቆአዊው+ የኢቄሽ ልጅ ኢራ+ ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 10  በሰባተኛው ወር፣ ሰባተኛው አዛዥ ከኤፍሬማውያን ወገን የሆነው ጴሎናዊው ሄሌጽ+ ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 11  በስምንተኛው ወር፣ ስምንተኛው አዛዥ ከዛራውያን+ ወገን የሆነው ሁሻዊው ሲበካይ+ ነበር፤ በእሱም ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 12  በዘጠነኛው ወር፣ ዘጠነኛው አዛዥ ከቢንያማውያን ወገን የሆነው አናቶታዊው+ አቢዔዜር+ ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 13  በአሥረኛው ወር፣ አሥረኛው አዛዥ ከዛራውያን+ ወገን የሆነው ነጦፋዊው ማህራይ+ ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 14  በ11ኛው ወር፣ 11ኛው አዛዥ ከኤፍሬም ልጆች ወገን የሆነው ጲራቶናዊው በናያህ+ ነበር፤ በእሱም ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 15  በ12ኛው ወር፣ 12ኛው አዛዥ ከኦትኒኤል ቤተሰብ የሆነው ነጦፋዊው ሄልዳይ ሲሆን በእሱ ምድብ ውስጥ 24,000 ሰዎች ነበሩ። 16  የእስራኤል ነገዶች መሪዎች እነዚህ ናቸው፦ ከሮቤላውያን የዚክሪ ልጅ ኤሊዔዘር መሪ ነበር፤ ከስምዖናውያን የማአካ ልጅ ሰፋጥያህ፤ 17  ከሌዊ የቀሙኤል ልጅ ሃሻብያህ፤ ከአሮን ቤተሰብ ሳዶቅ፤ 18  ከይሁዳ ከዳዊት ወንድሞች አንዱ የሆነው ኤሊሁ፤+ ከይሳኮር የሚካኤል ልጅ ኦምሪ፤ 19  ከዛብሎን የአብድዩ ልጅ ይሽማያህ፤ ከንፍታሌም የአዝርዔል ልጅ የሪሞት፤ 20  ከኤፍሬማውያን መካከል የአዛዝያ ልጅ ሆሺአ፤ ከምናሴ ነገድ እኩሌታ የፐዳያህ ልጅ ኢዩኤል፤ 21  በጊልያድ ካለው የምናሴ ነገድ እኩሌታ የዘካርያስ ልጅ ኢዶ፤ ከቢንያም የአበኔር+ ልጅ ያአሲዔል፤ 22  ከዳን የየሮሃም ልጅ አዛርዔል። እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23  ይሖዋ እስራኤልን በሰማያት እንዳሉ ከዋክብት እንደሚያበዛ ቃል ገብቶ ስለነበር ዳዊት 20 ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን አልቆጠረም።+ 24  የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ ቆጠራውን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም አልፈጸመውም። የአምላክ ቁጣ በእስራኤል ላይ ስለነደደ*+ በንጉሥ ዳዊት ዘመን ስለተከናወኑት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ ዘገባ ላይ ቁጥሩ አልሰፈረም። 25  የአዲዔል ልጅ አዝማዌት በንጉሡ ግምጃ ቤቶች+ ላይ ተሹሞ ነበር። የዖዝያ ልጅ ዮናታን ደግሞ በገጠሩ፣ በከተሞቹ፣ በመንደሮቹና በማማዎቹ ውስጥ በሚገኙት ግምጃ ቤቶች ላይ ተሹሞ ነበር። 26  የከሉብ ልጅ ኤዝሪ መሬቱን ለማልማት በመስክ በሚሠሩት ሠራተኞች ላይ ተሹሞ ነበር። 27  ራማዊው ሺምአይ በወይን እርሻዎቹ ላይ ተሹሞ ነበር፤ ሲፍሞታዊው ዛብዲ ለወይን ጠጅ አቅርቦት በሚውለው የወይን እርሻዎቹ ምርት ላይ ተሹሞ ነበር። 28  ጌዴራዊው ባአልሀናን በሸፌላ+ በነበሩት የወይራ ዛፎችና የሾላ ዛፎች+ ላይ ተሹሞ ነበር፤ ዮአስ ደግሞ በዘይት ማከማቻዎቹ ላይ ተሹሞ ነበር። 29  ሳሮናዊው ሺጥራይ በሳሮን+ የግጦሽ መሬት በሚሰማሩት ከብቶች ላይ ተሹሞ ነበር፤ የአድላይ ልጅ ሻፋጥ ደግሞ በሸለቋማ ሜዳዎቹ* ላይ በሚሰማሩት ከብቶች ላይ ተሹሞ ነበር። 30  እስማኤላዊው ኦቢል በግመሎቹ ላይ ተሹሞ ነበር፤ መሮኖታዊው የህድያ በአህዮቹ* ላይ ተሹሞ ነበር። 31  አጋራዊው ያዚዝ በመንጎቹ ላይ ተሹሞ ነበር። እነዚህ ሁሉ በንጉሥ ዳዊት ንብረት ላይ የተሾሙ አለቆች ነበሩ። 32  የዳዊት የወንድሙ ልጅ ዮናታን+ አስተዋይ የሆነ አማካሪና ጸሐፊ ነበር፤ የሃክሞኒ ልጅ የሂኤል የንጉሡ ልጆች ተንከባካቢ ነበር።+ 33  አኪጦፌል+ የንጉሡ አማካሪ ነበር፤ አርካዊው ኩሲ+ ደግሞ የንጉሡ ወዳጅ* ነበር። 34  ከአኪጦፌል በኋላ አማካሪ ሆነው የተሾሙት የበናያህ+ ልጅ ዮዳሄ እና አብያታር+ ነበሩ፤ ኢዮዓብ+ ደግሞ የንጉሡ ሠራዊት ዋና አዛዥ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በእስራኤልም ላይ ቁጣ ስለሆነ።”
ወይም “በረባዳማ ሜዳዎቹ።”
ቃል በቃል “በእንስት አህዮቹ።”
ወይም “ሚስጥረኛ።”