የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 2:1-29

  • ኢየሱስ፣ የማስተሰረያ መሥዋዕት (1, 2)

  • የእሱን ትእዛዛት መጠበቅ (3-11)

    • አሮጌውና አዲሱ ትእዛዝ (7, 8)

  • መልእክቱን የጻፈበት ምክንያት (12-14)

  • ዓለምን አትውደዱ (15-17)

  • ፀረ ክርስቶስን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (18-29)

2  የተወደዳችሁ ልጆቼ፣ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት* እንዳትሠሩ ነው። ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት* አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።+ 2  እሱ ለእኛ ኃጢአት+ የቀረበ የማስተሰረያ* መሥዋዕት ነው፤+ ሆኖም ለእኛ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ጭምር ነው።+ 3  ደግሞም ትእዛዛቱን መፈጸማችንን ከቀጠልን እሱን የምናውቅ መሆናችንን በዚህ እንረዳለን። 4  “እሱን አውቀዋለሁ” እያለ ትእዛዛቱን የማይፈጽም ሰው ቢኖር ውሸታም ነው፤ እውነትም በዚህ ሰው ውስጥ የለም። 5  ሆኖም የእሱን ቃል የሚጠብቅ ማንም ቢኖር የአምላክ ፍቅር በእርግጥ በዚህ ሰው ላይ ፍጹም በሆነ መንገድ ይታያል።+ ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለንም በዚህ እናውቃለን።+ 6  ከእሱ ጋር ያለኝን አንድነት ጠብቄ እኖራለሁ የሚል፣ እሱ በተመላለሰበት መንገድ የመመላለስ ግዴታ አለበት።+ 7  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበራችሁን የቆየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም።+ ይህ የቆየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8  ይሁንና በእሱም ሆነ በእናንተ ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ እጽፍላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን አሁንም እንኳ እያበራ ነው።+ 9  በብርሃን ውስጥ እንዳለ እየተናገረ ወንድሙን የሚጠላ+ አሁንም በጨለማ ውስጥ ነው።+ 10  ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ውስጥ ይኖራል፤+ በእሱም ዘንድ ምንም የሚያሰናክል ነገር የለም። 11  ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማም ይመላለሳል፤+ ደግሞም ጨለማው ዓይኑን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።+ 12  ልጆቼ ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ለእሱ ስም ሲባል ኃጢአታችሁ ይቅር ስለተባለላችሁ ነው።+ 13  አባቶች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ያለውን እሱን ስላወቃችሁት ነው። እናንተ ወጣት ወንዶች፣ የምጽፍላችሁ ክፉውን ስላሸነፋችሁት ነው።+ ልጆች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ አብን ስላወቃችሁት ነው።+ 14  አባቶች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ያለውን እሱን ስላወቃችሁት ነው። እናንተ ወጣት ወንዶች፣ የምጽፍላችሁ ጠንካሮች ስለሆናችሁ፣+ የአምላክ ቃል በልባችሁ ስለሚኖርና+ ክፉውን ስላሸነፋችሁት ነው።+ 15  ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ።+ ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም፤+ 16  ምክንያቱም በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣+ የዓይን አምሮትና+ ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት* ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም። 17  ከዚህም በተጨማሪ ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤+ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።+ 18  ልጆቼ ሆይ፣ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም ፀረ ክርስቶስ እየመጣ ነው፤+ አሁንም እንኳ ብዙ ፀረ ክርስቶሶች መጥተዋል፤+ ከዚህም በመነሳት ይህ የመጨረሻው ሰዓት መሆኑን እናውቃለን። 19  በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል።+ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ሆኖም ከእኛ ወገን የሆኑት ሁሉም አለመሆናቸው በግልጽ ይታይ ዘንድ ከእኛ ተለይተው ወጡ።+ 20  እናንተ ግን ቅዱስ ከሆነው ከእሱ የመንፈስ ቅብዓት አግኝታችኋል፤+ ደግሞም ሁላችሁም እውቀት አላችሁ። 21  የምጽፍላችሁ እውነትን+ ስለማታውቁ ሳይሆን እውነትን ስለምታውቁና ከእውነት ምንም ዓይነት ውሸት ስለማይወጣ ነው።+ 22  ኢየሱስን፣ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ውሸታም ማን ነው?+ ይህ አብንና ወልድን የሚክደው ፀረ ክርስቶስ ነው።+ 23  ወልድን የሚክድ ሁሉ በአብ ዘንድም ተቀባይነት የለውም።+ ወልድን አምኖ የሚቀበል ሁሉ+ ግን በአብም ዘንድ ተቀባይነት አለው።+ 24  በእናንተ በኩል ግን ከመጀመሪያ የሰማችሁት በልባችሁ ይኑር።+ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በልባችሁ የሚኖር ከሆነ እናንተም ከወልድና ከአብ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ትኖራላችሁ። 25  ከዚህም በተጨማሪ እሱ ራሱ የገባልን የተስፋ ቃል የዘላለም ሕይወት ነው።+ 26  እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ሊያሳስቷችሁ ከሚሞክሩት ሰዎች የተነሳ ነው። 27  እናንተ ግን ከእሱ የተቀበላችሁት የመንፈስ ቅብዓት+ በውስጣችሁ ይኖራል፤ በመሆኑም ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ያገኛችሁት ይህ ቅብዓት ስለ ሁሉም ነገር እያስተማራችሁ ነው፤+ ደግሞም እውነት እንጂ ውሸት አይደለም። ይህ ቅብዓት ባስተማራችሁ መሠረት ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ።+ 28  እንግዲህ ልጆቼ፣ እሱ በሚገለጥበት ጊዜ የመናገር ነፃነት+ እንዲኖረንና እሱ በሚገኝበት ወቅት ለኀፍረት ተዳርገን ከእሱ እንዳንርቅ ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ። 29  እሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእሱ የተወለደ መሆኑን ታውቃላችሁ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጠበቃ።”
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል በሆነ ጊዜ ላይ ለአፍታ የተፈጸመን ድርጊት የሚያመለክት ነው።
ወይም “የእርቅ።”
ወይም “በሀብት ጉራ መንዛት።”