ሀ3
መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ የቆየው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ የሆነው አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲቆይም አድርጓል። የሚከተለው ሐሳብ እንዲጻፍ ያደረገው እሱ ነው፦
‘የአምላካችን ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’–ኢሳይያስ 40:8
የመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የአረማይክ ቅዱሳን መጻሕፍት a ወይም ደግሞ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው ባይቆዩም ይህ አባባል እውነት ነው። ይሁን እንጂ በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች የሚያስተላልፉትን ሐሳብ በትክክል እንደያዘ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች የአምላክ ቃል ተጠብቆ እንዲቆይ አድርገዋል
አምላክ ያስጀመረው አንድ ጥንታዊ ልማድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክቶ ለሚነሳው ጥያቄ በከፊል መልስ ይሰጣል። አምላክ በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ እንዲገለበጥ አዝዞ ነበር። b ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የእስራኤል ነገሥታት በጽሑፍ የሰፈረውን ሕግ እንዲገለብጡ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 17:18) በተጨማሪም አምላክ፣ ሌዋውያን በጽሑፍ የሰፈረውን ሕግ ጠብቀው እንዲያቆዩና ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 31:26፤ ነህምያ 8:7) አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን ከተወሰዱ በኋላ ጽሑፉን የሚገለብጡ በቡድን የተደራጁ ገልባጮች ወይም ጸሐፍት (ሶፌሪም) ብቅ አሉ። (ዕዝራ 7:6 የግርጌ ማስታወሻዎች) በጊዜ ሂደት እነዚህ ጸሐፍት የ39ኙን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በርካታ ቅጂዎች አዘጋጁ።
ጸሐፍት ለብዙ መቶ ዘመናት እነዚህን መጻሕፍት በጥንቃቄ ሲገለብጡ ቆይተዋል። በመካከለኛው ዘመን ማሶሬቶች ተብለው የሚጠሩ በቡድን የተደራጁ አይሁዳውያን ጸሐፍት ቅጂዎቹን የመገልበጡን ልማድ ተረከቡ። ማሶሬቶች ያዘጋጁት ጥንታዊው የተሟላ ቅጂ ሌኒንግራድ ኮዴክስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህም በ1008/1009 ዓ.ም. እንደተጻፈ
ይታመናል። ይሁንና በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ 220 የሚሆኑ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ወይም ቁርጥራጮች በሙት ባሕር ጥቅልሎች ውስጥ ተገኙ። እነዚህ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ከሌኒንግራድ ኮዴክስ አንድ ሺህ ዓመት ቀድመው የተጻፉ ናቸው። የሙት ባሕር ጥቅልሎችን ከሌኒንግራድ ኮዴክስ ጋር በማወዳደር የተገኘው ውጤት አንድ ሐቅ ያስገነዝበናል፦ የሙት ባሕር ጥቅልሎቹ ከሌኒንግራድ ኮዴክሱ ጋር የተወሰነ የአገላለጽ ልዩነት ቢኖራቸውም ከእነዚህ ልዩነቶች መካከል አንዱም ቢሆን በመልእክቱ ላይ ያመጣው ለውጥ የለም።ስለ 27ቱ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ መጻሕፍት መጀመሪያ የተጻፉት በተወሰኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትና ጥቂት በሆኑ ሌሎች ቀደምት ደቀ መዛሙርት ነው። የጥንት ክርስቲያኖች የአይሁዳውያን ጸሐፍትን ልማድ በመከተል እነዚህን መጻሕፍት ይገለብጡ ነበር። (ቆላስይስ 4:16) የሮም ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጢያንና ሌሎች ሰዎች ጥንታዊ የሆኑ የክርስትና ጽሑፎችን ጠራርገው ለማጥፋት የጣሩ ቢሆንም በሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቁርጥራጮችና በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው ቆይተዋል።
በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ቀደም ሲል ከተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል እንደ አርመንኛ፣ ኮፕቲክ፣ ግዕዝ፣ ጆርጂያኛ፣ ላቲንና ሲሪያክ ያሉ ጥንታዊ ቋንቋዎች ይገኙበታል።
ለትርጉም የሚሆነውን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፍ መወሰን
በእጅ የተጻፉት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ሐሳቡን የሚገልጹበት መንገድ አንዱ ከሌላው ይለያል። ታዲያ የመጀመሪያው ጽሑፍ የያዘውን ሐሳብ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ሁኔታውን ከሚከተለው ምሳሌ ጋር ማነጻጸር ይቻላል፦ አንድ አስተማሪ 100 ተማሪዎችን ከአንድ መጽሐፍ ላይ አንድ ምዕራፍ እንዲገለብጡ አዘዛቸው እንበል። ከጊዜ በኋላ ይህ ምዕራፍ ቢጠፋ መቶዎቹን ግልባጮች በማነጻጸር የመጀመሪያው ምዕራፍ የያዘው ሐሳብ ምን እንደነበር ማወቅ ይቻላል። እያንዳንዱ ተማሪ ሲገለብጥ የተወሰነ ስህተት ሊሠራ ቢችልም ሁሉም ተማሪዎች ተመሳሳይ ስህተት ይፈጽማሉ ብሎ ማሰብ ግን የማይመስል ነገር ነው። በተመሳሳይም ምሁራን በእጃቸው ያሉትን በሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቁርጥራጮችና ግልባጮች በማወዳደር ገልባጮቹ የሠሯቸውን ስህተቶች መለየትና የመጀመሪያው ጽሑፍ የያዘው ትክክለኛ ሐሳብ ምን እንደነበር መወሰን ይችላሉ።
“የእነዚህን ያህል በትክክል ተላልፈው ለእኛ የደረሱ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም”
የመጀመሪያው ጽሑፍ የያዘው ሐሳብ በትክክል ለእኛ ስለመተላለፉ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ዊልያም ሄንሪ ግሪን የተባሉት ምሁር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው አስተያየት ሲሰጡ “የእነዚህን ያህል በትክክል ተላልፈው ለእኛ የደረሱ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል። ፍሬድሪክ ብሩስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወይም በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የአዲስ ኪዳን ጽሑፎቻችንን
ትክክለኛነት የሚያሳዩት ማስረጃዎች፣ በጥንት ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጇቸው ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ካሏቸው ማስረጃዎች ጋር ሲወዳደሩ በጣም ብዙ ናቸው፤ ያም ሆኖ የእነዚህን ጽሑፎች [ማለትም በጥንት ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች] ትክክለኛነት በተመለከተ ጥያቄ ለማንሳት የሚደፍር ሰው የለም።” አክለውም “አዲስ ኪዳን የዓለማዊ ጽሑፎች ስብስብ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛነቱ ፈጽሞ ጥርጣሬ ውስጥ አይገባም ነበር” ብለዋል።የዕብራይስጡ ጽሑፍ፦ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (1953-1960) ለትርጉም ሥራው መሠረት ያደረገው በሩዶልፍ ኪተል የተዘጋጀውን ቢብሊያ ሂብራይካ ነበር። ከዚያ ወዲህ ተሻሽለው የተዘጋጁት የዕብራይስጡ ጽሑፍ እትሞች ማለትም ቢብሊያ ሂብራይካ ስቱትጋርቴንስያ እና ቢብሊያ ሂብራይካ ኩዊንታ በሙት ባሕር ጥቅልሎች እንዲሁም በሌሎች በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያስገኙትን ውጤት አካተዋል። ብዙ ምርምር ተደርጎባቸው የተዘጋጁት እነዚህ ጽሑፎች በዋናው ጽሑፋቸው ላይ የሌኒንግራድ ኮዴክስን የተጠቀሙ ሲሆን የሳምራውያን ፔንታቱክን፣ የሙት ባሕር ጥቅልሎችን፣ የግሪክኛውን ሰብዓ ሊቃናት፣ የአረማይኩን ታርገም፣ የላቲኑን ቩልጌትና የሲሪያኩን ፐሺታ ጨምሮ ከሌሎች ምንጮች ያገኟቸውን አማራጭ የሆኑ አገላለጾች በግርጌ ማስታወሻ ላይ አስፍረዋል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲዘጋጅ ቢብሊያ ሂብራይካ ስቱትጋርቴንስያ እና ቢብሊያ ሂብራይካ ኩዊንታ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ሆነው አገልግለዋል።
የግሪክኛው ጽሑፍ፦ በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ብሩክ ፎስ ዌስትኮት እና ፌንተን ጆን አንተኒ ሆርት የተባሉት ምሁራን የመጀመሪያው የግሪክኛ ጽሑፍ የያዘውን ሐሳብ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ይገልጻል ብለው ያሰቡትን የግሪክኛ ዋና ጽሑፍ ሲያዘጋጁ በእጃቸው ያሉትን ጥንታዊ ቅጂዎችና ቁርጥራጮች አመሳክረዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ እነሱ ያዘጋጁትን ይህን ዋና ጽሑፍ ለትርጉም ሥራው መሠረት አድርጎ ተጠቅሞበታል። በፓፒረስ ላይ የተጻፉና በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተዘጋጁ የሚታመኑ ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎችንም አመሳክሯል። ከዚያ ወዲህ በርካታ በፓፒረስ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች ተገኝተዋል። በተጨማሪም በኔስል እና በአላንድ እንዲሁም በተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት የተዘጋጁ ዋና ጽሑፎች በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች ያስገኟቸውን ውጤቶች አካተዋል። ከእነዚህ ግኝቶች መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ትርጉም ውስጥ ተካተዋል።
እነዚህን ዋና ጽሑፎች መሠረት በማድረግ እንደ ኪንግ ጀምስ ቨርዥን ባሉ ቆየት ያሉ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅሶች ከጊዜ በኋላ በተነሱ ገልባጮች የተጨመሩ እንጂ በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንዳልነበሩ ማረጋገጥ ተችሏል። ይሁን እንጂ የጥቅሶቹ ቁጥር አሰጣጥ ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ በስፋት ሲሠራበት ስለቆየ እነዚህን ቁጥሮች ማስቀረት በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ቁጥሮች ላይ ክፍተት ይፈጥራል። እነዚህ ጥቅሶች ማቴዎስ 17:21፣ 18:11፣ 23:14፣ ማርቆስ 7:16፣ 9:44, 46፣ 11:26፣ 15:28፣ ሉቃስ 17:36፣ 23:17፣ ዮሐንስ 5:4፣ የሐዋርያት ሥራ 8:37፣ 15:34፣ 24:7፣ 28:29 እና ሮም 16:24 ናቸው። በዚህ ትርጉም ውስጥ ጥቅሶቹ በተተዉበት ቦታ ላይ ጥቅሱ መውጣቱን የሚጠቁም የግርጌ ማስታወሻ ገብቷል።
በማርቆስ ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኘው ረጅም መደምደሚያ (ከቁጥር 9 እስከ 20) እና በማርቆስ ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኘው አጭር መደምደሚያ እንዲሁም በዮሐንስ 7:53 እስከ 8:11 ላይ ያለው ሐሳብ በእጅ በተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ እንደማይገኙ ግልጽ ነው። ስለሆነም እነዚህ ትክክለኛ ያልሆኑ ጥቅሶች በዚህ ትርጉም ውስጥ አልተካተቱም። c
ምሁራን የመጀመሪያው ጽሑፍ የያዘውን ሐሳብ በትክክል ያንጸባርቃሉ ብለው የተስማሙባቸውን አንዳንድ አገላለጾች ለማካተት ተሞክሯል። ለምሳሌ ያህል፣ በእጅ በተጻፉ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ ማቴዎስ 7:13 “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው” ይላል። ቀደም ብለው በተዘጋጁት የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ላይ “በር” የሚለው ሐሳብ አልተካተተም ነበር። ይሁንና በእጅ በተጻፉት ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ በተካሄደው ተጨማሪ ምርምር “በር” የሚለው ሐሳብ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ ተችሏል። በመሆኑም በዚህ ትርጉም ላይ እንዲገባ ተደርጓል። እንዲህ የመሰሉ በርካታ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። ይሁንና እነዚህ ማስተካከያዎች ጥቃቅን ስለሆኑ የአምላክ ቃል በሚያስተላልፈው መሠረታዊ ሐሳብ ላይ የሚያመጡት ለውጥ የለም።
a ከዚህ በኋላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በሚለው ስያሜ ብቻ ይጠራሉ።
b በእጅ የተጻፉትን ቅጂዎች መገልበጥ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት የተጻፉት በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ላይ ስለነበር ነው።
c እነዚህ ጥቅሶች ትክክለኛ አይደሉም የተባሉበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በ1984 የታተመውን ባለማጣቀሻ አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) የግርጌ ማስታወሻ መመልከት ይቻላል።