መቅድም
አምላክ ለሁላችንም ሐሳቡን በጽሑፍ የገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ስላስጻፈው አምላክ ለማወቅ ከፈለግን በውስጡ የሰፈረውን ሐሳብ ማጥናት ይኖርብናል። (ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይሖዋ አምላክ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ስለ ሰዎችና ስለሚኖሩባት ምድር ያለውን ዓላማ ገልጿል።–ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 21:3, 4
የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረ ሌላ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ፍቅር፣ ምሕረትና ርኅራኄ ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ያነሳሳናል። ሰዎች ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ እጅግ ከባድ የሆነን መከራ እንኳ ተቋቁመው እንዲጸኑ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ፍጹም ከሆነው የአምላክ ፈቃድ ውጭ እየተመላለሰ ያለው ይህ ዓለም የሚፈጽማቸውን መጥፎ ተግባራት ያጋልጣል።–መዝሙር 119:105፤ ዕብራውያን 4:12፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ተጽፎ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ3,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎምም ሆነ በስፋት በመሰራጨት ረገድ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው። ደግሞም ይህ መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ይላል።–ማቴዎስ 24:14
መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው መልእክት ክብደት አንጻር ግባችን በኩረ ጽሑፉ የያዘውን ሐሳብ በታማኝነት የሚያስተላልፍ ብቻ ሳይሆን ግልጽና ለማንበብ ቀላል የሆነም ትርጉም ማዘጋጀት ነው። በተጨማሪው መረጃ ላይ የሚገኙት “ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎች፣” “የዚህ ትርጉም ገጽታዎች” እና “መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ የቆየው እንዴት ነው?” የሚሉት ርዕሶች ይህ ትርጉም ሲዘጋጅ መሠረት ሆነው ያገለገሉትን መመሪያዎችና የዚህን ትርጉም አንዳንድ ገጽታዎች ያብራራሉ።
ይሖዋ አምላክን የሚወዱና የሚያመልኩ ሰዎች ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የማግኘት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) በመሆኑም አዲስ ዓለም ትርጉም በተቻለ መጠን በብዙ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ካለን ፍላጎት የተነሳ ይህ ትርጉም በአማርኛ ቋንቋ እንዲዘጋጅ አድርገናል። ውድ አንባቢ፣ አንተም ‘አምላክን ለመፈለግና ለማግኘት’ በምታደርገው ጥረት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲረዳህ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው።–የሐዋርያት ሥራ 17:27
የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ
ነሐሴ 2013