የዓለም ፍጻሜ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ምን ብሏል?
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲናገር ምድር ወይም የሰው ዘር በአጠቃላይ እንደሚጠፉ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ይህ ብልሹ ሥርዓትና የዚህ ሥርዓት ደጋፊዎች ስለሚጠፉበት ጊዜ መናገሩ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ ክፉ ሥርዓት መቼ እንደሚጠፋ ይናገራል?
ኢየሱስ የዓለም ፍጻሜን በተመለከተ የተናገራቸውን ሁለት ሐሳቦች እስቲ እንመልከት፦
“እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማቴዎስ 25:13
“ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማርቆስ 13:33
በመሆኑም በዚህ ሥርዓት ላይ ጥፋት የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም። ይሁንና ፍጻሜው የሚሆነው አምላክ ‘በወሰነው ጊዜ’ ላይ ነው፤ አምላክ ጥፋቱ የሚመጣበትን “ቀንና ሰዓት” አስቀድሞ ወስኗል። (ማቴዎስ 24:36) ታዲያ ያ ጊዜ መቅረቡን የምናውቅበት ምንም መንገድ የለም ማለት ነው? እንደዛ ማለት አይደለም። ኢየሱስ፣ የዓለም ፍጻሜ መቅረቡን የሚጠቁሙ ክንውኖችን ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል።
የዓለም ፍጻሜ መቅረቡን የሚጠቁመው ምልክት
“የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” መቅረቡን የሚጠቁሙት ክስተቶች እነዚህ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል።” (ማቴዎስ 24:3, 7) በተጨማሪም “ቸነፈር” ማለትም ተላላፊ በሽታዎች እንደሚከሰቱ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ኢየሱስ በትንቢት የተናገራቸው እነዚህ ክስተቶች ሲፈጸሙ እያየህ ነው?
አውዳሚ ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ የምድር ነውጥ እንዲሁም አስከፊ በሽታዎች በዛሬው ጊዜ ብዙ መከራ እያስከተሉ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ2004 በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ የቀሰቀሰው ሱናሚ ለ225,000 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ከአንድ ዓመት ብዙም ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ የ2.6 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ኢየሱስ እንዲህ ያሉት ክስተቶች የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡን እንደሚጠቁሙ ተናግሯል።
‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዓለም ፍጻሜ ከመከሰቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ያለውን ጊዜ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ ይጠራዋል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-5 በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሚከሰት ይናገራል። (“ የዓለም ፍጻሜ ከመከሰቱ ጥቂት ቀደም ብሎ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሰዎች ራስ ወዳድ፣ ስግብግብና ጨካኝ እየሆኑ እንደመጡ አስተውለሃል? እነዚህ ነገሮችም የዓለም ፍጻሜ በጣም እንደቀረበ ማስረጃ ይሆናሉ።
ታዲያ የመጨረሻዎቹ ቀናት የሚቆዩት እስከ መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ለጥቂት ጊዜ’ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን” ያጠፋል።—ራእይ 11:15-18፤ 12:12
ምድር ገነት የምትሆንበት ጊዜ ቀርቧል!
አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት አስቀድሞ ወስኗል። (ማቴዎስ 24:36) ደስ የሚለው ግን፣ አምላክ ‘ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ (2 ጴጥሮስ 3:9) የሰው ልጆች የእሱን መመሪያዎች ታዝዘው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዚህ ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈን እሱ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ስለሚፈልግ ነው፤ በዚያን ጊዜ ምድር ገነት ትሆናለች።
አምላክ ዓለም አቀፍ የትምህርት መርሃ ግብር አዘጋጅቷል፤ ይህን ያደረገው ሰዎች በእሱ መንግሥት በሚተዳደረው ዓለም ውስጥ ለመኖር ብቁ እንዲሆኑ ለመርዳት ነው። ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ምሥራች “በመላው ምድር” እንደሚሰበክ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች በመስበክና በማስተማር በ2019 ብቻ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ሰዓት አሳልፈዋል። ኢየሱስ፣ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ይህ የስብከት ዘመቻ በመላው ምድር እንደሚካሄድ ተናግሯል።
የሰው አገዛዝ የሚያከትምበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። ደስ የሚለው ነገር፣ በዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈህ አምላክ ቃል በገባልን ገነት ውስጥ መኖር ትችላለህ። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብህ በቀጣዩ ርዕስ ላይ ይብራራል።
ኢየሱስ ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” የተናገረው ትንቢት ተስፋ ይሰጠናል