መጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ ትችላለህ?
ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንዳየነው፣ በቅርቡ አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት ከነችግሮቹ ጠራርጎ ያጠፋዋል። ይህ እንደሚሆን ምንም አንጠራጠርም። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶልናል፦
“ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ።”—1 ዮሐንስ 2:17
ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች እንደሚኖሩም እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም ከላይ ያለው ጥቅስ እንዲህ የሚል ሐሳብም ይዟል፦
“የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”
ስለዚህ ከጥፋቱ ለመትረፍ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አለብን። የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በመጀመሪያ እሱን ማወቅ ያስፈልጋል።
አምላክን ‘በማወቅ’ ከመጪው ጥፋት መትረፍ ትችላለህ
ኢየሱስ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን . . . ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ከመጪው ጥፋት ለመትረፍና ለዘላለም ለመኖር አምላክን “ማወቅ” ያስፈልገናል። ይህ ሲባል እንዲሁ አምላክ እንዳለ አምኖ መቀበል ወይም ስለ እሱ አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ማለት ብቻ አይደለም። ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልጋል። ከአንድ ሰው ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው አብረን ጊዜ ስናሳልፍ ነው። ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትም እንዲሁ ማድረግ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መማራችን ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ይረዳናል፤ እስቲ ከእነዚህ እውነቶች አንዳንዶቹን እንመልከት።
የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ
በሕይወት ለመኖር ዘወትር መመገብ ያስፈልገናል። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም።”—ማቴዎስ 4:4
በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ቃል የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ይህን ቅዱስ መጽሐፍ ስታጠና አምላክ ባለፉት ዘመናት ለሰው ልጆች ምን እንዳደረገ፣ አሁን ምን እያደረገልን እንደሆነና ወደፊት ምን እንደሚያደርግልን ትረዳለህ።
አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ
የአምላክን መመሪያ መታዘዝ ብትፈልግም እሱ ስህተት ናቸው ያላቸውን ነገሮች መተው ከብዶሃል? ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? አምላክን በደንብ ማወቅህ በዚህ ረገድ በጣም ይጠቅምሃል።
እስቲ ሳኩራ * የተባለችን ሴት ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ይህች ሴት መጥፎ ሥነ ምግባር የነበራት ሴት ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስትጀምር አምላክ “ከፆታ ብልግና ሽሹ” የሚል ትእዛዝ እንደሰጠ ተረዳች። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ሳኩራ አምላክ ኃይል እንዲሰጣት በመጸለይ ይህን መጥፎ ልማዷን ማቆም ቻለች። ይሁንና አሁንም መጥፎ ልማዷ እንዳያገረሽባት መታገል ያስፈልጋታል። እንዲህ ብላለች፦ “መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሮዬ ሲመጡ በጸሎት ለይሖዋ በግልጽ እነግረዋለሁ፤ ምክንያቱም በራሴ ኃይል ታግዬ ማሸነፍ እንደማልችል አውቃለሁ። ጸሎት ያለውን ኃይል መመልከቴ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት እንዲጠናከር ረድቶኛል።” እንደ ሳኩራ ሁሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለዋል። አምላክ አካሄዳቸውን አስተካክለው እሱን በሚያስደስት መንገድ ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ኃይል ሰጥቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:13
አምላክን ይበልጥ እያወቅከው ስትሄድ እሱም አንተን ‘ያውቅሃል’፤ እንደ ወዳጁ አድርጎ ይመለከትሃል። (ገላትያ 4:9፤ መዝሙር 25:14) ይህ ደግሞ ከመጪው ጥፋት ለመትረፍና አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ያስችልሃል። ይሁንና መጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ምን ይመስላል? ቀጣዩ ርዕስ ይህን ያብራራል።