ይህ ዓለም ይጠፋል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ እንደሚናገር ታውቅ ይሆናል። (1 ዮሐንስ 2:17) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲል የሰው ዘር ስለሚጠፋበት ጊዜ መናገሩ ነው? ምድራችን ሕይወት አልባ እንደምትሆን ወይም ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ መናገሩ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዓለም ፍጻሜ ሁለቱንም ነገሮች እንደማያመለክት በግልጽ ይናገራል።
የማይጠፋው ምንድን ነው?
የሰው ዘር
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ ምድርን “መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አልፈጠራትም]።”—ኢሳይያስ 45:18
ምድራችን
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4
ይህ ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ምድር መቼም አትጠፋም፤ ምንጊዜም የሰው ልጆች መኖሪያ ሆና ትቀጥላለች። ታዲያ የዓለም ፍጻሜ ሲባል ምን ማለት ነው?
እስቲ ይህን አስብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጪውን የዓለም ፍጻሜ በኖኅ ዘመን ከተከሰተው ነገር ጋር ያመሳስለዋል። በዚያን ጊዜ ምድር ‘በዓመፅ ተሞልታ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:13) ኖኅ ግን ጻድቅ ሰው ነበር። ስለዚህ አምላክ ክፉ ሰዎችን በውኃ ሲያጠፋ ኖኅንና ቤተሰቡን አዳናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ያኔ ስለተከሰተው ጥፋት ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በእነዚህ ነገሮች ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው።” (2 ጴጥሮስ 3:6) ያኔ የነበረው ዓለም የጠፋው በዚህ መንገድ ነው። ሆኖም የጠፋው ምንድን ነው? ምድር ሳትሆን በምድር ላይ የሚኖሩ ክፉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲናገር ምድር እንደምትጠፋ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚጠፉት በምድር ላይ ያሉ ክፉ ሰዎችና እነሱ ያዋቀሩት ሥርዓት ነው።
የሚጠፋው ምንድን ነው?
ችግር እና ክፋት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም። የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11
ይህ ምን ማለት ነው? በኖኅ ዘመን የተከሰተው የጥፋት ውኃ፣ ክፋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ አላደረገም። ከጥፋት ውኃው በኋላ፣ ክፉ ሰዎች እንደገና የሌሎችን ሕይወት መራራ ማድረጋቸውን ቀጠሉ። በቅርቡ ግን አምላክ፣ ክፋትን ጠራርጎ ያስወግዳል። በመዝሙር መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው “ክፉዎች አይኖሩም።” አምላክ ክፋትን የሚያስወግደው እሱ ባቋቋመው መንግሥት አማካኝነት ነው፤ የአምላክ መንግሥት፣ ከሰማይ ሆኖ ጻድቅ ሰዎችን የሚያስተዳድር ዓለም አቀፍ መንግሥት ነው።
እስቲ ይህን አስብ፦ አሁን በዓለም ላይ ያሉ መንግሥታት፣ የአምላክን መንግሥት አገዛዝ ይቀበላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይቀበሉ ይናገራል። እንዲያውም የአምላክን መንግሥት በመቃወም የሞኝነት ድርጊት ይፈጽማሉ። (መዝሙር 2:2) ውጤቱስ ምን ይሆናል? የአምላክ መንግሥት፣ ሰዎች የሚያስተዳድሯቸውን መንግሥታት በሙሉ ያጠፋል፤ “እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” (ዳንኤል 2:44) ሆኖም ሰዎች ያቋቋሟቸው መንግሥታት መጥፋት ያለባቸው ለምንድን ነው?
የሰው አገዛዝ መጥፋት አለበት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የሰው ልጅ “አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።”—ኤርምያስ 10:23
ይህ ምን ማለት ነው? ሰው ሰውን እንዲያስተዳድር አልተፈጠረም። የሰው ልጆች ሌሎችን ለማስተዳደር ወይም ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያደርጉት ሙከራ የማይሳካላቸው ለዚህ ነው።
እስቲ ይህን አስብ፦ ብሪታኒካ አካደሚክ የተባለ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው የየትኛውም አገር መንግሥት ብቻውን በሚያደርገው ጥረት “የሰው ልጆች የጋራ ጠላት የሆኑትን ድህነትን፣ ረሃብን፣ በሽታን፣ የተፈጥሮ አደጋን፣ ጦርነትንና ዓመፅን ማስወገድ” የሚችል አይመስልም። የማመሣከሪያ ጽሑፉ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች . . . እነዚህን የሰው ልጆች ችግሮች በመዋጋት ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻለው ዓለም በአንድ መንግሥት ከተዳደረች ብቻ ነው ብለው ያምናሉ።” ሆኖም የዓለም መንግሥታት በሙሉ ተዋህደው አንድ መንግሥት ቢሆኑ እንኳ ዓለም የምትተዳደረው ፍጹም ባልሆኑ የሰው ልጆች እስከሆነ ድረስ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ማስወገድ አይችሉም። ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማስወገድ ችሎታ ያለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ሐሳብ እንደምንረዳው፣ ጥሩ ሰዎች የዓለምን ፍጻሜ ወይም አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትን ጊዜ የሚፈሩበት ምክንያት የለም። እንዲያውም በጉጉት የሚጠብቁት ጊዜ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ብልሹ አሮጌ ዓለም አምላክ በሚያመጣው አስደናቂ አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ ነው።
ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ቀጣዩ ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ይዟል።