አስተማማኝ የወደፊት ሕይወት—የሁሉም ሰው ምኞት
የወደፊት ሕይወትህ ምን ዓይነት እንዲሆን ትፈልጋለህ? አብዛኞቹ ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው ደስታ፣ ጤናና ሰላም የሞላበት እንዲሁም የተደላደለ ሕይወት ይመኛሉ፤ አንተም እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም።
ይሁንና በርካታ ሰዎች የሚመኙትን ዓይነት ሕይወት የማግኘታቸው ጉዳይ ያጠራጥራቸዋል። እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሉ ድንገተኛና ያልተጠበቁ ክስተቶች የማኅበረሰቡን ኑሮ ሲያመሰቃቅሉ፣ ኢኮኖሚውን ሲያናጉና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሲጥሉ ተመልከተዋል። በዚህም ምክንያት አስተማማኝ የወደፊት ሕይወት የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ይህ ሁኔታ የፈጠረው ግራ መጋባት ሰዎች አስተማማኝ ሕይወት ይሰጡናል ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች ሁሉ ወደመፈለግ ዞር እንዲሉ አድርጓቸዋል። አንዳንዶች እንደ ዕድል ወይም ዕጣ ፋንታ ያሉ የማይታዩ ኃይሎች ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠሩት ይፈቅዳሉ። ብዙዎች ደግሞ ትምህርት እና ሀብት አስተማማኝ ሕይወት ለማግኘት እንደሚረዷቸው በማሰብ እነዚህን ነገሮች ያሳድዳሉ። አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት የሚያስፈልገው ጥሩ ሰው መሆን ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ።
እነዚህ አማራጮች የምትፈልገውን ዓይነት ሕይወት ለማግኘት የሚረዱህ ይመስልሃል? መልሱን ለማግኘት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመር ያስፈልግሃል፦
የወደፊት ሕይወትህ የተመካው በምን ላይ ነው?
ትምህርትና ገንዘብ ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳሉ?
ጥሩ ሰው መሆንህ ብቻ የወደፊት ሕይወትህን አስተማማኝ ያደርገዋል?
የወደፊት ሕይወትህን በተመለከተ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
ይህ የመጠበቂያ ግንብ እትም ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።