አምላክ ከዚህ በፊት ምን አድርጓል?
አንድን ሰው በደንብ ለማወቅ ይህ ሰው ምን ነገሮችን እንዳከናወነና የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደተወጣ ማወቅህ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም አምላክን በደንብ ለማወቅ ከዚህ በፊት ስላደረጋቸው ነገሮች ማወቅ ያስፈልግሃል። አምላክ በቀድሞ ዘመን ያደረጋቸው ነገሮች በአሁኑ ጊዜ እየጠቀሙን ያሉት እንዴት እንደሆነና ወደፊትም ምን ያህል እንደሚጠቅሙን ስታውቅ መገረምህ አይቀርም።
አምላክ ለእኛ ሲል ብዙ መልካም ነገሮችን ፈጥሯል
ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ነው፤ ደግሞም “የማይታዩት ባሕርያቱ . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) “ምድርን በኃይሉ የሠራው፣ ፍሬያማ የሆነችውን መሬት በጥበቡ የመሠረተውና ሰማያትን በማስተዋሉ የዘረጋው እሱ ነው።” (ኤርምያስ 10:12) በተጨማሪም አስደናቂ የሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ አምላክ ለእኛ ትልቅ ግምት እንደሚሰጠን ያሳያሉ።
ይሖዋ ሰዎችን “በራሱ መልክ” መፍጠሩ ሕይወታችንን ምን ያህል አስደሳች እንዳደረገው ለማሰብ ሞክር። (ዘፍጥረት 1:27) አምላክ ወደር የለሽ ባሕርያቱን በጥቂቱም ቢሆን ማንጸባረቅ እንድንችል አድርጎ ፈጥሮናል። መንፈሳዊ ነገሮችን የመረዳት ማለትም የእሱን አመለካከትና መሥፈርት የመገንዘብ ችሎታ ሰጥቶናል። በእሱ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት ስናደርግ ይበልጥ ደስተኛ መሆንና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት እንችላለን። በተጨማሪም አምላክ ከእሱ ጋር ዝምድና የመመሥረት ችሎታ ሰጥቶናል።
ምድራችን የተሠራችበት መንገድ አምላክ ለእኛ ያለውን ስሜት ያንጸባርቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “[አምላክ] ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና [ልባችንን] በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።” (የሐዋርያት ሥራ 14:17) አምላክ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉንን ነገሮች ብቻ በመፍጠር አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ሕይወታችንን አስደሳች የሚያደርጉ ነገሮችን በዓይነትና በብዛት ፈጥሮልናል። ሆኖም እነዚህ አምላክ ለእኛ ሲል ካደረጋቸው በርካታ ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።
ይሖዋ ምድርን የፈጠራት የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩባት አስቦ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ምድርን ለሰው ልጆች መዝሙር 115:16፤ ኢሳይያስ 45:18) ለመሆኑ አምላክ ምድርን የፈጠራት እነማን እንዲኖሩባት ነው? የሚኖሩባትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው? “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
እንደሰጣት’ እንዲሁም “መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [እንዳልፈጠራት]” ይገልጻል። (በዚህ መሠረት ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ምድርን ‘እንዲያለሙና እንዲንከባከቡ’ ገነት ውስጥ አስቀመጣቸው። (ዘፍጥረት 2:8, 15) አምላክ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” በማለት ሁለት አስደሳች ኃላፊነቶች ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:28) በመሆኑም አዳምና ሔዋን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር። የሚያሳዝነው ግን፣ አምላክን ላለመታዘዝ በመምረጣቸው ‘ምድርን ከሚወርሱት ጻድቃን’ መካከል የመሆን መብታቸውን አጡ። ይሁን እንጂ የእነሱ አለመታዘዝ ይሖዋ ለእኛም ሆነ ለምድር ያለውን ዓላማ እንዲቀይር አላደረገውም፤ ስለዚህ ጉዳይ በኋላ ላይ በሰፊው እንመለከታለን። ከዚያ በፊት ግን አምላክ ያደረገውን ሌላ ነገር እንመልከት።
አምላክ በጽሑፍ የሰፈረ ቃሉን ሰጥቶናል
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ቃል ተብሎም ይጠራል። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ለምንድን ነው? በዋነኝነት ስለ እሱ መማር እንድንችል ነው። (ምሳሌ 2:1-5) እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን አስመልክቶ ለሚፈጠርብን ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ አይሰጥም፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ የሚችል መጽሐፍ ሊኖር አይችልም። (መክብብ 3:11) ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ሐሳብ በሙሉ አምላክን ይበልጥ ማወቅ እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ ሌሎችን ስለያዘበት መንገድ ከሚገልጹት ዘገባዎች ስለ ባሕርያቱ ማወቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እሱ ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሚወድና ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሚጠላ እንረዳለን። (መዝሙር 15:1-5) በተጨማሪም ከአምልኮ፣ ከሥነ ምግባርና ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን አመለካከት እንዳለው እንገነዘባለን። እንዲሁም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው ነገሮች የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የይሖዋን ባሕርያት ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሕያው አድርገው ያቀርቡልናል።—ዮሐንስ 14:9
ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠበት ሌላው ምክንያት ሰዎች አስደሳችና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያውቁ ለመርዳት ነው። ይሖዋ በቤተሰብ ሕይወታችን ደስተኛ መሆን፣ ባለን ረክተን መኖርና ጭንቀትን መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ገልጾልናል። እንዲሁም በዚህ መጽሔት ውስጥ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለምናነሳቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ይዟል፤ ከእነዚህ መካከል ‘መከራ የበዛው ለምንድን ነው?’ እና ‘የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል?’ የሚሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመጀመሪያ ዓላማውን ለማስፈጸም ምን እርምጃ እንደወሰደ ያብራራል።
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ከመለኮታዊ እርዳታ ውጭ ሊጻፍ የማይችል ልዩ መጽሐፍ ነው፤ ይህን የሚያሳዩ ሌሎች በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ እንችላለን። አርባ የሚያህሉ ሰዎች በ1,600 ዓመታት ርዝማኔ ውስጥ የጻፉት ቢሆንም መጽሐፉን ያጻፈው አምላክ ስለሆነ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ አንድ ጭብጥ ሊኖረው ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቱ ሳይቀየር እስከ ዘመናችን ደርሷል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን በማመሣከር ይህን ማረጋገጥ ተችሏል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይተረጎም፣ እንዳይሰራጭና እንዳይነበብ የተሰነዘረበትን ጥቃት በሙሉ ተቋቁሟል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በስፋት በመሰራጨትና በመተርጎም ረገድ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ለመሆን በቅቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ መቆየቱ ‘የአምላካችን ቃል ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር’ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ኢሳይያስ 40:8
አምላክ ዓላማው እንደሚፈጸም ዋስትና ሰጥቷል
አምላክ ካደረጋቸው ነገሮች ውስጥ የሚካተተው ሌላው ነገር፣ ለእኛ ያለው ዓላማ መፈጸሙ እንደማይቀር ዋስትና ለመስጠት ሲል ያደረገው ልዩ ዝግጅት ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ይሁን እንጂ አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት መሥራቱ እሱ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚወለዱ ልጆቹም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን እንዲያጡ አድርጓል። “ስለሆነም በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት የአምላክ ዓላማ እንቅፋት ገጠመው። ታዲያ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን?
ይሖዋ እርምጃ የወሰደው ከባሕርያቱ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። ፍትሑ አዳምንና ሔዋንን ለጥፋታቸው ተጠያቂ እንዲያደርጋቸው አነሳስቶታል። ፍቅሩ ደግሞ ወደፊት የሚወለዱት ዘፍጥረት 3:15) የሰው ልጆች በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት የሚችሉበት ዝግጅት አድርጓል። ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
ልጆቻቸው መዳን የሚያገኙበት ዝግጅት እንዲያደርግ ገፋፍቶታል። በተጨማሪም የተነሳው ዓመፅ እልባት የሚያገኝበትን መንገድ ለመወሰን ጥበቡን የተጠቀመ ሲሆን መፍትሔው ምን እንደሆነ ወዲያውኑ ተናግሯል። (ይሖዋ የአዳም ዓመፅ ካስከተለው ችግር የሰው ልጆችን ነፃ ለማውጣት ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው፤ ኢየሱስ የመጣው ሕይወት የሚገኝበትን መንገድ ለማስተማርና “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” ነው። a (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 14:6) ኢየሱስ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ስለነበር ቤዛ መሆን ይችላል። ሆኖም ከአዳም በተለየ መልኩ እስከ ሞት ድረስ ሙሉ በሙሉ ታዛዥ ሆኗል። ኢየሱስ መሞት የሚገባው ሰው ስላልነበር ይሖዋ ከሞት ካስነሳው በኋላ በሰማይ እንዲኖር አድርጓል። በመሆኑም ኢየሱስ አዳም ያላደረገውን ነገር ማድረግ ማለትም ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት መስጠት ይችላል። “ምክንያቱም በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮም 5:19) አምላክ የሰው ዘር በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖር የገባውን ቃል በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይፈጽማል።
ይሖዋ የአዳም ዓመፅ ያስከተላቸውን ችግሮች ለመፍታት ካደረገው ዝግጅት ስለ እሱ ብዙ ነገር እንማራለን። ይሖዋ የጀመረውን ዳር እንዳያደርስ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እንመለከታለን፤ ቃሉ ‘በእርግጥ ይፈጸማል።’ (ኢሳይያስ 55:11) በተጨማሪም ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እንገነዘባለን። “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።”—1 ዮሐንስ 4:9, 10
አምላክ “ለገዛ ልጁ እንኳ [ሳይሳሳ] ለእኛ ለሁላችን አሳልፎ የሰጠው” መሆኑ ቃል የገባልንን ‘ሌሎች ነገሮች ሁሉ በደግነት እንደሚሰጠን’ ማረጋገጫ ይሆነናል። (ሮም 8:32) አምላክ ወደፊት ምን ሊያደርግልን ቃል ገብቷል? የዚህን ጥያቄ መልስ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
አምላክ ከዚህ በፊት ምን አድርጓል? ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ስለ እሱ መማር እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ቤዛውን ያዘጋጀልን ሲሆን ይህም ዓላማው እንደሚፈጸም ዋስትና ይሆነናል
a ስለ ቤዛው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 27 ተመልከት። መጽሐፉ www.dan124.com/am ላይም ይገኛል።