በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ ስለ “ቡችሎች” የተናገረው ምሳሌ ሌሎችን ዝቅ የሚያደርግ ነበር?

ቡችላ ያቀፈች ሕፃን፣ የግሪካውያን ወይም የሮማውያን ቅርጽ (በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መካከል)

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከእስራኤል ክልል ውጭ በምትገኘውና የሮም አውራጃ በሆነችው በሶርያ ሳለ አንዲት ግሪካዊት ሴት እንዲረዳት ጠይቃው ነበር። ኢየሱስ የሰጣት ምላሽ፣ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን ‘ከቡችሎች’ ጋር የሚያመሳስል ምሳሌ የያዘ ነበር። በሙሴ ሕግ መሠረት ደግሞ ውሾች እንደ ርኩስ እንስሳት ይቆጠራሉ። (ዘሌዋውያን 11:27) ታዲያ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ግሪካዊቷን ሴትና አይሁዳውያን ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን ዝቅ ለማድረግ ብሎ ነው?

በጭራሽ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገለጸው በዚያን ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጠው አይሁዳውያንን ለመርዳት ነበር። ስለዚህ ለግሪካዊቷ ሴት ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ አይደለም” አላት። (ማቴዎስ 15:21-26፤ ማርቆስ 7:26) ብዙውን ጊዜ በግሪካውያንና በሮማውያን ዘንድ ውሻ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ የሚያኖሩትና ከልጆች ጋር እንዲጫወት የሚፈቅዱለት ተወዳጅ እንስሳ ነበር። በመሆኑም የኢየሱስ አድማጮች “ቡችሎች” የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሯቸው የመጣው ተወዳጅ የሆነ እንስሳ ሊሆን ይችላል። ግሪካዊቷ ሴት ኢየሱስ ያለውን ከሰማች በኋላ “አዎ ጌታ ሆይ፣ ግን እኮ ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት መልሳለታለች። ኢየሱስ የሴትየዋን እምነት ያደነቀ ሲሆን ልጇንም ፈውሶላታል።—ማቴዎስ 15:27, 28

ሐዋርያው ጳውሎስ የባሕር ጉዞው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ያቀረበው ሐሳብ ትክክለኛ ነበር?

የአንድ ትልቅ የጭነት መርከብ ቅርጽ (አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.)

ጳውሎስ ወደ ጣሊያን ለመሄድ የተሳፈረበት መርከብ ከኃይለኛ አውሎ ነፋስ ጋር እየታገለ ነበር። መርከቡ በአንድ ወደብ ላይ ቆሞ እያለ ሐዋርያው ጉዟቸውን ከመቀጠል ይልቅ ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉት ሐሳብ አቀረበ። (የሐዋርያት ሥራ 27:9-12) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ምክር የሰጠው ለምንድን ነው?

በጥንት ዘመን የነበሩ መርከበኞች በክረምት ወራት በሜድትራንያን ባሕር ላይ መጓዝ አደገኛ እንደሆነ አሳምረው ያውቁ ነበር። ከኅዳር አጋማሽ እስከ መጋቢት አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ በዚህ ባሕር ላይ የመርከብ ጉዞ አይደረግም ነበር። ጳውሎስ ጉዞ እንዳያደርጉ ሐሳብ ያቀረበው ግን በመስከረም ወይም በጥቅምት መካከል ባለው ጊዜ ነበር። ሮማዊው ጸሐፊ ቬጀቲየስ (አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.) በጻፈው ኤፒቶም ኦቭ ሚሊታሪ ሳይንስ ላይ በሜድትራንያን ባሕር ላይ የሚደረግ ጉዞን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አንዳንድ ወራት ለጉዞ በጣም ተስማሚ ናቸው፤ አንዳንዶቹ አስተማማኝ አይደሉም፤ በተቀሩት ወራት ደግሞ የባሕር ጉዞ ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም።” ቬጀቲየስ ከግንቦት 27 እስከ መስከረም 14 ባለው ጊዜ በመርከብ መጓዝ የማያሰጋ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ከመስከረም 15 እስከ ኅዳር 11 እና ከመጋቢት 11 እስከ ግንቦት 26 ያሉት ወቅቶች ግን ለጉዞ አስተማማኝ እንዳልሆኑ ወይም አደገኛ እንደሆኑ ተናግሯል። የጉዞ ልምድ ያለው ጳውሎስ ይህን እውነታ በሚገባ ያውቅ እንደነበር አያጠራጥርም። የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤትም ቢሆኑ እነዚህን ነገሮች ሳያውቁ አይቀሩም፤ ሆኖም የጳውሎስን ምክር መቀበል አልፈለጉም። ምክሩን ችላ ብለው ጉዟቸውን በመቀጠላቸውም መርከቡ አደጋ ደርሶበታል።—የሐዋርያት ሥራ 27:13-44