ማንኛውም ነገር ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ
“ማንኛውም ሰው ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ።”—ቆላ. 2:18
1, 2. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች ምን ዓይነት ሽልማት ለማግኘት በጉጉት ይጠባበቃሉ? (ለ) ዓይናችን በሽልማታችን ላይ እንዲያተኩር ምን ሊረዳን ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
በዛሬው ጊዜ ያሉ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “አምላክ . . . የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” የማግኘት ግሩም ተስፋ አላቸው። (ፊልጵ. 3:14) ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚነግሡበትን እንዲሁም የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ለመርዳት ከእሱ ጋር ሆነው የሚሠሩበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ራእይ 20:6) አምላክ ለእነዚህ ክርስቲያኖች የሰጣቸው ተስፋ ምንኛ አስደናቂ ነው! ሌሎች በጎች የተባሉት ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚህ የተለየ ተስፋ አላቸው። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው!—2 ጴጥ. 3:13
2 ጳውሎስ እንደ እሱ ቅቡዓን የሆኑት ክርስቲያኖች ታማኝ ሆነው እንዲኖሩና ሽልማቱን ማግኘት እንዲችሉ ለመርዳት ሲል “አእምሯችሁ . . . ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ቆላ. 3:2) እነዚህ ክርስቲያኖች ውድ በሆነው ሰማያዊ ውርሻቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ነበረባቸው። (ቆላ. 1:4, 5) በእርግጥም ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ፣ ይሖዋ ቃል በገባላቸው በረከቶች ላይ ማሰላሰላቸው ዓይናቸው በሽልማታቸው ላይ እንዲያተኩር ይረዳቸዋል።—1 ቆሮ. 9:24
3. ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ስለ የትኞቹ አደገኛ ሁኔታዎች አስጠንቅቋቸዋል?
ቆላ. 2:16-18) ጳውሎስ የጠቀሳቸው አንዳንድ አደገኛ ሁኔታዎች በዘመናችንም ሊያጋጥሙንና ሽልማታችንን እንድናጣ ሊያደርጉን የሚችሉ ናቸው። ለአብነት ያህል፣ ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በብልግና ምኞቶች ላለመሸነፍ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አብራርቷል። እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የሰጠው ምክር በዛሬው ጊዜ ለምንገኝ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከተካተቱት ፍቅር የተንጸባረቀባቸው ማሳሰቢያዎች አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
3 በተጨማሪም ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ሽልማታቸውን እንዲያጡ ሊያደርጓቸው ስለሚችሉ ነገሮች አስጠንቅቋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቶስ በማመን ሳይሆን የሙሴን ሕግ በመጠበቅ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከሚሞክሩ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች እንዲርቁ በቆላስይስ ጉባኤ ላሉት ወንድሞች ጽፎላቸዋል። (የብልግና ምኞቶችን ግደሉ
4. የብልግና ምኞቶች ሽልማታችንን ሊያሳጡን የሚችሉት ለምንድን ነው?
4 ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹን ከፊታቸው ስለተዘረጋው አስደናቂ ተስፋ ካስታወሳቸው በኋላ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣ መጥፎ ፍላጎትና . . . ስግብግብነት ናቸው።” (ቆላ. 3:5) የብልግና ምኞቶች ከፍተኛ የማታለል ኃይል ያላቸው ሲሆን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንዲሁም የወደፊት ተስፋችንን እንድናጣ ሊያደርጉን ይችላሉ። በብልግና ምኞቶች የተሸነፈ አንድ ወንድም ወደ ጉባኤ ከተመለሰ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ድርጊቱን እንድፈጽም የገፋፋኝ ስሜት በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ምን እንዳደረግኩ እንኳ የታወቀኝ የፆታ ብልግና ከፈጸምኩ በኋላ ነው።”
5. የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንድንጥስ በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንድንጥስ በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን የተለየ ጥንቃቄ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የሚጠናኑ ክርስቲያኖች እጅ ለእጅ መያያዝን፣ መሳሳምን ወይም ሰዎች በሌሉበት አብሮ መሆንን በተመለከተ፣ ገና መጠናናት ሲጀምሩ ግልጽ የሆኑ ገደቦችን ማስቀመጣቸው ጥበብ ነው። (ምሳሌ 22:3) አንድ ክርስቲያን ለሥራ ወደ ሌላ አካባቢ በሚሄድበት ወይም ከተቃራኒ ፆታ ጋር በሚሠራበት ወቅትም የሥነ ምግባር ፈተና ሊያጋጥመው ይችላል። (ምሳሌ 2:10-12, 16) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን መናገርህ፣ ሥርዓታማ ምግባር ማሳየትህ እንዲሁም ማሽኮርመም ከባድ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም በምናዝንበት ወይም ብቸኝነት በሚሰማን ጊዜ በሥነ ምግባር ፈተና ላለመውደቅ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። እንዲህ ባሉት ወቅቶች፣ እንደምንወደድ እንዲሰማን የሚያደርገን ሰው እንፈልግ ይሆናል። ስሜታችንን የሚረዳልንና የሚያስብልን ሰው በጣም ከመፈለጋችን የተነሳ ትኩረት የሚሰጠንን ማንኛውንም ሰው ለመቅረብ እንፈተን ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ የይሖዋንና የሕዝቦቹን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ፤ ይህን ማድረግህ ሽልማትህን ከሚያሳጣ ነገር ለመራቅ ይረዳሃል።—መዝሙር 34:18ን እና ምሳሌ 13:20ን አንብብ።
6. ከመዝናኛ ምርጫችን ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
6 የብልግና ምኞቶችን ለመግደል፣ የሥነ ምግባር ብልግናን ከሚያስፋፉ መዝናኛዎች መራቅ ይኖርብናል። በዛሬው ጊዜ ባሉት በአብዛኞቹ መዝናኛዎች ላይ የሚቀርቡት ነገሮች ጥንት በሰዶምና በገሞራ ከነበረው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላሉ። (ይሁዳ 7) መዝናኛ የሚያዘጋጁት ሰዎች፣ የፆታ ብልግናን ሁሉም ሰው የሚፈጽመው ነገር እንደሆነና የሚያስከትለው ምንም ዓይነት መዘዝ እንደሌለ አድርገው በማቅረብ የራሳቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ለማስፋፋት ይሞክራሉ። ስለዚህ ሁልጊዜ ንቁዎች መሆናችን አስፈላጊ ነው፤ ዓለም በሚያቀርበው በማንኛውም ነገር ከመዝናናት ይልቅ መራጮች ከሆንን ለአደጋ አንጋለጥም። ዓይናችን በሕይወት ሽልማት ላይ እንዳያተኩር እንቅፋት ሊሆኑብን ከሚችሉ መዝናኛዎች መራቅ ይኖርብናል።—ምሳሌ 4:23
‘ፍቅርን እና ደግነትን ልበሱ’
7. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ?
7 የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን በረከት እንደሆነ ሁላችንም እንስማማለን። በስብሰባዎቻችን ላይ የአምላክን ቃል ማጥናታችን እንዲሁም እርስ በርስ በደግነትና በፍቅር መደጋገፋችን ዓይናችን በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በጉባኤው አባላት መካከል ውጥረት እንዲነግሥ ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮችን ካልፈታናቸው በወንድሞቻችን ላይ ቂም ወደ መያዝ ሊመሩን ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 3:8, 9ን አንብብ።
8, 9. (ሀ) ሽልማቱን ለማግኘት የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? (ለ) አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቅር ቢያሰኘን ሰላም ለመፍጠር ምን ሊረዳን ይችላል?
8 በሌሎች ላይ ቂም መያዛችን ሽልማታችንን ሊያሳጣን ይችላል፤ ታዲያ ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ እንችላለን? ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፦ “የአምላክ ምርጦች፣ ቅዱሳንና የተወደዳችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።”—ቆላ. 3:12-14
9 ፍቅርና ደግነት እርስ በርስ ይቅር እንድንባባል ሊረዱን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራችን የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ስሜታችንን ጎዳው እንበል፤ በዚህ ወቅት እኛ ራሳችን ደግነት የጎደለው ነገር የተናገርንባቸውን ወይም ያደረግንባቸውን ጊዜያት ለማስታወስ መሞከራችን ጠቃሚ ነው። በእነዚያ ወቅቶች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስህተታችንን ይቅር በማለት ፍቅርና ደግነት ስላሳዩን አመስጋኞች አይደለንም? (መክብብ 7:21, 22ን አንብብ።) በተለይ ደግሞ ክርስቶስ፣ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ ላሳየው ደግነት አመስጋኞች ነን። (ቆላ. 3:15) ሁላችንም የምንወደውና የምናመልከው አምላክ አንድ ነው፤ አንድ ዓይነት መልእክት እንሰብካለን፤ የሚያጋጥሙን ብዙዎቹ ችግሮችም አንድ ዓይነት ናቸው። እርስ በርስ ይቅር በመባባል ደግነትና ፍቅር ማሳየታችን ለክርስቲያናዊ አንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ እንዲሁም ዓይናችን በሕይወት ሽልማት ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል።
10, 11. (ሀ) ቅናት አደገኛ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ቅናት ሽልማታችንን እንዳያሳጣን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ቅናት ሽልማታችንን ሊያሳጣን ይችላል። ለምሳሌ ቃየን በወንድሙ በአቤል በመቅናቱ የወንድሙን ሕይወት አጥፍቷል። ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን በሙሴ መቅናታቸው እሱን እንዲቃወሙ አድርጓቸዋል። ንጉሥ ሳኦልም ዳዊት ባገኘው ስኬት ስለቀና እሱን ለመግደል ተነሳስቷል። የአምላክ ቃል “ቅናትና ጠበኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ” የሚል መሆኑ ምንም አያስገርምም።—ያዕ. 3:16
11 ልባችን በፍቅርና በደግነት እንዲሞላ ካደረግን በሌሎች ላይ ቶሎ ቅናት አያድርብንም። የአምላክ ቃል “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4) ቅናት በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ለመከላከል የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ይጠቅመናል፤ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የአንድ አካል ክፍሎች እንደሆንን ይኸውም ሁላችንም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደሆንን ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን “አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ” ከሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ራሳችንን በሌሎች ቦታ እንድናስቀምጥ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 12:16-18, 26) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ሌሎች ባገኙት በረከት ከመቅናት ይልቅ አብረናቸው እንደሰታለን። የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነውን የዮናታንን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ንጉሥ ሆኖ በመቀባቱ ዮናታን ቅናት አላደረበትም። እንዲያውም ዳዊትን አበረታቶታል። (1 ሳሙ. 23:16-18) እኛስ እንደ ዮናታን ደግና አፍቃሪ መሆን እንችላለን?
ከቤተሰባችሁ ጋር ሆናችሁ ሽልማቱን ለማግኘት ጣሩ
12. ከቤተሰባችን ጋር ሆነን ሽልማቱን ለማግኘት የሚረዳን የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ነው?
12 የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ የሚያደርጉ ቤተሰቦች፣ ሰላምና ደስታ የሰፈነበት ሕይወት መምራት እንዲሁም ሽልማቱን ማግኘት ይችላሉ። ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ቤተሰብን አስመልክቶ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “ሚስቶች ሆይ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ሊያደርጉት የሚገባ ስለሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው። ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና። አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።” (ቆላ. 3:18-21) በዛሬው ጊዜ ያሉ ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆችም ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ እንደሚጠቀሙ ጥርጥር የለውም።
13. አንዲት ክርስቲያን የማያምን ባሏን ወደ እውነት እንዲመጣ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?
13 ባለቤትሽ የማያምን ቢሆንና በተገቢው መንገድ እንደማይዝሽ ቢሰማሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ተበሳጭተሽ ከእሱ ጋር ብትጨቃጨቂ ሁኔታው ሊሻሻል ይችላል? በዚህ መንገድ፣ የምትፈልጊውን ነገር እንዲፈጽም ማድረግ ብትችዪ እንኳ ባለቤትሽ በአንቺ ምግባር ተማርኮ ወደ እውነት የመምጣቱ አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የባልሽን የራስነት ሥልጣን ብታከብሪ፣ በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍንና ይሖዋ እንዲከበር የበኩልሽን 1 ጴጥሮስ 3:1, 2ን አንብብ።
አስተዋጽኦ ታበረክቻለሽ፤ አልፎ ተርፎም ባለቤትሽ በአንቺ ምግባር ተማርኮ እውነተኛውን አምልኮ ሊቀበልና ሽልማቱን አብራችሁ ልታገኙ ትችላላችሁ።—14. አንድ ክርስቲያን ባል የማታምን ሚስቱ ባታከብረው ምን ማድረግ ይኖርበታል?
14 ባለቤትህ የማታምን ብትሆንና እንደማታከብርህ ቢሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በእሷ ላይ በመጮኽ የቤቱ አዛዥ ማን እንደሆነ ለማሳየት ብትሞክር አንተን ለማክበር የምትነሳሳ ይመስልሃል? በጭራሽ! አምላክ የራስነት ሥልጣንህን ልክ እንደ ኢየሱስ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድትጠቀምበት ይጠብቅብሃል። (ኤፌ. 5:23) የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበት በፍቅርና በትዕግሥት ነው። (ሉቃስ 9:46-48) አንድ ባል የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል ከሆነ ሚስቱ በእሱ ምግባር ተማርካ እውነተኛውን አምልኮ እንድትቀበል ሊረዳት ይችላል።
15. አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን እንደሚወድ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
15 ባሎች “ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (ቆላ. 3:19) አፍቃሪ የሆነ ባል፣ የሚስቱን ሐሳብ በማዳመጥና የእሷን ሐሳብ ከፍ አድርጎ በመመልከት ሚስቱን እንደሚያከብር ያሳያል። (1 ጴጥ. 3:7) ሚስቱ ያለችውን ሁሉ ይፈጽማል ማለት ባይሆንም ውሳኔ ከማድረጉ በፊት እሷን ማማከሩ የተሻለ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይረዳዋል። (ምሳሌ 15:22) አፍቃሪ የሆነ ባል፣ ሚስቱ እንድታከብረው ከመጠየቅ ይልቅ በራሷ ተነሳስታ እንድታከብረው በሚያደርግ መንገድ ይይዛታል። አንድ ባል፣ ሚስቱንና ልጆቹን የሚወድ ከሆነ ቤተሰቡ ይሖዋን በደስታ ያገለግላል፤ እንዲሁም የሕይወትን ሽልማት አብረው ይወርሳሉ።
ልጆች—ማንኛውም ነገር ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ
16, 17. ወላጆችህ አንተን በሚይዙበት መንገድ እንዳትማረር ምን ሊረዳህ ይችላል?
16 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ከሆንክ ወላጆችህ ስሜትህን እንደማይረዱልህ ወይም በጣም ጥብቅ እንደሆኑብህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም በወላጆችህ በጣም ከመበሳጨትህ የተነሳ፣ ይሖዋን ማገልገልህን ብትተው የተሻለ እንደሚሆን ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእነሱ ተማርረህ ይሖዋን ማገልገልህን ብታቆም ይዋል ይደር እንጂ፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወላጆችህንና የጉባኤህን አባላት ያህል ከልቡ ስለ አንተ የሚያስብ ሰው እንደሌለ መገንዘብህ አይቀርም።
17 እስቲ አስበው፦ ወላጆችህ ምንም ዓይነት እርማት የማይሰጡህ ቢሆን በእርግጥ እንደሚወዱህ ይሰማህ ነበር? (ዕብ. 12:8) ምናልባትም ያስከፋህ ወላጆችህ አንተን የሚገሥጹበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ምክንያታቸውን ለማስተዋል ሞክር። ነገሩን በሰከነ መንፈስ ለማሰብና ወላጆችህ ሲገሥጹህ ከመጠን በላይ ላለመበሳጨት ጥረት አድርግ። የአምላክ ቃል “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:27) እርማት ሲሰጥህ ተግሣጹ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በተረጋጋ መንፈስ ምክሩን ተቀብለህ በተግባር አውለው፤ ይህም በሳል ሰው ለመሆን ጥረት እንደምታደርግ የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 1:8) ይሖዋን ከልብ የሚወዱ ወላጆች ያሉህ መሆኑ ትልቅ በረከት እንደሆነ ፈጽሞ አትዘንጋ። የወላጆችህ ፍላጎት የሕይወትን ሽልማት እንድታገኝ አንተን መርዳት ነው።
18. ዓይንህ በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?
18 ሽልማታችን በሰማይ የማይሞት ሕይወት ማግኘትም ይሁን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ ከፊታችን የተዘረጋው ተስፋ አስደናቂ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ይህን ተስፋ የሰጠን ፈጣሪያችን በመሆኑ ቃሉን እንደሚፈጽም አንጠራጠርም። ገነት የምትሆነው ምድር ‘በይሖዋ እውቀት እንደምትሞላ’ አምላክ ተናግሯል። (ኢሳ. 11:9) በዚያ ወቅት በምድር ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ ከአምላክ የተማረ ይሆናል። ይህ ከፍተኛ ጥረት ልናደርግለት የሚገባ ሽልማት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እንግዲያው ይሖዋ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ፤ እንዲሁም ማንኛውም ነገር ሽልማቱን እንዲያሳጣህ አትፍቀድ!