ይሖዋን መጠጊያችሁ አድርጋችሁታል?
“ይሖዋ የአገልጋዮቹን ሕይወት ይዋጃል፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ አይፈረድባቸውም።”—መዝ. 34:22
1. ከአዳም በወረስነው ኃጢአት የተነሳ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምን ይሰማቸዋል?
“እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” (ሮም 7:24) በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ይህን ሐሳብ እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማቸው ጊዜ አለ። ሁላችንም ይሖዋን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ቢኖረንም ከአዳም በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ይሖዋን የሚያሳዝን ድርጊት የምንፈጽምበት ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ወቅት እንደ ጳውሎስ ስሜታችን ሊደቆስ ይችላል። እንዲያውም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ አምላክ ፈጽሞ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ተሰምቷቸዋል።
2. (ሀ) መዝሙር 34:22 የአምላክ አገልጋዮች በጥፋተኝነት ስሜት ከመጠን በላይ ሊደቆሱ እንደማይገባ የሚጠቁመው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? (“ ጠቃሚ ትምህርት ወይስ ትንቢታዊ ጥላ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
2 ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ይሖዋን መጠጊያ ወይም መሸሸጊያ የሚያደርጉ ሰዎች በጥፋተኝነት ስሜት ከመጠን በላይ ሊደቆሱ እንደማይገባ ይናገራሉ። (መዝሙር 34:22ን አንብብ።) ይሁንና ይሖዋን መሸሸጊያ ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው? የይሖዋን ምሕረትና ይቅርታ ለማግኘት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል? በጥንቷ እስራኤል የመማጸኛ ከተሞች እንዲኖሩ ስለተደረገው ዝግጅት መመርመራችን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ያስችለናል። በእርግጥ ይህ ዝግጅት የነበረው በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ነው፤ ሕጉ ደግሞ በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ጀምሮ በሌላ ሕግ ተተክቷል። ሆኖም ይህን ሕግ የሰጠው ይሖዋ እንደሆነ እናስታውስ። በመሆኑም የመማጸኛ ከተሞች እንዲኖሩ የተደረገው ዝግጅት ይሖዋ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ኃጢአተኞችና ስለ ንስሐ ያለውን አመለካከት ለመገንዘብ ይረዳናል። በመጀመሪያ ግን እነዚህ ከተሞች ለዚህ ዓላማ እንዲውሉ የተደረገበትን ምክንያት እንዲሁም ከተሞቹ የሚሰጡትን አገልግሎት እስቲ እንመልከት።
“ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን ምረጡ”
3. ሆን ብሎ ነፍስ ካጠፋ ሰው ጋር በተያያዘ እስራኤላውያን ምን ማድረግ ነበረባቸው?
3 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የሚፈጸሙ ከነፍስ ማጥፋት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይሖዋ በጣም አክብዶ ይመለከታቸው ነበር። ሆን ብሎ ነፍስ ያጠፋን ግለሰብ፣ የሟቹ የቅርብ ዘመድ የሚገድለው ሲሆን ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ደም ተበቃይ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዘኁ. 35:19) እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወሰደው፣ ነፍሰ ገዳዩ ላፈሰሰው ንጹሕ ደም ሕይወቱን እንዲከፍል ሲባል ነው። በዚህ ረገድ አፋጣኝ እርምጃ መወሰዱ ተስፋይቱ ምድር በደም እንዳትበከል ያደርጋል፤ ይሖዋ ለሕዝቡ “[የሰው ደም ማፍሰስ] ምድሪቱን ስለሚበክል ያላችሁባትን ምድር አትበክሉ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር።—ዘኁ. 35:33, 34
4. በእስራኤል ውስጥ አንድ ሰው ሳያስበው ነፍስ ቢያጠፋ ምን ይደረግ ነበር?
4 ይሁንና በእስራኤል ውስጥ አንድ ሰው ሳያስበው ነፍስ ቢያጠፋ ምን ይደረግ ነበር? ግለሰቡ አውቆ ባይሆንም እንኳ ንጹሕ ደም አፍስሷል፤ በመሆኑም ከተጠያቂነት አያመልጥም። (ዘፍ. 9:5) ሆኖም እንዲህ ያለው ግለሰብ፣ ደም ተበቃዩ እንዳይገድለው ከስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ ይችል ነበር፤ ይህም ምሕረት የተንጸባረቀበት ዝግጅት ነው። በዚያ ከተማ ውስጥ እንዲቆይ እስከተፈቀደለት ድረስ ጥበቃ ያገኛል። ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ፣ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ መቆየት ይገባዋል።—ዘኁ. 35:15, 28
5. የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል የምንለው ለምንድን ነው?
5 የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት እንዲኖር ያደረጉት እስራኤላውያን ሳይሆኑ ይሖዋ ራሱ ነው። ይሖዋ፣ ለኢያሱ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቶት ነበር፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘. . . ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን ምረጡ።’” ከተሞቹ ‘ለዚህ ዓላማ ተቀድሰው’ ነበር። (ኢያሱ 20:1, 2, 7, 8) እነዚህ ከተሞች ለልዩ አገልግሎት እንዲውሉ በቀጥታ መመሪያ የሰጠው ይሖዋ ከመሆኑ አንጻር የሚከተሉት ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል፦ ‘ይህ ዝግጅት ስለ ይሖዋ ምሕረት ይበልጥ እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው? ይህ ዝግጅት በዛሬው ጊዜ ይሖዋን መጠጊያ ወይም መሸሸጊያ ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ ምን ያስተምረናል?’
“ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይናገር”
6, 7. (ሀ) ሳያውቅ ነፍስ ላጠፋው ግለሰብ ፍርድ በመስጠት ረገድ ሽማግሌዎች ምን ሚና ይጫወታሉ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ የሄደው ሰው ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ማቅረብ ያለበት ለምንድን ነው?
6 ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ፣ ከመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ በከተማዋ በር ላይ ቆሞ መጀመሪያ “ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን [መናገር]” አለበት። ሽማግሌዎቹም ወደ ከተማቸው ያስገቡታል። (ኢያሱ 20:4) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ይህ ግለሰብ የሰው ነፍስ ወዳጠፋበት ከተማ እንዲመለስና የዚያ ከተማ ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ ፍርድ እንዲሰጡ ይደረጋል። (ዘኁልቁ 35:24, 25ን አንብብ።) ግለሰቡ ወደ መማጸኛ ከተማ እንዲመለስ የሚፈቀድለት ሽማግሌዎቹ፣ ነፍስ ያጠፋው ሳያስበው መሆኑን ከፈረዱ ብቻ ነው።
7 ጉዳዩን ሽማግሌዎች የሚመለከቱት ለምንድን ነው? የእስራኤልን ጉባኤ ንጽሕና ለመጠበቅ እንዲሁም ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ ይሖዋ ካደረገው ምሕረት የተንጸባረቀበት ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ግለሰቡ ወደ ሽማግሌዎች ሳይሄድ ከቀረ “ራሱን ለአደጋ ያጋልጣል።” አክለውም “አምላክ ባደረገለት ጥበቃ የሚያስገኝ ዝግጅት ስላልተጠቀመ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል” ብለዋል። ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋ ሰው እርዳታ ማግኘት የሚችልበት ዝግጅት አለ፤ ሆኖም ከዝግጅቱ ለመጠቀም ጥረት ማድረግና የሚሰጠውን እርዳታ መቀበል አለበት። ይህ ግለሰብ መጠጊያ ለማግኘት፣ ይሖዋ እንዲለዩ ወዳደረጋቸው የመማጸኛ ከተሞች ባይሄድና የሟቹ የቅርብ ዘመድ አግኝቶ ቢገድለው ገዳዩ በደም ዕዳ አይጠየቅም።
8, 9. ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
8 በዛሬው ጊዜ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ እንዲችል ያዕ. 5:14-16) በሁለተኛ ደረጃ፣ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የሽማግሌዎችን እርዳታ ማግኘታቸው የአምላክን ሞገስ እንደገና እንዲያገኙ እንዲሁም ኃጢአት መሥራት ልማድ እንዳይሆንባቸው ይረዳቸዋል። (ገላ. 6:1፤ ዕብ. 12:11) በሦስተኛ ደረጃ፣ ሽማግሌዎች ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ለማጽናናት እንዲሁም ከመጠን ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳይደቆሱ ለመርዳት የሚያስችል ኃላፊነትና ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች “ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” እንደሆኑ ገልጿል። (ኢሳ. 32:1, 2) ይህ ዝግጅት የአምላክ ምሕረት መገለጫ ነው ቢባል አትስማማም?
የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል። እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ግለሰቦችን ጉዳይ ሽማግሌዎች እንዲመለከቱ ዝግጅት ያደረገው ይሖዋ ራሱ ነው። (9 በርካታ የአምላክ አገልጋዮች የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃቸውና የተሰጣቸውን እርዳታ መቀበላቸው እፎይታ አስገኝቶላቸዋል። ዳንኤል የተባለን ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዳንኤል ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ሳይናገር ወራት አለፉ። እንዲህ ብሏል፦ “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ሽማግሌዎች ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት እርዳታ ሊያደርጉልኝ እንደማይችሉ ተሰማኝ። ያም ቢሆን የፈጸምኩት ኃጢአት የሚያስከትለውን ነገር ስለምፈራ የምኖረው በስጋት ነበር። ወደ ይሖዋ በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ፣ ለፈጸምኩት በደል በቅድሚያ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።” በመጨረሻም ዳንኤል የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቀ። በወቅቱ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ሽማግሌዎች መሄድ መጀመሪያ ላይ በጣም አስፈርቶኝ እንደነበር አልክድም። ካነጋገርኳቸው በኋላ ግን ከላዬ ላይ ከባድ ሸክም የወረደልኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። አሁን ምንም ነገር እንቅፋት ሳይሆንብኝ ይሖዋን ማነጋገር እችላለሁ።” በዛሬው ጊዜ ዳንኤል ንጹሕ ሕሊና ያለው ሲሆን በቅርቡም የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ተሾሟል።
“ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ” መሸሽ አለበት
10. ሳያውቅ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ ምን እርምጃ መውሰድ ነበረበት?
10 ሳያስበው የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ ምሕረት ማግኘት ከፈለገ መውሰድ ያለበት እርምጃ አለ። በአቅራቢያው ወዳለ የመማጸኛ ከተማ መሸሽ ነበረበት። (ኢያሱ 20:4ን አንብብ።) ይህ ግለሰብ ዘና እንደማይል የታወቀ ነው፤ ሕይወቱን ማዳን ከፈለገ በተቻለ ፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መሄድና እዚያው መቆየት አለበት! እርግጥ ይህን ማድረግ መሥዋዕት ያስከፍለዋል። ሥራውንና የሞቀ ቤቱን ትቶ የሚሄድ ከመሆኑም ሌላ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነቱን ያጣል፤ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ ወደ ቀድሞ ሕይወቱ መመለስ አይችልም። * (ዘኁ. 35:25) ይሁንና እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት መክፈሉ የሚያስቆጨው አይሆንም። ግለሰቡ ከመማጸኛው ከተማ ከወጣ ይህ ድርጊቱ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋቱ እንዳልተጸጸተ የሚያሳይ ይሆናል፤ ከዚህም ሌላ የራሱን ሕይወት ሊያጣ ይችላል።
11. ንስሐ የገባ አንድ ክርስቲያን ለይሖዋ ምሕረት አድናቆት እንዳለው ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
11 በዛሬው ጊዜም ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የአምላክን ምሕረት ማግኘት ከፈለጉ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። እንዲህ ያሉት ግለሰቦች የሚፈጽሙትን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ይህም ሲባል ከከባድ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ያለ ኃጢአት ወደ መፈጸም ከሚመሩ ቀለል ተደርገው የሚታዩ ኃጢአቶችም መራቅ አለባቸው ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ ንስሐ የገቡ ክርስቲያኖች የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘናችሁ እንዴት ለተግባር እንዳነሳሳችሁ ተመልከቱ! አዎ፣ አቋማችሁን ለማስተካከል እርምጃ እንድትወስዱ አነሳስቷችኋል፤ ደግሞም እንዴት ያለ ቁጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሃት፣ እንዴት ያለ ጉጉት፣ እንዴት ያለ ቅንዓት እንዳስገኘ ተመልከቱ! በእርግጥም ስህተታችሁን ለማረም እርምጃ እንድትወስዱ አድርጓችኋል።” (2 ቆሮ. 7:10, 11) ከኃጢአት ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን፣ ያለንበት ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስበን የሚጠቁም ነው፤ በተጨማሪም ‘ምንም ዓይነት ኃጢአት ብንፈጽም ይሖዋ ምሕረት ያደርግልናል’ የሚል አመለካከት እንደሌለን ያሳያል።
12. አንድ ክርስቲያን የአምላክን ምሕረት ላለማጣት የትኞቹን ነገሮች መተው ሊያስፈልገው ይችላል?
12 አንድ ክርስቲያን የይሖዋን ምሕረት ላለማጣት የትኞቹን ነገሮች መተው ሊያስፈልገው ይችላል? አንድን ነገር በጣም የሚወደው ቢሆንም እንኳ ወደ ኃጢአት ሊመራው የሚችል ከሆነ ለመተው ፈቃደኛ መሆን አለበት። (ማቴ. 18:8, 9) አንዳንድ ጓደኞችህ ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር እንድትፈጽም የሚገፋፉህ ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ታቋርጣለህ? ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ራስህን ለመግዛት እየታገልክ ከሆነ ከልክ በላይ እንድትጠጣ ሊፈትኑህ ከሚችሉ ሁኔታዎች ትርቃለህ? የብልግና ምኞቶች ወደ አእምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ ከሆነ ርኩስ ሐሳቦችን ከሚቀሰቅሱ ፊልሞች፣ ድረ ገጾች ወይም ድርጊቶች በሙሉ ለመራቅ ጥረት ታደርጋለህ? ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ላለማጉደል ስንል ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕት ብንከፍል የሚያስቆጭ አይሆንም። የእሱን ሞገስ እንዳጣን ማሰብ ከሚፈጥረው ስሜት የከፋ ምንም ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን “ዘላለማዊ ታማኝ ፍቅር” ማግኘት ከሚፈጥረው ደስታ የሚበልጥ ነገር የለም።—ኢሳ. 54:7, 8
“መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል”
13. ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ የሄደው ግለሰብ ከፍርሃትና ከስጋት ነፃ ሆኖ ደስተኛ ሕይወት ሊመራ ይችላል የምንለው ለምን እንደሆነ አብራራ።
13 ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ የሄደው ግለሰብ እዚያ ከደረሰ በኋላ ያለስጋት መኖር ይችላል። ይሖዋ ስለ እነዚያ ከተሞች ሲናገር “መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል” ብሏል። (ኢያሱ 20:2, 3) ይሖዋ፣ ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ በዚያ ጉዳይ እንደገና ለፍርድ ሊቀርብ እንደሚችል የሚጠቁም ነገር አልተናገረም፤ ደም ተበቃዩም ቢሆን ወደ መማጸኛው ከተማ ገብቶ፣ ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋውን ግለሰብ እንዲገድለው አይፈቀድለትም። በመሆኑም ሸሽቶ የሄደው ሰው፣ የበቀል እርምጃ ይወሰድብኛል ብሎ አይፈራም። በዚያ ከተማ ውስጥ እስካለ ድረስ ይሖዋ ጥበቃ ስለሚያደርግለት ያለስጋት መኖር ይችላል። የመማጸኛ ከተማ እስር ቤት አይደለም። በከተማዋ ውስጥ ሆኖ መሥራት፣ ሌሎችን መርዳት እንዲሁም ይሖዋን በሰላም ማገልገል ይችላል። በእርግጥም አስደሳችና የሚያረካ ሕይወት መምራት ይችላል!
14. ንስሐ የገባ ክርስቲያን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላል?
14 ከባድ ኃጢአት ከፈጸሙ በኋላ ንስሐ የገቡ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች፣ በደላቸው “ተብትቦ እንደያዛቸው” ይባስ ብሎም ይሖዋ ምንጊዜም በኃጢአት እንደቆሸሹ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ይቅር ሲል፣ ሙሉ በሙሉ ምሕረት እንደሚያደርግ መተማመን ትችላለህ! ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል ይህ መዝሙር 103:8-12ን አንብብ።
እውነት መሆኑን በሕይወቱ ተመልክቷል። ሽማግሌዎች እርማት ከሰጡትና እንደገና ንጹሕ ሕሊና እንዲያገኝ ከረዱት በኋላ የተሰማውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። ጉዳዩ በአግባቡ ከተፈታ በኋላ፣ የነበረኝ የጥፋተኝነት ስሜት ተወገደልኝ። ለኃጢአታችን አንድ ጊዜ ይቅር ከተባልን ዳግመኛ አንጠየቅበትም። ይሖዋ በደላችንን ከእኛ አርቆ እንደሚጥለው ተናግሯል። በመሆኑም ኃጢአታችንን እያሰብን መብሰልሰል አያስፈልገንም።” ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ፣ የመማጸኛ ከተማ ውስጥ ከገባ በኋላ ደም ተበቃዩ እንዳይገድለው መስጋት አያስፈልገውም። በተመሳሳይ እኛም ይሖዋ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ፣ ያንን ኃጢአት እንደ አዲስ አንስቶ በእኛ ላይ ለመፍረድ ምክንያት እንደሚፈልግ በማሰብ ልንሰጋ አይገባም።—15, 16. ኢየሱስ ቤዛ እና ሊቀ ካህናት መሆኑ በአምላክ ምሕረት ላይ ይበልጥ እንድትተማመን የሚረዳህ ለምንድን ነው?
15 ክርስቲያኖች፣ በይሖዋ ምሕረት ለመተማመን የሚያስችል ከእስራኤላውያን የበለጠ ምክንያት አላቸው። ጳውሎስ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ አለመቻሉ የፈጠረበትን ስሜት ከገለጸ በኋላ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል። (ሮም 7:25) ጳውሎስ፣ ከኃጢአት ምኞቶችና ቀደም ሲል የፈጸመው በደል ከሚያሳድርበት ስሜት ጋር ይታገል ነበር፤ ሆኖም ለፈጸመው ኃጢአት ንስሐ ስለገባ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ ይቅር እንዳለው ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ስለሰጠን ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም ውስጣዊ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል። (ዕብ. 9:13, 14) በተጨማሪም ሊቀ ካህናችን ነው፤ በመሆኑም ለእኛ “ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ [ሊያድን] ይችላል።” (ዕብ. 7:24, 25) በእስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት የሚጫወተው ሚና፣ ሕዝቡ ኃጢአታቸውን ይሖዋ ይቅር እንደሚልላቸው ለመተማመን ይረዳቸው ነበር፤ ከዚህ አንጻር ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ የሚያቀርበው አገልግሎትማ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለ ምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን [ለመቅረብ]” ይበልጥ እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን።—ዕብ. 4:15, 16
16 እንግዲያው ይሖዋን መሸሸጊያህ ማድረግ ከፈለግህ፣ በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ይኑርህ። ቤዛው ብዙዎችን ለመጥቀም የተደረገ ዝግጅት እንደሆነ ብቻ አድርገህ ከማሰብ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ አንተንም እንደሚጠቅምህ እምነት ይኑርህ። (ገላ. 2:20, 21) አንተም የኃጢአት ይቅርታ እንድታገኝ መሠረት የሚሆነው ቤዛው እንደሆነ እምነት ይኑርህ። ቤዛው አንተም የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ መንገድ እንደከፈተልህ እምነት ይኑርህ። የኢየሱስ መሥዋዕት ይሖዋ ለአንተ የሰጠህ ስጦታ ነው።
17. ይሖዋን መጠጊያህ ማድረግ የምትፈልገው ለምንድን ነው?
17 የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት ይሖዋ ምን ያህል መሐሪ አምላክ እንደሆነ ያሳያል። አምላክ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት፣ ሕይወት ቅዱስ መሆኑን አስተምሮናል፤ በተጨማሪም ሽማግሌዎች እንዴት እንደሚረዱን፣ እውነተኛ ንስሐ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት እንዲሁም ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚለን መተማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ ከዚህ ዝግጅት እንማራለን። አንተስ ይሖዋን መጠጊያህ ወይም መሸሸጊያህ እያደረግኸው ነው? ከይሖዋ የበለጠ አስተማማኝ መጠጊያ የለም! (መዝ. 91:1, 2) የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት የይሖዋን የላቀ ፍትሕና ምሕረት ለመምሰል እንዴት እንደሚረዳን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
^ አን.10 የአይሁዳውያን የማመሣከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋው ሰው ቤተሰቦች፣ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ አብረውት እንዲኖሩ የሚፈቀድላቸው ይመስላል።