የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ “ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ሲባል፣ ይሖዋ ልንሸከም የምንችለው ፈተና ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ በመገምገም ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን ይወስናል ማለት ነው?
እንዲህ ያለው አመለካከት ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ እንመልከት። አንድ ወንድም፣ ልጁ ራሱን ባጠፋበት ወቅት እንዲህ በማለት ጠይቋል፦ ‘እኔና ባለቤቴ የልጃችን ሞት ያስከተለብንን ሐዘን መቋቋም እንችል እንደሆነ ይሖዋ አስቀድሞ አስቦበታል ማለት ነው? ይህ መከራ የደረሰብን አምላክ ልንቋቋመው እንደምንችል ስላሰበ ነው?’ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ነገር ይቆጣጠራል ብለን ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት አለ?
በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የተጠቀሰውን የጳውሎስን ሐሳብ ጠለቅ ብለን ስንመረምር የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን፦ ይሖዋ ልንሸከም የምንችለው ፈተና ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ ከገመገመ በኋላ በዚህ ላይ ተመሥርቶ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን ይወስናል ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርጉንን አራት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።
አንደኛ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። በሕይወታችን ውስጥ የምንከተለውን ጎዳና በተመለከተ የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ ይፈልጋል። (ዘዳ. 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) ትክክለኛውን መንገድ ከመረጥን፣ ይሖዋ አካሄዳችንን እንደሚመራልን መተማመን እንችላለን። (ምሳሌ 16:9) የተሳሳተ አካሄድ ከመረጥን ግን ውሳኔያችን ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አንችልም። (ገላ. 6:7) ይሖዋ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን የሚወስን ቢሆን ኖሮ ይህ የመምረጥ ነፃነታችንን መጋፋት አይሆንበትም?
ሁለተኛ፣ ይሖዋ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” እንዳያጋጥሙን አይከላከልልንም። (መክ. 9:11) በመጥፎ ጊዜ አጉል ቦታ ላይ በመገኘታችን ምክንያት አደጋ ሊያጋጥመን ምናልባትም የከፋ ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። ኢየሱስ፣ ግንብ ተንዶባቸው ስለሞቱ 18 ሰዎች በተናገረበት ወቅት፣ ሰዎቹ እንዲህ ዓይነት አደጋ የደረሰባቸው አምላክ ይህ እንዲሆን ስለወሰነ አለመሆኑን ገልጿል። (ሉቃስ 13:1-5) እንዲህ ያሉ ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲደርሱ፣ ማን እንደሚተርፍና ማን እንደሚሞት አምላክ አስቀድሞ ይወስናል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊነት የጎደለው አይሆንም?
ሦስተኛ፣ ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጉዳይ እያንዳንዳችንን ይመለከታል። ሰይጣን፣ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው አጠያያቂ እንደሆነ ገልጿል፤ ማናቸውም ቢሆኑ ፈተና ሲደርስባቸው ለይሖዋ ታማኝ እንደማይሆኑ ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4፤ ራእይ 12:10) ይሖዋ አንዳንድ ፈተናዎችን ልንሸከማቸው እንደማንችል በማሰብ እነዚህ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን የሚከላከልልን ከሆነ፣ አምላክን የምናገለግለው ለራሳችን ጥቅም እንደሆነ በመግለጽ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ትክክል ሊሆን ነው ማለት ነው።
አራተኛ፣ ይሖዋ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ነገር በሙሉ አስቀድሞ ማወቅ አያስፈልገውም። አምላክ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን አስቀድሞ ይወስናል የሚለው አመለካከት፣ ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ሁሉንም ነገር ያውቃል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሆኖም ይህ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም። እርግጥ ነው፣ አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታ አለው። (ኢሳ. 46:10) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ እንዳልሆነ ይናገራል። (ዘፍ. 18:20, 21፤ 22:12) ስለሆነም ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት የመምረጥ ነፃነታችንን እንደሚያከብርልን በሚያሳይ መንገድ ነው። ደግሞስ ነፃነታችንን የሚያከብር እንዲሁም አፍቃሪና ጻድቅ የሆነ አምላክ እንዲህ ማድረጉ የሚጠበቅ ነገር አይደለም?—ዘዳ. 32:4፤ 2 ቆሮ. 3:17
ታዲያ፣ “አምላክ . . . ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም” የሚለውን የጳውሎስ ሐሳብ ልንረዳው የሚገባው እንዴት ነው? ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ይሖዋ ፈተናዎች ከመድረሳቸው በፊት ስለሚያደርገው ነገር ሳይሆን ፈተና ወይም መከራ በሚደርስብን ወቅት ስለሚያደርገው ነገር ነው። * ሐዋርያው የተናገራቸው ቃላት፣ በሕይወታችን ውስጥ የትኛውም ፈተና ቢደርስብን በይሖዋ እስከተማመንን ድረስ እሱ እንደሚደግፈን ማረጋገጫ ይሰጡናል። (መዝ. 55:22) ጳውሎስ የተናገረው የሚያጽናና ሐሳብ በሁለት መሠረታዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ ነው።
አንደኛ፣ የሚደርስብን ፈተና “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ” አይደለም። በእኛ ላይ የሚደርሱት መከራዎች ከዚህ በፊት በሌሎች ላይ የደረሱ ናቸው። በአምላክ ላይ እስከታመንን ድረስ፣ የሚደርስብን ፈተና ልንሸከመው ከምንችለው በላይ አይደለም። (1 ጴጥ. 5:8, 9) በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ስለደረሱባቸው ፈተናዎች ነው። (1 ቆሮ. 10:6-11) ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል የትኛውም ቢሆን በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ወይም ታማኝ እስራኤላውያን ሊሸከሙት የማይችሉት አልነበረም። እዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ‘ከእነሱ አንዳንዶቹ’ እንዳልታዘዙ አራት ጊዜ ጠቅሷል። አንዳንድ እስራኤላውያን በአምላክ ባለመታመናቸው ምክንያት በመጥፎ ምኞቶች መሸነፋቸው የሚያሳዝን ነው።
ሁለተኛ፣ “አምላክ ታማኝ ነው።” አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ከሚናገሩት ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው እሱ “ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ ሁሉ . . . ታማኝ ፍቅር” ያሳያቸዋል። (ዘዳ. 7:9) በተጨማሪም እነዚህ ዘገባዎች አምላክ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚፈጽም ያሳያሉ። (ኢያሱ 23:14) ባለፉት የታሪክ ዘመናት እንደታየው አምላክ ሁልጊዜ ታማኝ ነው፤ ከዚህ አንጻር፣ እሱን የሚወዱና የሚታዘዙ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጋር በተያያዘ (1) የትኛውም ፈተና መሸከም ከሚችሉት በላይ እንዲከብድባቸው እንደማይፈቅድ እንዲሁም (2) “መውጫ መንገዱን” እንደሚያዘጋጅላቸው መተማመን ይችላሉ።
ይሖዋ፣ በእሱ የሚታመኑ ሰዎች ፈተና ሲደርስባቸው መውጫ መንገድ የሚያዘጋጅላቸው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ ፈቃዱ ከሆነ ፈተናውን ሊያስወግደው ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ “ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ [ይሖዋ] መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” እንዳለ አስታውስ። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ “መውጫ መንገዱን” የሚያዘጋጀው ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንድንችል የሚያስፈልገንን ድጋፍ በመስጠት ነው። ይሖዋ፣ መውጫ መንገድ ሊያዘጋጅልን የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት፦
-
“በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሖዋ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና ታማኙ ባሪያ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት አእምሯችንን፣ ልባችንንና ስሜታችንን ያረጋጋልናል።—ማቴ. 24:45፤ ዮሐ. 14:16 ግርጌ፤ ሮም 15:4
-
በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሊመራን ይችላል። (ዮሐ. 14:26) ፈተናዎች ሲያጋጥሙን፣ መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድናስታውስ እንዲሁም መውሰድ የሚገባንን የጥበብ እርምጃ እንድናስተውል ይረዳናል።
-
በመላእክቱ ተጠቅሞ ይረዳናል።—ዕብ. 1:14
-
በንግግራቸውና በድርጊታቸው “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልን የሚችሉ የእምነት አጋሮቻችንን በመጠቀም ይረዳናል።—ቆላ. 4:11
እንግዲያው በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ያላቸውን ትርጉም በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ይሖዋ፣ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን አስቀድሞ አይወስንም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ነገር አለ፦ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ከታመንን፣ ፈተናዎቹ ሰው መሸከም ከሚችለው በላይ እንዲከብዱብን አይፈቅድም፤ እንዲሁም ፈተናዎቹን በጽናት መቋቋም እንድንችል ምንጊዜም መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል። ይህን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
^ አን.2 “ፈተና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መከራ” የሚል ፍቺም ሊሰጠው ይችላል።