የይሖዋን በረከት ለማግኘት መታገላችሁን ቀጥሉ
“ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ታግለህ በመጨረሻ አሸንፈሃል።”—ዘፍ. 32:28
መዝሙሮች፦ 60, 38
1, 2. የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል?
ታማኝ ከሆነው ከመጀመሪያው ሰው ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘመናችን ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ትግል አድርገዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የይሖዋን ሞገስና በረከት ለማግኘት ሲሉ “በመከራ ውስጥ በከፍተኛ ተጋድሎ [እንደጸኑ]” ጽፏል። (ዕብ. 10:32-34) ጳውሎስ ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ተጋድሎ እንደ ሩጫ፣ ትግልና ቡጢ ባሉ በግሪክ ይካሄዱ የነበሩ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች ከሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት ጋር አነጻጽሮታል። (ዕብ. 12:1, 4) በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች በሕይወት ሩጫ እየተካፈልን ሲሆን በውድድሩ ላይ ትኩረታችንን በመከፋፈል አሊያም እኛን ጠልፈው ወይም ታግለው በመጣል ደስታችንን እና የወደፊት ሽልማታችንን ሊያሳጡን የሚሞክሩ ጠላቶች አሉን።
2 በመጀመሪያ ደረጃ ከሰይጣንና እሱ ከሚቆጣጠረው ዓለም ጋር ከባድ ትግል እናደርጋለን። (ኤፌ. 6:12) በዓለም ላይ ያሉ እንደ “ምሽግ” የሆኑ ነገሮች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን መታገላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከእነዚህም መካከል ዓለም የሚያስፋፋቸው ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች እንዲሁም እንደ ፆታ ብልግና፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣትና ዕፅ መውሰድ የመሳሰሉት ጎጂ ልማዶች ይገኙበታል። በተጨማሪም ካሉብን ድክመቶችና ተስፋ እንድንቆርጥ ከሚያደርጉን ነገሮች ጋር ሁልጊዜ መታገል አለብን።—2 ቆሮ. 10:3-6፤ ቆላ. 3:5-9
3. አምላክ ከጠላቶቻችን ጋር ለምናደርገው ውጊያ የሚያሠለጥነን እንዴት ነው?
3 እንደነዚህ ያሉትን ኃይለኛ ጠላቶቻችንን በእርግጥ ማሸነፍ እንችላለን? አዎ፣ ግን ያለምንም ትግል እናሸንፋለን ማለት አይደለም። ጳውሎስ፣ በዚያ ዘመን በቡጢ ውድድር ከሚካፈል ሰው ጋር ራሱን በማነጻጸር “ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:26) አንድ የቡጢ ተወዳዳሪ ባላጋራው የሚሰነዝርበትን ቡጢ እንደሚመክት ሁሉ እኛም ጠላቶቻችን ከሚሰነዝሩብን ጥቃት ራሳችንን መከላከል አለብን። ይሖዋ ይህን ማድረግ እንድንችል የሚያሠለጥነን ከመሆኑም ሌላ ይረዳናል። በቃሉ በኩል ሕይወት አድን የሆነ መመሪያ ይሰጠናል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ይረዳናል። ታዲያ የተማራችሁትን በተግባር እያዋላችሁት ነው? እንዲህ የማታደርጉ ከሆነ የጠላትን ጥቃት ሙሉ በሙሉ መከላከል አትችሉም፤ ይህም ‘ቡጢ ሰንዝራችሁ አየር እንደ መምታት’ ይሆንባችኋል።
4. ክፉው እንዳያሸንፈን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ጠላቶቻችን ጨርሶ ባልጠበቅነው ጊዜ ወይም በተዳከምንበት ወቅት ጥቃት ሊሰነዝሩብን ስለሚችሉ ሁልጊዜ ንቁ መሆን አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ “በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል። (ሮም 12:21) “በክፉ አትሸነፍ” የሚለው ሐሳብ ክፉውን ማሸነፍ እንደምንችል ያሳያል። ክፉውን ማሸነፍ የምንችለው በትግሉ ከጸናን ነው። በሌላ በኩል ግን ከተዘናጋንና መታገላችንን ካቆምን በሰይጣን፣ እሱ በሚቆጣጠረው ክፉ ዓለምና ኃጢአተኛ በሆነው ሥጋችን ልንሸነፍ እንችላለን። ሰይጣን፣ ተሸንፋችሁ እጅ እንድትሰጡ እንዲያደርጋችሁ ፈጽሞ አትፍቀዱ!—1 ጴጥ. 5:9
5. (ሀ) የአምላክን በረከት ለማግኘት በምናደርገው ትግል ለመጽናት ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ስለ የትኞቹ ሰዎች እንመለከታለን?
5 በትግል ላይ ያሉ ሰዎች፣ አሸናፊ መሆን ከፈለጉ እየታገሉ ያሉበትን ዓላማ መዘንጋት የለባቸውም። የአምላክን ሞገስና በረከት ማግኘት እንዲችሉ በዕብራውያን 11:6 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ምንጊዜም በአእምሯቸው መያዝ ይኖርባቸዋል፤ ጥቅሱ “ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል” ይላል። “ከልብ ለሚፈልጉት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ያመለክታል። (ሥራ 15:17) የይሖዋን በረከት ለማግኘት ሲሉ ብርቱ ጥረት ያደረጉ ወንዶችንና ሴቶችን ግሩም ምሳሌ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እናገኛለን። ያዕቆብ፣ ራሔል፣ ዮሴፍና ጳውሎስ ስሜታቸውን የሚደቁሱ ብሎም ኃይላቸውን የሚያሟጥጡ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ጽናት የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝ አሳይተዋል። በትግሉ አሸናፊ የሆኑትን እነዚህን አራት ሰዎች መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
ጽናት በረከት ያስገኛል
6. ያዕቆብ በትግሉ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ምን ሽልማትስ አግኝቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
6 ያዕቆብ ለይሖዋ ፍቅር እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት የነበረው ከመሆኑም ሌላ አምላክ ዘሩን እንደሚባርክ በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት ስለነበረው በትግሉ ጸንቷል። (ዘፍ. 28:3, 4) ያዕቆብ 100 ዓመት ገደማ ሳለ የአምላክን በረከት ለማግኘት ሲል ሥጋ ከለበሰ መልአክ ጋር እንኳ ሳይቀር ባለ በሌለ ኃይሉ ታግሏል። (ዘፍጥረት 32:24-28ን አንብብ።) ያዕቆብ ከአንድ ኃያል መልአክ ጋር ለመታገል የሚያስፈልገው ብርታት ሊኖረውና በትግሉ ሊጸና የቻለው በራሱ ኃይል ነው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው! ያዕቆብ በትግሉ ላለመሸነፍ ቆርጦ ነበር፤ እስከ መጨረሻው ድረስ በፍልሚያው ጸንቷል! ደግሞም በመጽናቱ ሽልማቱን አግኝቷል። በእርግጥም፣ እስራኤል የሚል ስም የተሰጠው መሆኑ ተገቢ ነው፤ እስራኤል “ከአምላክ ጋር የታገለ [በጽናት የተጣበቀ]” ወይም “አምላክ ይታገላል” የሚል ትርጉም አለው። ያዕቆብ እኛም የምንጓጓለትን አስደናቂ ሽልማት ይኸውም የይሖዋን ሞገስና በረከት አግኝቷል።
7. (ሀ) ራሔል ምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ገጥሟት ነበር? (ለ) በትግሉ የጸናችውና ውሎ አድሮ የተባረከችው እንዴት ነው?
7 የያዕቆብ ሚስት የሆነችው ራሔልም ይሖዋ ለባሏ የገባውን ቃል እንዴት እንደሚፈጽም ለማየት ትጓጓ ነበር። ይሁንና ልትወጣው የማትችል መሰናክል ያጋጠማት ይመስል ነበር። ራሔል ልጅ አልነበራትም። በዚያ ዘመን ደግሞ ይህ እንደ ከባድ መከራ የሚታይ ነገር ነበር። ታዲያ ራሔል ተስፋ አስቆራጭና ከቁጥጥሯ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም በትግሉ ለመቀጠል የሚያስችላትን ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው? ተስፋ ቆርጣ እጅ አልሰጠችም። ከዚህ ይልቅ አጥብቃ በመጸለይ መታገሏን ቀጠለች። ይሖዋም ራሔል ያቀረበችውን ምልጃ የሰማ ሲሆን ውሎ አድሮ ልጆች በመስጠት ባርኳታል። በእርግጥም፣ ራሔል “ብርቱ ትግል ገጠምኩ፤ አሸናፊም ሆንኩ!” ብላ በድል አድራጊነት መናገሯ የሚያስገርም አይደለም።—8. ዮሴፍ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? የወሰደው እርምጃ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
8 ያዕቆብና ራሔል በጽናት ረገድ የተዉት ምሳሌ በልጃቸው በዮሴፍ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት፤ ዮሴፍ እምነቱን የሚፈትን ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ እነሱ የተዉት ምሳሌ ጠቅሞታል። ዮሴፍ የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ሕይወቱ ተመሰቃቀለ። ወንድሞቹ ስለቀኑበት ለባርነት ሸጡት። ከጊዜ በኋላም በግብፅ ሳለ ያለጥፋቱ ለዓመታት ታሰረ። (ዘፍ. 37:23-28፤ 39:7-9, 20, 21) ሆኖም ዮሴፍ ባጋጠመው ነገር ተስፋ አልቆረጠም፤ አሊያም ደግሞ በምሬት ተሞልቶ ለበቀል አልተነሳሳም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ያደረገው ከይሖዋ ጋር ባለው አስደሳች ዝምድና ላይ ነበር። (ዘሌ. 19:18፤ ሮም 12:17-21) ከዮሴፍ ምሳሌ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። አስተዳደጋችን ጥሩ ባይሆን ወይም አሁን ያለንበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም እንኳ በጽናት መታገላችንን መቀጠል ያስፈልገናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዘፍጥረት 39:21-23ን አንብብ።
9. እንደ ያዕቆብ፣ ራሔልና ዮሴፍ ሁሉ እኛም የይሖዋን በረከት ለማግኘት ምን ዓይነት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል?
9 እስቲ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህንና ፈተና የሆነብህን አንድ ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። ምናልባትም ግፍና ጭፍን ጥላቻ እየደረሰብህ አሊያም ሰዎች እያፌዙብህ ይሆናል። ወይም አንድ ሰው በቅናት ተነሳስቶ በሐሰት እየወነጀለህ ሊሆን ይችላል። ተስፋ ቆርጠህ እጅ ከመስጠት ይልቅ ያዕቆብ፣ ራሔልና ዮሴፍ ይሖዋን በደስታ ማገልገላቸውን ለመቀጠል የረዳቸው ምን እንደሆነ አስታውስ። እነዚህ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራቸው አምላክ ብርታት ሰጥቷቸዋል እንዲሁም ባርኳቸዋል። መታገላቸውን የቀጠሉ ከመሆኑም ሌላ ካቀረቡት ልባዊ ጸሎት ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዱ ነበር። የምንኖረው የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ በተቃረበበት ወቅት በመሆኑ፣ ከፊታችን የተዘረጋልንን አስተማማኝ ተስፋ አጥብቀን መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው! አንተስ፣ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ስትል ባለ በሌለ ኃይልህ ለመታገል ፈቃደኛ ነህ?
በረከት ለማግኘት ስትሉ ለመታገል ፈቃደኞች ናችሁ?
10, 11. (ሀ) የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ዓይነት ትግል ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል? (ለ) ትክክለኛውን ምርጫ ለማድረግ ስንታገል አሸናፊ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
10 የአምላክን በረከት ለማግኘት ከየትኞቹ ሁኔታዎች ጋር መታገል ሊያስፈልገን ይችላል? ብዙዎች ከሚታገሏቸው ነገሮች አንዱ የሥጋ ድክመት ነው። ሌሎች ደግሞ ለአገልግሎቱ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል። አንተም ካለብህ የጤና እክል ወይም ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገልክ ይሆናል። ያስቀየማቸውን ወይም ከባድ በደል የፈጸመባቸውን ሰው ይቅር ለማለት የሚታገሉም አሉ። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ሁላችንም፣ ለታማኞቹ ወሮታ ከፋይ የሆነውን አምላክ ማገልገል አስቸጋሪ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ነገሮች ጋር መታገል አለብን።
11 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ክርስቲያን መሆንና ትክክለኛውን ኤር. 17:9 ግርጌ) ልባችሁ መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረባችሁ እንደሆነ ከተሰማችሁ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አጥብቃችሁ ጸልዩ። መጸለያችሁና መንፈስ ቅዱስን ማግኘታችሁ፣ ትክክለኛውንና የይሖዋን በረከት የሚያስገኝላችሁን አካሄድ ለመከተል ብርታት ይሰጣችኋል። በተጨማሪም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም የግል ጥናትና ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ይኑራችሁ።—መዝሙር 119:32ን አንብብ።
ምርጫ ማድረግ ብርቱ ትግል ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ አታላይ የሆነው ልባችን በተቃራኒው መንገድ እንድንሄድ የሚገፋፋን ከሆነ ትግሉ ከባድ ይሆንብናል። (12, 13. ሁለት ክርስቲያኖች መጥፎ ምኞቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል እርዳታ ያገኙት እንዴት ነው?
12 የአምላክ ቃልና ቅዱስ መንፈሱ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን፣ በርካታ ክርስቲያኖች መጥፎ ምኞቶችን እንዲያስወግዱ እንዴት እንደረዷቸው የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወጣት በጥር 2004 ንቁ! ላይ የወጣውን “መጥፎ ምኞቶችን ታግለህ ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ካነበበ በኋላ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ አእምሮዬ የሚመጡትን መጥፎ ሐሳቦች ለመቆጣጠር እታገላለሁ። በመጽሔቱ ላይ ‘ብዙዎች ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ በጣም ከባድ ነው’ የሚለውን ሐሳብ ሳነብ ሌሎች ወንድሞችም እንደ እኔ ዓይነት ትግል እንዳለባቸውና በትግሉ ብቻዬን እንዳልሆንኩ ተገነዘብኩ።” ይህ ወጣት በኅዳር 2003 ንቁ! ላይ ከወጣው “ከፆታ ጋር በተያያዘ ሰዎች የፈለጉትን አኗኗር ቢመርጡ አምላክ ይቀበለዋል?” ከሚለው ርዕስም ጥቅም አግኝቷል። ለአንዳንዶች ትግሉ ‘ሥጋቸውን እንደሚወጋ እሾህ’ እንደሚሆንባቸው መጽሔቱ ይገልጻል። (2 ቆሮ. 12:7) እንደነዚህ ያሉ ክርስቲያኖች የጽድቅን ጎዳና ለመከተል ምንጊዜም ትግል ማድረግ ቢያስፈልጋቸውም ወደፊት ከዚህ ዓይነቱ ትግል እንደሚገላገሉ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ይህ ወጣት ይህን ማወቁ፣ አንድ ቀን ባለፈ ቁጥር በቀጣዩም ቀን ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ብርታት እንደሚሰጠው ተናግሯል። አክሎም “ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ እያንዳንዱን ቀን በታማኝነት ለማለፍ እንድንችል በድርጅቱ አማካኝነት ስለሚረዳን በጣም አመስጋኝ ነኝ” ብሏል።
13 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር የአንዲት እህትን ተሞክሮም እንመልከት። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ምንጊዜም የሚያስፈልገንን ምግብ ልክ በትክክለኛው ጊዜ ስለምታቀርቡልን ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ። ብዙውን ጊዜ፣ የሚወጡት ርዕሶች ለእኔ ተብለው እንደተዘጋጁ ይሰማኛል። ይሖዋ የሚጠላውን አንድ መጥፎ ዝንባሌ ለማሸነፍ ለዓመታት ስታገል ኖሬያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ቆርጬ ትግሉን ለማቆም ይቃጣኛል። ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ መሆኑን አውቃለሁ፤ ሆኖም በውስጤ ላለው ለዚህ መጥፎ ዝንባሌ ጥላቻ ስላላዳበርኩ የይሖዋን እርዳታ ማግኘት እንደሚገባኝ አይሰማኝም ነበር። ይህ ዓይነቱ የማያቋርጥ ትግል ሕይወቴን ከባድ አድርጎብኛል። . . . በመጋቢት 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ‘ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?’ የሚለውን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ይሖዋ በእርግጥም ሊረዳኝ እንደሚፈልግ ተሰምቶኛል።”
14. (ሀ) ጳውሎስ ስለሚያደርገው ትግል ምን ተሰምቶት ነበር? (ለ) ካሉብን ድክመቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
14 ሮም 7:21-25ን አንብብ። ጳውሎስ ፍጹም ባለመሆናችን ካሉብን ምኞቶችና ድክመቶች ጋር መታገል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቶታል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ በይሖዋ በመታመን ወደ እሱ ከጸለየና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካዳበረ በውስጡ ያለውን ይህን ትግል ማሸነፍ እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። እኛም ካሉብን ድክመቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን እንችላለን። እንዴት? የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል፣ ድክመቶቻችንን በራሳችን ኃይል ለማሸነፍ ከመታገል ይልቅ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመን እንዲሁም በቤዛው ላይ እምነት በማሳደር ነው።
15. ምንጊዜም ታማኞች ለመሆንና በፈተናዎች ለመጽናት ጸሎት ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?
15 አምላክ አንድ ጉዳይ ምን ያህል እንዳሳሰበን እንድናሳይ የሚፈልግበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ እኛ ራሳችን (ወይም አንድ የቤተሰባችን አባል) በጠና ብንታመም አሊያም ግፍ ቢፈጸምብን ምን እናደርጋለን? ይሖዋ፣ በታማኝነት ለመቀጠል ብሎም ደስታችንንና መንፈሳዊ ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር የሚያስችለንን ብርታት እንዲሰጠን አዘውትረን በመለመን በእሱ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን እናሳያለን። (ፊልጵ. 4:13) በጳውሎስ ዘመንም ሆነ በዚህ ዘመን የኖሩ የብዙ ክርስቲያኖች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጸሎት ኃይላችን እንዲታደስና ለመጽናት የሚያስችል ድፍረት እንድናገኝ ይረዳናል።
የይሖዋን በረከት ለማግኘት መታገላችሁን ቀጥሉ
16, 17. ከምታደርገው ትግል ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
16 ዲያብሎስ ተስፋ እንድትቆርጡና ተሸንፋችሁ እጅ እንድትሰጡ ለማድረግ እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም። እናንተ ግን “መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ [ለመያዝ]” ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። (1 ተሰ. 5:21) ከሰይጣን፣ ክፉ ከሆነው የሰይጣን ዓለም እንዲሁም ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር በምታደርጉት ትግል አሸናፊዎች እንደምትሆኑ እርግጠኞች ሁኑ። አምላክ እናንተን ለማበርታት ባለው ኃይል ሙሉ በሙሉ የምትተማመኑ ከሆነ አሸናፊ መሆን ትችላላችሁ።—2 ቆሮ. 4:7-9፤ ገላ. 6:9
17 እንግዲያው መታገላችሁን ቀጥሉ። መፋለማችሁን አታቋርጡ። ምንጊዜም ተጋደሉ። ጸንታችሁ ተመላለሱ። ይሖዋ “ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት” እንደሚያፈስላችሁ ሙሉ እምነት ይኑራችሁ።—ሚል. 3:10