የጥናት ርዕስ 6
‘የሴት ራስ ወንድ ነው’
‘የሴት ራስ ወንድ ነው።’—1 ቆሮ. 11:3
መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ
ማስተዋወቂያ *
1. አንዲት ነጠላ እህት አንድን ወንድም ለማግባት ስታስብ ምን ብላ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል?
ሁሉም ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ናቸው፤ እሱ ደግሞ ፍጹም የሆነ ራስ ነው። ሆኖም አንዲት ክርስቲያን ትዳር ስትመሠርት ራሷ የሚሆነው ፍጹም ያልሆነ ወንድ ነው። ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ወንድም ለማግባት ስታስብ እንዲህ ብላ ራሷን መጠየቋ ጠቃሚ ነው፦ ‘ይህ ወንድም ጥሩ የቤተሰብ ራስ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ነገሮች አሉ? በሕይወቱ ወስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣል? ካልሆነ ከተጋባን በኋላ ጥሩ መንፈሳዊ የቤተሰብ ራስ ይሆናል ብዬ እንዳስብ የሚያደርግ ምን ምክንያት አለኝ?’ በእርግጥ አንዲት እህት እንዲህ ብላ ራሷን መጠየቋም ተገቢ ነው፦ ‘እኔ ራሴ ለትዳር ሕይወት የሚጠቅሙ ምን ባሕርያት አሉኝ? ታጋሽና ደግ ነኝ? ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መሥርቼያለሁ?’ (መክ. 4:9, 12) አንዲት ሚስት በትዳሯ ደስተኛ መሆኗ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተመካው ከማግባቷ በፊት በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ነው።
2. በዚህ ጥናት ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያን እህቶች ለባሎቻቸው በመገዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል! ከእነዚህ ታማኝ ሴቶች ጋር ይሖዋን ማገልገል በጣም ያስደስተናል! በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ (1) ሚስቶች የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (2) አንዲት ሚስት ለባሏ ለመገዛት ፈቃደኛ የምትሆነው ለምንድን ነው? (3) ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች መገዛትን በተመለከተ ከኢየሱስ፣ ከአቢጋኤል እንዲሁም የዮሴፍ ሚስትና የኢየሱስ እናት ከሆነችው ከማርያም ምን ሊማሩ ይችላሉ?
ክርስቲያን ሚስቶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?
3. ፍጹም የሆነ ትዳር የለም የምንለው ለምንድን ነው?
3 ትዳር ፍጹም የሆነ የአምላክ ስጦታ ነው፤ ሰዎች ግን ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐ. 1:8) የአምላክ ቃል፣ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በመግለጽ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው የሚያስጠነቅቃቸው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 7:28) አንዲትን ሚስት ሊያጋጥሟት የሚችሉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እስቲ እንመልከት።
4. አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት ዝቅ እንደሚያደርጋት እንዲሰማት የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
4 አንዲት ሚስት በአስተዳደጓ የተነሳ ለባሏ መገዛት ዝቅ እንደሚያደርጋት ሊሰማት ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ማሪሶል እንዲህ ብላለች፦ “ባደግኩበት አካባቢ ሴቶች በምንም ነገር ከወንዶች ማነስ እንደሌለባቸው ሁልጊዜ ይነገራቸው ነበር። የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ይሖዋ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ሴቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ቢጠብቅባቸውም በትዳር ውስጥ የተከበረ ድርሻ እንዳላቸውም እረዳለሁ። ሆኖም የራስነት ሥርዓትን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የሚከብደኝ ጊዜ አለ።”
5. ሴቶች በትዳር ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በተመለከተ አንዳንዶች ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት አላቸው?
5 በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት፣ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ባል ይኖራት ይሆናል። በደቡብ አሜሪካ የምትኖር ኢቮን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በእኛ አካባቢ ሴቶች የሚበሉት ወንዶች ከበሉ በኋላ ነው። በቤት ውስጥ ሴቶች ልጆች ምግብ እንዲያበስሉና እንዲያጸዱ ይጠበቅባቸዋል፤ ወንዶች ልጆች ግን እናቶቻቸውና እህቶቻቸው የፈለጉትን ነገር ያደርጉላቸዋል፤ የቤቱ ንጉሥ እንደሆኑም ይነገራቸዋል።” በእስያ የምትኖር ዪንግሊንግ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በእኛ ቋንቋ ‘ሴቶች ብሩህ አእምሮ ወይም ክህሎቶች አያስፈልጓቸውም’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ አንድ አባባል አለ። ሚስቶች የቤት ውስጥ ሥራ ከማከናወን ውጭ ለባሎቻቸው ምንም ዓይነት ሐሳብ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም።” እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የጎደለውና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት ተጽዕኖ ያሳደረበት አንድ ባል የሚስቱን ሕይወት መራራ ያደርግባታል፤ ይህ አመለካከት ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ጋር የሚቃረን ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ያሳዝነዋል።—ኤፌ. 5:28, 29፤ 1 ጴጥ. 3:7
6. ሚስቶች ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የመሠረቱትን ወዳጅነት ለማጠናከር ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
6 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ ክርስቲያን ባሎች የቤተሰቡን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ይጠብቅባቸዋል። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም ያገቡ እህቶች በየቀኑ የአምላክን ቃል ለማንበብና ባነበቡት ነገር ላይ ለማሰላሰል እንዲሁም ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት ለማቅረብ ከተጣበበው ፕሮግራማቸው ላይ የተወሰነ ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል። ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሚስቶች ሥራ ስለሚበዛባቸው እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ጊዜም ሆነ አቅም እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል፤ ሆኖም ጊዜ መድበው እንዲህ ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እያንዳንዳችን ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት እንድንመሠርትና ይህን ወዳጅነት ጠብቀን እንድንኖር ይፈልጋል።—ሥራ 17:27
7. አንዲት ሚስት ይሖዋ የሰጣትን ድርሻ መወጣት ቀላል እንዲሆንላት የሚያደርገው ምንድን ነው?
7 አንዲት ሚስት ፍጹም ላልሆነው ባሏ መገዛት ብዙ ጥረት ቢጠይቅባት የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና ለባሏ እንድትገዛ የሚያነሳሷትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ማወቋና አምና መቀበሏ ይሖዋ የሰጣትን ድርሻ መወጣት ቀላል እንዲሆንላት ያደርጋል።
አንዲት ሚስት ለመገዛት ፈቃደኛ የምትሆነው ለምንድን ነው?
8. በኤፌሶን 5:22-24 ላይ በተገለጸው መሠረት አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለባሏ ለመገዛት ፈቃደኛ የምትሆነው ለምንድን ነው?
8 አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለባሏ ለመገዛት ፈቃደኛ የምትሆነው ይሖዋ እንዲህ እንድታደርግ ስለሚጠብቅባት ነው። (ኤፌሶን 5:22-24ን አንብብ።) ሰማያዊ አባቷን ታምነዋለች፤ ምክንያቱም ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ እንደሆነና የሚጠቅማት ባይሆን ኖሮ አንድን ነገር እንድታደርግ እንደማይጠይቃት ታውቃለች።—ዘዳ. 6:24፤ 1 ዮሐ. 5:3
9. አንዲት ክርስቲያን እህት የባሏን ሥልጣን ማክበሯ ምን ውጤት አለው?
9 ዓለም፣ ሴቶች የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ እንዲሉ ያበረታታል፤ እንዲሁም ለባል መገዛት ሴቶችን ዝቅ ያደርጋል የሚለውን አመለካከት ያስፋፋል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለውን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን አያውቁም። ይሖዋ መቼም ቢሆን የሚወዳቸው ሴቶች ልጆቹ ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ የሚያደርግ ትእዛዝ እንዲፈጽሙ አይጠብቅባቸውም። ይሖዋ የሰጣትን ድርሻ ለመወጣት የቻለችውን ያህል ጥረት የምታደርግ አንዲት ሚስት በቤተሰቧ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ታደርጋለች። (መዝ. 119:165) ባሏ፣ እሷም ሆነች ልጆቿ ይጠቀማሉ።
10. ካሮል ከሰጠችው ሐሳብ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
10 ፍጹም ላልሆነው ባሏ የምትገዛ ሚስት የራስነት ሥርዓትን ላቋቋመው ለይሖዋ ፍቅርና አክብሮት እንዳላት ታሳያለች። በደቡብ አሜሪካ የምትኖረው ካሮል እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ስህተት እንደሚሠራ አውቃለሁ፤ እሱ ለሚሠራቸው ስህተቶች የምሰጠው ምላሽ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ምን ያህል ከፍ አድርጌ እንደምመለከት እንደሚያሳይም አውቃለሁ። ስለዚህ በሰማይ ያለውን አባቴን ለማስደሰት ስል ምንጊዜም ተገዢ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ።”
11. አኒስ የተባለች አንዲት እህት ይቅር ባይ እንድትሆን የረዳት ምንድን ነው? እሷ ከሰጠችው ሐሳብስ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
11 አንዲት ሚስት ባሏ ለስሜቷና ለሚያሳስቧት ነገሮች ግድ እንደሌለው የሚሰማት ከሆነ እሱን ማክበርና ለእሱ መገዛት ተፈታታኝ ሊሆንባት ይችላል። ባለትዳር የሆነች አኒስ የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማት ምን እንደምታደርግ እስቲ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “በጉዳዩ ላለመበሳጨት ጥረት አደርጋለሁ። ሁላችንም ስህተት እንደምንሠራ ለማስታወስ እሞክራለሁ። ሁልጊዜም ግብ የማደርገው እንደ ይሖዋ በነፃ ይቅር ለማለት ነው። ይቅር ማለቴ ደግሞ የአእምሮ ሰላሜ እንዲመለስ ያደርጋል።” (መዝ. 86:5) ይቅር ባይ የሆነች ሚስት ብዙውን ጊዜ ለባሏ መገዛት ቀላል ይሆንላታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
12. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ዓይነት ምሳሌዎች እናገኛለን?
12 አንዳንዶች መገዛት የድክመት ምልክት እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይህ አመለካከት ግን ፈጽሞ ከእውነታው
የራቀ ነው። ጠንካራ የሆኑ ሆኖም ለሌሎች በመገዛት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ብዙ ሰዎች አሉ። እስቲ ከኢየሱስ፣ ከአቢጋኤልና ከማርያም ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።13. ኢየሱስ ለይሖዋ የሚገዛው ለምንድን ነው? አብራራ።
13 ኢየሱስ ለይሖዋ ይገዛል፤ ይህን የሚያደርገው ግን የማሰብ ችሎታው ወይም ክህሎቱ ዝቅተኛ ስለሆነ አይደለም። ኢየሱስ በጣም ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተማሩ በራሱ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለው ያሳያል። (ዮሐ. 7:45, 46) ይሖዋ ጽንፈ ዓለምን በፈጠረበት ወቅት ኢየሱስ አብሮት እንዲሠራ የፈቀደለት ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው ስለሚያውቅ ነው። (ምሳሌ 8:30፤ ዕብ. 1:2-4) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ይሖዋ ‘በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል።’ (ማቴ. 28:18) ኢየሱስ ከፍተኛ ችሎታ ቢኖረውም ከይሖዋ መመሪያ ይጠይቃል። ለምን? ምክንያቱም አባቱን ይወደዋል።—ዮሐ. 14:31
14. (ሀ) ባሎች ይሖዋ ለሴቶች ካለው አመለካከት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? (ለ) ባሎች በምሳሌ 31 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
14 ባሎች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ይሖዋ ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ያዘዘው ሴቶችን ከወንዶች ዝቅ አድርጎ ስለሚመለከት አይደለም። ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች እንዲሆኑ ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም መምረጡ በራሱ ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። (ገላ. 3:26-29) ይሖዋ ለልጁ ሥልጣን በመስጠት እንደሚተማመንበት አሳይቷል። በተመሳሳይም ጥበበኛ የሆነ አንድ ባል ለሚስቱ አንዳንድ ኃላፊነቶች ይሰጣል። የአምላክ ቃል፣ አንዲት ባለሙያ ሚስት ስላላት ድርሻ ሲናገር የቤቱን ሥራ በኃላፊነት እንደምትከታተል፣ መሬት እንደምትገዛና እንደምታስተዳድር እንዲሁም እንደምትነግድ ይገልጻል። (ምሳሌ 31:15, 16, 18ን አንብብ።) ይህች ሚስት ሐሳቧን የመግለጽ ነፃነት እንደሌላት ባሪያ አይደለችም። ከዚህ ይልቅ ባሏ እምነት ይጥልባታል፤ እንዲሁም የምትሰጠውን ሐሳብ ያዳምጣል። (ምሳሌ 31:11, 26, 27ን አንብብ።) አንድ ባል ሚስቱን እንዲህ በአክብሮት የሚይዛት ከሆነ ለእሱ መገዛት አስደሳች ይሆንላታል።
15. ሚስቶች ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
15 ሚስቶች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮችን ያከናወነ ቢሆንም ለይሖዋ የራስነት ሥልጣን መገዛቱ ዝቅ እንደሚያደርገው አልተሰማውም። (1 ቆሮ. 15:28፤ ፊልጵ. 2:5, 6) በተመሳሳይም የኢየሱስን ምሳሌ የምትከተል አንዲት ባለሙያ ሚስት ለባሏ መገዛቷ ዝቅ እንደሚያደርጋት አይሰማትም። ባሏን የምትደግፈው እሱን ስለምትወደው ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት ይሖዋን ስለምትወድና ስለምታከብር ነው።
16. በአንደኛ ሳሙኤል 25:3, 23-28 ላይ እንደተገለጸው አቢጋኤል ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተጋፍጣለች? (ሽፋኑን ተመልከት።)
16 አቢጋኤል ናባል የተባለ ባል ነበራት። ናባል ራስ ወዳድ፣ ኩሩና ምስጋና ቢስ ሰው ነበር። ያም ቢሆን አቢጋኤል ከዚህ ትዳር የምትገላገልበትን አቋራጭ መንገድ አልፈለገችም። ዳዊትና ሰዎቹ ናባልን ሊገድሉ እየመጡ እንደሆነ ስትሰማ ዝም ልትል ትችል ነበር። እሷ ግን ናባልንና ሌሎቹን የቤተሰቡን አባላት ለመታደግ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደች። አቢጋኤል 400 በሚሆኑ የታጠቁ ወንዶች ፊት መቅረብና ዳዊትን በአክብሮት ማሳመን ምን ያህል ድፍረት ጠይቆባት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ለባሏ ጥፋት ራሷን ተጠያቂ ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ ሆናለች። (1 ሳሙኤል 25:3, 23-28ን አንብብ።) ዳዊት፣ ይሖዋ በዚህች ጠንካራ ሴት ተጠቅሞ ከባድ ስህተት ከመፈጸም እንዲቆጠብ የሚያደርግ አስፈላጊ ምክር እንደሰጠው አምኖ ተቀብሏል።
17. ባሎች ስለ ዳዊትና ስለ አቢጋኤል ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
17 ባሎች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? አቢጋኤል አስተዋይ ሴት ነበረች። ዳዊት ምክሯን መስማቱ ጠቅሞታል። የደም ባለዕዳ ሊያደርገው ከሚችል ድርጊት ጠብቆታል። በተመሳሳይም አስተዋይ የሆነ ባል አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት ሚስቱ የምትሰጠውን አስተያየት በቁም ነገር ያስብበታል። የእሷን አስተያየት መስማቱ የሞኝነት ውሳኔ ከማድረግ ሊጠብቀው ይችላል።
18. ሚስቶች አቢጋኤል ከተወችው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
1 ጴጥ. 3:1, 2) መልካም ምግባሯ በባሏ ላይ ለውጥ ባያመጣም እንኳ ይሖዋ ለባሏ በመገዛት የምታሳየውን ታማኝነት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኛ መሆን ትችላለች።
18 ሚስቶች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? አንዲት ሚስት ይሖዋን መውደዷና ማክበሯ በቤተሰቧ ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ ባሏ አማኝ ባይሆን ወይም የይሖዋን መሥፈርቶች ባይከተልም እንኳ እንዲህ ማድረጓ ጠቃሚ ነው። ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ምክንያት ከትዳሯ ለመገላገል አትሞክርም። ከዚህ ይልቅ ባሏን በማክበርና ለእሱ በመገዛት ስለ ይሖዋ ለማወቅ እንዲነሳሳ ልታደርገው ትሞክራለች። (19. አንዲት ሚስት ለባሏ የማትታዘዘው ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሟት ነው?
19 ሆኖም ለባሏ የምትገዛ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ባሏ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ነገር እንድታደርግ ቢጠይቃት ከእሱ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አትሆንም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት የማያምን ባሏ እንድትዋሽ፣ እንድትሰርቅ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ሌላ ነገር እንድታደርግ ሊጠይቃት ይችላል። ያገቡ እህቶችን ጨምሮ ሁሉም ክርስቲያኖች በዋነኝነት ታዛዥ የሚሆኑት ለይሖዋ ነው። አንዲት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥስ ነገር እንድታደርግ ብትጠየቅ ፈቃደኛ እንዳልሆነች መግለጽ ይኖርባታል፤ እንደዚያ የማታደርግበትን ምክንያት በደግነት ሆኖም በቆራጥነት ማስረዳት ትችላለች።—ሥራ 5:29
20. ማርያም ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ወዳጅነት መሥርታ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
20 ማርያም ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ወዳጅነት መሥርታ ነበር። ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ከሆነችው ከኤልሳቤጥ ጋር በተነጋገረችበት ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ከ20 ጊዜ በላይ ጠቅሳለች። (ሉቃስ 1:46-55) እስቲ ሌላም ሐሳብ እንመልከት፤ ማርያም ለዮሴፍ የታጨች ቢሆንም የይሖዋ መልአክ መጀመሪያ የተገለጠው ለእሱ አልነበረም። መልአኩ መጀመሪያ በቀጥታ ያነጋገረው ማርያምን ሲሆን የአምላክን ልጅ እንደምትወልድ አብስሯታል። (ሉቃስ 1:26-33) ይሖዋ ማርያምን በሚገባ ያውቃት ነበር፤ ልጁን በፍቅርና በእንክብካቤ እንደምታሳድግለት እምነት ጥሎባታል። ማርያምም ብትሆን ኢየሱስ ከሞተና ተነስቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም እንኳ ከይሖዋ ጋር ያላትን ጥሩ ዝምድና ጠብቃ እንደኖረች ምንም ጥርጥር የለውም።—ሥራ 1:14
21. ባሎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም ከሚናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
21 ባሎች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ጥበበኛ የሆነ ባል፣ ሚስቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ በማወቋ ደስተኛ ነው። በሚስቱ እንደተበለጠ ወይም ቦታውን እንደወሰደችበት አይሰማውም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥሩ እውቀት ያላት ሚስት ለቤተሰቧ በረከት እንደሆነች ይገነዘባል። እርግጥ ነው፣ አንዲት ሚስት ከባሏ የበለጠ እውቀት ቢኖራትም እንኳ በቤተሰብ አምልኮና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነት የባልየው ነው።—22. ሚስቶች ከማርያም ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
22 ሚስቶች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት ቢጠበቅባትም መንፈሳዊነቷን መንከባከብ የራሷ ኃላፊነት ነው። (ገላ. 6:5) ይህን ለማድረግ ደግሞ ለግል ጥናትና ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ መመደብ ይኖርባታል። ይህም ለይሖዋ ያላትን ፍቅርና አክብሮት ጠብቃ ለመኖር እንዲሁም ለባሏ በደስታ ለመገዛት ይረዳታል።
23. ለባሎቻቸው የሚገዙ ሚስቶች ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንም ሆነ ጉባኤውን የሚጠቅሙት እንዴት ነው?
23 ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ምንጊዜም ለባሎቻቸው ለመገዛት ጥረት የሚያደርጉ ሚስቶች ደስታና እርካታ ይኖራቸዋል፤ ይሖዋ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነት ደስታ የላቸውም። ለባሎቻቸው የሚገዙ ሚስቶች ለወጣት ወንዶችም ሆነ ለወጣት ሴቶች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። በቤተሰባቸው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጉባኤው ውስጥም ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ቲቶ 2:3-5) በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መካከል አብላጫውን ቦታ የሚይዙት ሴቶች ናቸው። (መዝ. 68:11) ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሁላችንም በጉባኤው ውስጥ አስፈላጊ ድርሻ እናበረክታለን። ቀጣዩ ርዕስ እያንዳንዳችን ይህን ድርሻችንን መወጣት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
መዝሙር 131 “አምላክ ያጣመረውን”
^ አን.5 ይሖዋ አንዲት ሚስት ለባሏ እንድትገዛ ይጠብቅባታል። ሆኖም ይህ ምን ማለት ነው? ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ከኢየሱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሴቶች መገዛትን በተመለከተ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።