ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን የሚያመጣው እውነት
“በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።”—ማቴ. 10:34
1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ሰላም በማግኘት ተባርከናል? (ለ) በዚህ ዘመን የተሟላ ሰላም እንዳናገኝ እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
ሁላችንም ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሰላማዊ ሕይወት መምራት እንፈልጋለን። በመሆኑም ይሖዋ ከሚረብሹ ሐሳቦችና ከአሉታዊ ስሜቶች የሚጠብቀንን “የአምላክ ሰላም” በመስጠት ውስጣዊ መረጋጋት እንዲኖረን ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! (ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም ራሳችንን ለይሖዋ ስለወሰንን ‘ከአምላክ ጋር ሰላም’ ሊኖረን ማለትም ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ልንመሠርት ችለናል።—ሮም 5:1
2 ይሁንና አምላክ በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ሰላምን የሚያሰፍንበት ጊዜ ገና አልመጣም። የምንኖረው በዓይነቱ ልዩ በሆነውና በግጭት በተሞላው የመጨረሻው ዘመን ውስጥ ስለሆነ በርካታ ሰዎች የጠበኝነት ባሕርይ ማንጸባረቅ ይቀናቸዋል። (2 ጢሞ. 3:1-4) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሰይጣንን እንዲሁም እሱ የሚያስፋፋቸውን የሐሰት ትምህርቶች ለመቃወም መንፈሳዊ ውጊያ ማካሄድ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 10:4, 5) ሰላማችንን የሚያውከው ትልቁ ምክንያት ግን ከማያምኑ ቤተሰቦቻችን የሚመጣው ተቃውሞ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ቤተሰቦቻችን በእምነታችን ሊያፌዙብን፣ ቤተሰብን እንደምንከፋፍል አድርገው ሊናገሩ ወይም እምነታችንን ካልካድን እንደ ቤተሰቡ አባል አድርገው እንደማይቀበሉን ሊገልጹ ይችላሉ። ታዲያ ከቤተሰብ ለሚሰነዘር ተቃውሞ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እንዲህ ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ በተሳካ መንገድ ተቋቁመን ማለፍ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ከቤተሰብ ለሚሰነዘር ተቃውሞ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
3, 4. (ሀ) የኢየሱስ ትምህርቶች ምን ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ? (ለ) ኢየሱስን መከተል ይበልጥ ከባድ የሚሆነው መቼ ነው?
3 ኢየሱስ እሱ የሚያስተምረው ትምህርት በሰዎች መካከል ክፍፍል እንደሚፈጥር እንዲሁም ተከታዮቹ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው እሱን መከተላቸውን ለመቀጠል ድፍረት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። እንዲህ ያለው ተቃውሞ በቤተሰብ መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ሊያደፈርስ ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም። እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ምራትን ከአማቷ ለመለያየት ነው። በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ።”—ማቴ. 10:34-36
4 ኢየሱስ “ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ” ሲል ደቀ መዛሙርቱ እሱን መከተል ስለሚያስከትለው ውጤት ማሰብ እንዳለባቸው ማስገንዘቡ ነበር። የኢየሱስ ትምህርት በሰዎች መካከል ክፍፍል ሊፈጥር ይችላል። እርግጥ ነው፣ የኢየሱስ ዓላማ የአምላክን የእውነት መልእክት ማወጅ እንጂ በሰዎች መካከል ቅራኔ መፍጠር አልነበረም። (ዮሐ. 18:37) ያም ቢሆን የአንድ ሰው የቅርብ ወዳጆች ወይም ቤተሰቦች እውነትን ለመቀበል ፈቃደኞች ካልሆኑ ይህ ሰው የክርስቶስን ትምህርቶች በታማኝነት መከተል ከባድ ሊሆንበት ይችላል።
5. የክርስቶስ ተከታዮች ምን ደርሶባቸዋል?
5 ኢየሱስ ተከታዮቹ በጽናት ተቋቁመው ማለፍ ከሚያስፈልጋቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል የቤተሰብ ተቃውሞ እንደሚገኝበት ገልጿል። (ማቴ. 10:38) ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ሲሉ ከቤተሰቦቻቸው የሚሰነዘርባቸውን ፌዝ ተቋቁመው መጽናት አስፈልጓቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በቤተሰቦቻቸው እስከመገለል ደርሰዋል። ያም ቢሆን ያገኙት በረከት የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ካጡት ነገር በእጅጉ የላቀ ነው።—ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።
6. ቤተሰቦቻችን ይሖዋን ለማምለክ የምናደርገውን ጥረት በሚቃወሙበት ጊዜ የትኞቹን ነገሮች መዘንጋት አይኖርብንም?
6 ቤተሰቦቻችን ይሖዋን ለማምለክ የምናደርገውን ጥረት ቢቃወሙም ይህ ለእነሱ ያለንን ፍቅር አይቀንሰውም፤ ይሁንና ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ለማንኛውም ሰው ካለን ፍቅር ሊበልጥ እንደሚገባ መዘንጋት አይኖርብንም። (ማቴ. 10:37) በተጨማሪም ሰይጣን ለቤተሰባችን ያለንን ፍቅር ተጠቅሞ ንጹሕ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ እንደሚሞክር ልንገነዘብ ይገባል። በቤተሰብ ውስጥ ተቃውሞ ሊያጋጥመን የሚችለው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
የማያምን የትዳር ጓደኛ
7. የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ክርስቲያኖች ላሉበት ሁኔታ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
7 መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (1 ቆሮ. 7:28) የማያምን የትዳር ጓደኛ ባላቸው ክርስቲያኖች ትዳር ውስጥ የሚፈጠረው ውጥረትና ጭንቀት ደግሞ የከፋ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን፣ ያሉበትን ሁኔታ ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ማየታቸው አስፈላጊ ነው። የትዳር ጓደኛችሁ ክርስቶስን ለመከተል ፈቃደኛ አለመሆኑ ብቻውን፣ ለመለያየት ወይም ለፍቺ መሠረት ሊሆን አይችልም። (1 ቆሮ. 7:12-16) አንድ የማያምን ባል ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለበትን ኃላፊነት ላይወጣ ቢችልም የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ መጠን ሊከበር ይገባዋል። የማታምን ሚስት ያለው ክርስቲያን ባልም ለሚስቱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ጥልቅ ፍቅር ሊያሳያት ይገባል።—ኤፌ. 5:22, 23, 28, 29
8. የትዳር ጓደኛችሁ ለይሖዋ በምታቀርቡት አገልግሎት ላይ ገደብ ለመጣል ቢሞክር የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችሁን መጠየቃችሁ ጠቃሚ ነው?
8 የትዳር ጓደኛችሁ ለይሖዋ በምታቀርቡት አገልግሎት ላይ ገደብ ለመጣል ቢሞክርስ? ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት ባሏ አገልግሎት መውጣት የምትችለው በተወሰኑ ቀናት ላይ ብቻ እንደሆነ ነግሯት ነበር። እናንተም ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ራሳችሁን እንደሚከተለው በማለት ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ ጨርሶ ይሖዋን እንዳላመልክ እየከለከለኝ ነው? ካልሆነ እሱ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበል እችል ይሆን?’ ምክንያታዊ ፊልጵ. 4:5
መሆናችሁ በትዳራችሁ ውስጥ አላስፈላጊ ቅራኔ እንዳይፈጠር ይረዳችኋል።—9. የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ክርስቲያኖች ልጆቻቸው ለማያምነው ወላጃቸው አክብሮት እንዲኖራቸው ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
9 የማያምን የትዳር ጓደኛ ካላችሁ በተለይም ልጆችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ እናንተ “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እንዲታዘዙ ልጆቻችሁን ማስተማር ትፈልጋላችሁ። (ኤፌ. 6:1-3) ይሁንና የትዳር ጓደኛችሁ ላቅ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የማይከተል ቢሆንስ? የትዳር ጓደኛችሁን በማክበር ምሳሌ ሁኑ። የትዳር ጓደኛችሁ ባሉት ጥሩ ጎኖች ላይ ትኩረት አድርጉ፤ እንዲሁም ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁን አድናቆት ግለጹ። በልጆቻችሁ ፊት ስለ ትዳር ጓደኛችሁ አሉታዊ ነገሮችን ከመናገር ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ይሖዋን ለማምለክም ሆነ ላለማምለክ የመምረጥ ነፃነት እንዳለው አስረዷቸው። ልጆቹ የሚያሳዩት መልካም ምግባር የማያምነው የትዳር ጓደኛችሁ ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳብ ሊያደርግ ይችላል።
10. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
10 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የማያምነው የትዳር ጓደኛ ልጆቹ የሐሰት ሃይማኖት በዓላትን ማክበር አሊያም የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን መማር አለባቸው የሚል አቋም ሊይዝ ይችላል። አንዳንድ ባሎች ክርስቲያን ሚስቶቻቸው ለልጆቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያስተምሩ ሊከለክሉ ይችላሉ። ያም ቢሆን አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለልጆቿ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር የቻለችውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርባታል። (ሥራ 16:1፤ 2 ጢሞ. 3:14, 15) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የማያምን ባል የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ሚስቱ መደበኛ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ለልጆቹ እንዳታስጠና ወይም ልጆቹን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛ እንዳትሄድ ሊከለክላት ይችላል። በዚህ ጊዜ እህት የባሏን ውሳኔ ብታከብርም ያገኘችውን አጋጣሚ ተጠቅማ ለልጆቿ ስለምታምንበት ነገር ለመናገር ጥረት ታደርጋለች፤ እንዲህ በማድረግ ልጆቿ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ማሠልጠንና ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ መርዳት ትችላለች። (ሥራ 4:19, 20) እርግጥ ነው፣ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ልጆቹ ውሎ አድሮ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ እንዳለባቸው የታወቀ ነው።—ዘዳ. 30:19, 20 *
ቤተሰቦቻችን እውነተኛውን አምልኮ በሚቃወሙበት ጊዜ
11. የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ቤተሰቦቻችን ጋር ቅራኔ እንዲፈጠር የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
11 መጀመሪያ ላይ፣ ለቤተሰቦቻችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመርን አልነገርናቸው ይሆናል። እምነታችን እየጠነከረ ሲሄድ ግን ስለምናምንበት ነገር መናገር እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። (ማር. 8:38) በዚህ ረገድ ቆራጥ አቋም መያዝህ በአንተና በማያምኑት ቤተሰቦችህ መካከል ችግር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፤ ከሆነ ከዚህ በታች የተጠቀሱት ነጥቦች ንጹሕ አቋምህን ሳታላላ ከቤተሰብህ ጋር የሚፈጠረውን ቅራኔ መቀነስ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁሙሃል።
12. የማያምኑ ቤተሰቦቻችን የሚቃወሙን ለምን ሊሆን ይችላል? ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
12 የማያምኑ ቤተሰቦቻችሁን ስሜት ለመረዳት ጥረት አድርጉ። እኛ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመማራችን በጣም እንደምንደሰት የታወቀ ነው፤ ቤተሰቦቻችን ግን እንደተታለልን ወይም የመናፍቃን ቡድን አባል እንደሆንን አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። በዓላትን አብረናቸው ስለማናከብር ለእነሱ ያለን ፍቅር እንደቀነሰ ሊሰማቸው ይችላል። አልፎ ተርፎም በያዝነው አቋም የተነሳ አምላክ እንደሚቀጣን በማሰብ ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። በመሆኑም ራሳችንን በእነሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንዲሁም በእርግጥ ያስጨነቃቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በትኩረት ማዳመጥ ይኖርብናል። (ምሳሌ 20:5) ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ምሥራቹን ለማካፈል ሲል የእያንዳንዱን ሰው ስሜት ለመረዳት ጥረት ያደርግ ነበር፤ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው።—1 ቆሮ. 9:19-23
13. የማያምኑ ቤተሰቦቻችንን እንዴት ልናነጋግራቸው ይገባል?
13 በለዘበ አንደበት አነጋግሯቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን” ይላል። (ቆላ. 4:6) ከቤተሰቦቻችን ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማንጸባረቅ እንድንችል ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ እንችላለን። እያንዳንዱን የሐሰት ሃይማኖት ትምህርት እያነሳን ከእነሱ ጋር መከራከር አይኖርብንም። አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻችን በንግግራቸው ወይም በድርጊታቸው ሊጎዱን ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሲሰድቡን እንባርካለን፤ ስደት ሲያደርሱብን በትዕግሥት እናሳልፋለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ በለዘበ አንደበት እንመልሳለን።”—1 ቆሮ. 4:12, 13
14. ምንጊዜም መልካም ምግባር ማሳየት ምን ጥቅም አለው?
14 ምንጊዜም መልካም ምግባር ይኑራችሁ። ተቃዋሚ የሆኑ ቤተሰቦቻችንን በለዘበ አንደበት ማነጋገራችን ከእነሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳ ቢሆንም የበለጠ ውጤት የሚያስገኘው ግን የምናሳየው መልካም ምግባር ነው። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2, 16ን አንብብ።) በመሆኑም ቤተሰቦችህ የይሖዋ ምሥክሮች አስደሳች ትዳር እንዳላቸው፣ ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው እንደሚያሳድጉ፣ ንጹሖችና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ እንዲሁም አርኪ ሕይወት እንደሚመሩ ከግል ሕይወትህ መመልከት እንዲችሉ አድርግ። ቤተሰቦችህ ወደ እውነት ባይመጡ እንኳ ታማኝ በመሆን ይሖዋን እንዳስደሰትከው ማወቅህ እርካታ ይሰጥሃል።
15. ቅራኔ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስቀረት አስቀድመን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
15 አስቀድማችሁ ተዘጋጁ። ቅራኔ ሊፈጥሩ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ እንደሆኑና እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት ልትይዟቸው እንደሚገባ አስቀድማችሁ አስቡ። (ምሳሌ 12:16, 23) በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የባለቤቴ አባት እውነትን በጣም ይቃወም ነበር። በመሆኑም እኔና ባለቤቴ እሱን ልንጠይቀው ከመደወላችን በፊት ወደ ይሖዋ እንጸልያለን፤ እንዲህ የምናደርገው የባለቤቴ አባት ተቆጥቶ በሚናገርበት ወቅት አጸፋውን እንዳንመልስ ይሖዋ እንዲረዳን ነው። በተጨማሪም ጥሩ ጭውውት ማድረግ እንድንችል ልንወያይባቸው የምንችላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች አስቀድመን ለማሰብ እንሞክራለን። ስለ ሃይማኖት የጦፈ ክርክር ውስጥ መግባት ስለማንፈልግ ከእሱ ጋር በምናወራበት ጊዜ ላይ ገደብ እናበጃለን።”
16. ከቤተሰብህ ጋር በመጋጨትህ የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ለማሸነፍ ምን ሊረዳህ ይችላል?
16 እርግጥ ነው፣ ከማያምኑ ቤተሰቦቻችሁ ጋር ሊያጋጯችሁ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደማትችሉ የታወቀ ነው። ቤተሰቦቻችሁን ስለምትወዷቸውና ምንጊዜም እነሱን ማስደሰት ስለምትፈልጉ ከእነሱ ጋር የሚያጋጫችሁ ሁኔታ ሲፈጠር የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። በዚህ ወቅት፣ ለቤተሰባችሁ ያላችሁ ፍቅር ለይሖዋ ካላችሁ ታማኝነት በልጦ እንዳይገኝ ልትጠነቀቁ ይገባል። እንዲህ ያለ አቋም መያዛችሁ ቤተሰቦቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትን ተግባራዊ ማድረግ መቼም ቢሆን ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። ደግሞም ሌሎች እውነትን እንዲቀበሉ ማስገደድ እንደማትችሉ ማስታወስ ይኖርባችኋል። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በአኗኗራችሁ እንዲታይ አድርጉ። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም እሱን የማምለክ ምርጫ አቅርቦላቸዋል።—ኢሳ. 48:17, 18
የቤተሰባችን አባል ይሖዋን ማምለኩን ሲተው
17, 18. የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ማምለኩን በሚተውበት ጊዜ የሚሰማችሁን ሐዘን ለመቋቋም ምን ሊረዳችሁ ይችላል?
17 የቤተሰባችን አባል ከጉባኤ በሚወገድበት ወይም ራሱን በሚያገልበት ጊዜ በከባድ ሐዘን ልንዋጥ እንችላለን። በዚህ ወቅት የሚሰማንን ሐዘን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
18 መንፈሳዊ ልማዶቻችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ። አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት በመካፈልና ለመጽናት የሚያስችላችሁን ኃይል እንዲሰጣችሁ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ራሳችሁን ለመገንባት ጥረት አድርጉ። (ይሁዳ 20, 21) ይሁንና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርጉም የሚሰማችሁን ሐዘን መቋቋም ቢከብዳችሁስ? ተስፋ አትቁረጡ! ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ያላችሁ መሆኑ አስተሳሰባችሁንና ስሜታችሁን ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል። የመዝሙር 73 ጸሐፊ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። ይህ ግለሰብ የተሳሳተ አመለካከት በመያዙ ምክንያት በጣም የተረበሸበት ወቅት ነበር፤ ይሁንና ወደ አምላክ መቅደስ መግባቱ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረድቶታል። (መዝ. 73:16, 17) ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችሁን መቀጠላችሁ እናንተንም ሊረዳችሁ ይችላል።
19. ለይሖዋ ተግሣጽ አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
19 ለይሖዋ ተግሣጽ አክብሮት ይኑራችሁ። ይሖዋ የሚሰጠው ተግሣጽ ለጊዜው የሚያም ቢሆንም ውሎ አድሮ ተግሣጽ የተሰጠውን ግለሰብ ጨምሮ ለሁሉም ሰው የተሻለ ጥቅም ያስገኛል። (ዕብራውያን 12:11ን አንብብ።) ይሖዋ ንስሐ ከማይገቡ ኃጢአተኞች ጋር ‘መግጠማችንን እንድንተው’ አዞናል። (1 ቆሮ. 5:11-13) ይህን ትእዛዝ መከተል ከባድ ሊሆንብን ቢችልም ከተወገደ የቤተሰባችን አባል ጋር በስልክ፣ በጽሑፍ መልእክት፣ በደብዳቤ፣ በኢሜይል ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት አላስፈላጊ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል።
20. ምን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?
20 ተስፋ አትቁረጡ። ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል”፤ በመሆኑም ይሖዋን ማምለኩን የተወ የቤተሰባችን አባል አንድ ቀን ወደ ይሖዋ ይመለሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 13:7) ከይሖዋ የራቀው የቤተሰባችሁ አባል ለውጥ እያደረገ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ካስተዋላችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ ብርታት እንዲሰጠውና “ወደ እኔ ተመለስ” በማለት ይሖዋ ላቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ልትጸልዩለት ትችላላችሁ።—ኢሳ. 44:22
21. ኢየሱስን በመከተላችሁ ምክንያት ከቤተሰባችሁ ጋር ቅራኔ ከተፈጠረ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?
21 ኢየሱስ ማንኛውንም ሰው ከእሱ የምናስበልጥ ከሆነ የእሱ ተከታዮች ልንሆን እንደማንችል ተናግሯል። የእሱ ደቀ መዛሙርት ግን የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ደፋር በመሆን ለእሱ ታማኞች ሆነው እንደሚቀጥሉ ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስን መከተላችሁ በቤተሰባችሁ ውስጥ “ሰይፍ” አምጥቶ ከሆነ ያጋጠማችሁን ተፈታታኝ ሁኔታ በተሳካ መንገድ ለመቋቋም በይሖዋ ታመኑ፤ እሱ እንዲረዳችሁ በጸሎት ለምኑት። (ኢሳ. 41:10, 13) ይሖዋና ኢየሱስ ደስ እንደሚሰኙባችሁና የታማኝነት ጎዳና በመከተላችሁ እንደሚባርኳችሁ በማወቅ ተደሰቱ።
^ አን.10 በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን ማሠልጠን የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ነሐሴ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።