የጥናት ርዕስ 22
በዓይን ለማይታዩት ውድ ሀብቶች አድናቆት አሳይ
“ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው . . . በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው። የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።”—2 ቆሮ. 4:18
መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር
ማስተዋወቂያ *
1. ኢየሱስ በሰማይ ሀብት ስለ ማከማቸት ምን ብሏል?
በዓይናችን ልናያቸው የማንችላቸው ውድ ሀብቶች አሉ። እንዲያውም ከሁሉ በላይ ውድ የሆኑት ሀብቶች በዓይን የሚታዩ አይደሉም። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ከቁሳዊ ሀብቶች በእጅጉ ስለሚልቁት ሰማያዊ ሀብቶች ገልጿል። ከዚያም “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል” የሚለውን መሠረታዊ እውነታ ተናግሯል። (ማቴ. 6:19-21) ልባችን፣ ውድ አድርገን የምንመለከታቸውን ነገሮች ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይገፋፋናል። ‘በሰማይ ለራሳችን ሀብት’ የምናከማቸው በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም በማትረፍ ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው እንዲህ ያለው ሀብት ፈጽሞ ሊጠፋ ወይም ሊሰረቅ አይችልም።
2. (ሀ) በ2 ቆሮንቶስ 4:17, 18 ላይ ጳውሎስ በምን ላይ እንድናተኩር ማሳሰቢያ ሰጥቶናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ዓይናችን በማይታዩት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር’ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (2 ቆሮንቶስ 4:17, 18ን አንብብ።) የማይታዩት ነገሮች ከተባሉት መካከል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኛቸው በረከቶች ይገኙበታል። በዚህ ርዕስ ላይ በአሁኑ ጊዜ ልናገኛቸው የምንችላቸውን አራት የማይታዩ ሀብቶች እንመለከታለን፤ እነሱም ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት፣ ስጦታ የሆነው የጸሎት መብት፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ እንዲሁም አገልግሎታችንን ስናከናውን ከሰማይ የምናገኘው ድጋፍ ናቸው። ለእነዚህ የማይታዩ ሀብቶች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነም በዚህ ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት
3. በዓይን ከማናያቸው ውድ ሀብቶች ሁሉ የሚልቀው ሀብት የትኛው ነው? ይህን ሀብት እንድናገኝ ያስቻለንስ ምንድን ነው?
3 በዓይን ከማናያቸው ውድ ሀብቶች ሁሉ የሚልቀው ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ነው። (መዝ. 25:14) አምላክ ቅዱስ ሆኖ ሳለ ኃጢአተኛ ከሆኑ የሰው ልጆች ጋር ወዳጅነት መመሥረት የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የቻለው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ የሰው ልጆችን ‘ኃጢአት ስለሚያስወግድ’ ነው። (ዮሐ. 1:29) ይሖዋ ለሰው ልጆች መዳን ለማስገኘት ያለው ዓላማ እንደሚሳካ፣ ቤዛው ከመከፈሉ በፊትም ያውቅ ነበር። አምላክ፣ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ከኖሩ የሰው ልጆች ጋር ወዳጅነት ሊመሠርት የቻለው ለዚህ ነው።—ሮም 3:25
4. በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ አንዳንድ የአምላክ ወዳጆችን ጥቀስ።
4 በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ አንዳንድ የአምላክ ወዳጆችን እስቲ እንመልከት። አብርሃም አስደናቂ እምነት ያሳየ ሰው ነበር። አብርሃም ከሞተ ከ1,000 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ስለ እሱ ሲናገር “ወዳጄ” ብሎታል። (ኢሳ. 41:8) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ሞትም እንኳ ቢሆን ይሖዋን ከቅርብ ወዳጆቹ ሊለየው አይችልም። በይሖዋ ፊት አብርሃም ሕያው ነው። (ሉቃስ 20:37, 38) ሌላው ምሳሌ ደግሞ ኢዮብ ነው። መላእክት በሰማይ በተሰበሰቡበት ጉባኤ ፊት ይሖዋ ስለ ኢዮብ በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ይሖዋ ኢዮብን “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” በማለት ጠርቶታል። (ኢዮብ 1:6-8) ዳንኤል ደግሞ ባዕድ አምልኮ በተስፋፋበት አገር ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። ታዲያ ይሖዋ እሱን በተመለከተ ምን ተሰምቶታል? መላእክት በዕድሜ ለገፋው ለዳንኤል ተገልጠው በአምላክ ዘንድ ‘እጅግ የተወደደ’ እንደሆነ ሦስት ጊዜ ነግረውታል። (ዳን. 9:23፤ 10:11, 19) ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ወዳጆቹን የሚያስነሳበትን ጊዜ እንደሚናፍቅ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።—ኢዮብ 14:15
5. ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
5 በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረቱ ምን ያህል ሰዎች አሉ? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ይህን ማድረግ ችለዋል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በጣም ብዙ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የአምላክ ወዳጆች መሆን እንደሚፈልጉ በምግባራቸው እያሳዩ ነው። ይሖዋ “ከቅኖች ጋር . . . የጠበቀ ወዳጅነት አለው።” (ምሳሌ 3:32) እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር መወዳጀት የቻሉት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ነው። ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ፣ ራሳቸውን ለእሱ ወስነው የሚጠመቁ ሁሉ ወዳጆቹ እንዲሆኑ ፈቅዷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ ከሚበልጠው አካል ጋር “የጠበቀ ወዳጅነት” መመሥረት ችለዋል፤ እኛም እነዚህን አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ ይህን መብት ማግኘት እንችላለን።
6. ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
6 ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከመቶ ዓመት በላይ አምላክን በታማኝነት እንዳገለገሉት እንደ አብርሃምና እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም በታማኝነት መጽናት ይኖርብናል፤ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ስናገለግል ብንቆይም እንኳ በታማኝነት መጽናታችን አስፈላጊ ነው። እንደ ዳንኤል ሁሉ እኛም ከሕይወታችን ይልቅ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ልናስቀድም ይገባል። (ዳን. 6:7, 10, 16, 22) ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ሁኔታውን በይሖዋ እርዳታ በመወጣት ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ጠብቀን መኖር እንችላለን።—ፊልጵ. 4:13
ስጦታ የሆነው የጸሎት መብት
7. (ሀ) ምሳሌ 15:8 እንደሚገልጸው ይሖዋ ስለ ጸሎታችን ምን ይሰማዋል? (ለ) ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?
7 ሌላው በዓይን የማይታይ ውድ ሀብት ጸሎት ነው። የቅርብ ጓደኛሞች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው ይነጋገራሉ። እኛስ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ሊኖረን ይችላል? በሚገባ! ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ያነጋግረናል፤ በቃሉ ላይ ሐሳቡንና ስሜቱን አስፍሮልናል። እኛ ደግሞ በጸሎት አማካኝነት እሱን ልናነጋግረው እንዲሁም ውስጣዊ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ምሳሌ 15:8ን አንብብ።) አፍቃሪ ወዳጅ የሆነው ይሖዋ ጸሎታችንን በመስማት ብቻ ሳይወሰን ምላሽም ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ ለጸሎታችን ፈጣን ምላሽ እናገኛለን። በሌሎች ጊዜያት ግን ለጸሎታችን መልስ ለማግኘት ስለ ጉዳዩ ደጋግመን መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ ለጸሎታችን በትክክለኛው ጊዜና ከሁሉ በተሻለው መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ መተማመን እንችላለን። እርግጥ ነው፣ አምላክ የሚሰጠን ምላሽ እኛ ከጠበቅነው የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመንን ችግር ከማስወገድ ይልቅ ችግሩን “በጽናት መቋቋም” የምንችልበትን ጥበብና ብርታት ይሰጠን ይሆናል።—1 ቆሮ. 10:13
ልናካፍለው እንችላለን። ይሖዋም ቢሆን የእኛን ጸሎት መስማት ያስደስተዋል። (8. ለጸሎት መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
8 በዋጋ ሊተመን ለማይችለው የጸሎት መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ “ዘወትር ጸልዩ” የሚለውን መለኮታዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ ነው። (1 ተሰ. 5:17) ይሖዋ እንድንጸልይ አያስገድደንም። የመምረጥ ነፃነታችንን ስለሚያከብር “ሳትታክቱ ጸልዩ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል። (ሮም 12:12) ስለዚህ በየዕለቱ በተደጋጋሚ በመጸለይ አድናቆታችንን ማሳየት እንችላለን። በእርግጥ በጸሎታችን ውስጥ ይሖዋን ማመስገንና ማወደስ እንዳለብንም መዘንጋት አይኖርብንም።—መዝ. 145:2, 3
9. አንድ ወንድም ስለ ጸሎት ምን ብሏል? አንተስ ስለ ጸሎት ምን ይሰማሃል?
9 ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ባገለገልን መጠን እሱ ለጸሎታችን የሚሰጠውን መልስ የማየት ብዙ አጋጣሚ እናገኛለን፤ ይህም ለጸሎት ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ላለፉት 47 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈል የቆየውን ክሪስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ክሪስ እንዲህ ብሏል፦ “ማለዳ ላይ ይሖዋን በጸሎት በማነጋገር የማሳልፈው ጊዜ በጣም ያስደስተኛል። ጎህ ቀድዶ የፀሐይዋ ብርሃን በጤዛ ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረውን ውብ እይታ እየተመለከትኩ ይሖዋን ማነጋገር መንፈሴን ያድሰዋል! ይህ ሁኔታ፣ ጸሎትን ጨምሮ ይሖዋ ለሰጠኝ ስጦታዎች በሙሉ እሱን እንዳመሰግነው ያነሳሳኛል። በቀኑ መጨረሻ ላይ መጸለዬ ደግሞ ንጹሕ ሕሊና ኖሮኝ ወደ መኝታዬ እንድሄድ ይረዳኛል።”
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ
10. የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደ ውድ ሀብት ልንመለከተው የሚገባው ለምንድን ነው?
10 እንደ ውድ ሀብት ልንመለከተው የሚገባው ሌላው በዓይን የማይታይ ስጦታ፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን ልመና እንድናቀርብ አሳስቦናል። (ሉቃስ 11:9, 13) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንኳ ሊሰጠን ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ሥራ 1:8) ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን በአምላክ መንፈስ እርዳታ ልንወጣው እንችላለን።
11. መንፈስ ቅዱስ በየትኞቹ መንገዶች ይረዳናል?
11 መንፈስ ቅዱስ አምላክን ስናገለግል የሚሰጡንን ሥራዎች ለማከናወን እንድንችል ይረዳናል። የአምላክ መንፈስ፣ ያለንን ተሰጥኦ እና ችሎታ ለማሻሻል ይረዳናል። ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን ለመወጣት ያግዘናል። በሥራችን ጥሩ ውጤት የምናገኘው በራሳችን ችሎታ ሳይሆን በአምላክ መንፈስ እርዳታ መሆኑን እናውቃለን።
12. በመዝሙር 139:23, 24 ላይ እንደተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ምን ለማድረግ እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን?
12 የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ መንፈሱ በውስጣችን ያለን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ ወይም ዝንባሌ ለማወቅ እንዲረዳን መጸለይ ነው። (መዝሙር 139:23, 24ን አንብብ።) እንዲህ ያለውን ልመና ካቀረብን፣ ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት በውስጣችን ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም ዝንባሌ እንድናስተውል ያደርጋል። የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም ዝንባሌ እንዳለን ከተገነዘብን ደግሞ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲህ ያለውን ሐሳብ ወይም ዝንባሌ ለማሸነፍ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን፣ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዳይረዳን ሊያደርግ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል።—ኤፌ. 4:30
13. ለመንፈስ ቅዱስ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ምን ይረዳናል?
13 መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ እያከናወናቸው ባሉት ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለዚህ መንፈስ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ይረዳናል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ይህ ሐሳብ አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ስምንት ሚሊዮን ተኩል የሚሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ መንፈስ እርዳታ ከመላው ምድር ሊሰበሰቡ ችለዋል። በተጨማሪም የምንኖረው በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው፤ ይህም የሆነው የአምላክ መንፈስ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ያሉ ግሩም ባሕርያት እንድናዳብር ስለረዳን ነው። እነዚህ ባሕርያት “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ ውድ ስጦታ ነው!
አገልግሎታችንን ስናከናውን ከሰማይ የምናገኘው ድጋፍ
14. በአገልግሎት ስንካፈል ምን ድጋፍ እናገኛለን?
14 ሌላው የማይታይ ውድ ሀብት፣ ከይሖዋ እና ከድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ጋር “አብረን የምንሠራ” መሆናችን ነው። (2 ቆሮ. 6:1) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል እንዲህ ያለ አጋጣሚ እናገኛለን። ጳውሎስ ራሱንና በዚህ ሥራ የሚካፈሉትን ሰዎች በተመለከተ “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:9) በክርስቲያናዊው አገልግሎት ስንካፈል የኢየሱስም የሥራ ባልደረቦች እንሆናለን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ “እኔ . . . ከእናንተ ጋር ነኝ” እንዳለ አስታውስ። (ማቴ. 28:19, 20) ስለ መላእክትስ ምን ማለት ይቻላል? ‘በምድር ላይ ለሚኖሩ ሁሉ የዘላለም ምሥራች ለማብሰር’ በምናከናውነው ሥራ መላእክት ይመሩናል፤ ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው!—ራእይ 14:6
15. ይሖዋ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ያለውን ጉልህ ድርሻ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።
15 ከሰማይ እንዲህ ያለ ድጋፍ በማግኘታችን ምን ውጤት ሊገኝ ችሏል? የመንግሥቱን ዘር ስንዘራ አንዳንድ ዘሮች በጥሩ ልብ ላይ አርፈው ያድጋሉ። (ማቴ. 13:18, 23) ታዲያ እነዚህ የእውነት ዘሮች እንዲያድጉና ፍሬ እንዲያፈሩ የሚያደርጋቸው ማን ነው? ኢየሱስ “አብ ካልሳበው በቀር” ማንም ሰው የእሱ ተከታይ ሊሆን እንደማይችል ተናግሯል። (ዮሐ. 6:44) ይህን የሚያሳይ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ከተማ ውጭ ተሰብስበው ለነበሩ የተወሰኑ ሴቶች በሰበከበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ሴቶች መካከል ሊዲያ ስለተባለችው ሴት እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋም ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት።” (ሥራ 16:13-15) እንደ ሊዲያ ሁሉ በዛሬው ጊዜም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይሖዋ እየሳባቸው ነው።
16. በአገልግሎት ላይ ለምናገኘው ማንኛውም ስኬት ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው?
16 በአገልግሎት ላይ ለምናገኘው ማንኛውም ስኬት ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤን በተመለከተ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቶናል፤ “እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤ ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በአገልግሎታችን ለምናገኘው ማንኛውም ስኬት ሁልጊዜ እውቅና ልንሰጥ የሚገባው ለይሖዋ ነው።
17. ከአምላክ፣ ከክርስቶስና ከመላእክት ጋር ‘አብረን የመሥራት’ መብታችንን እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 ከአምላክ፣ ከክርስቶስና ከመላእክት ጋር ‘አብረን የመሥራት’ መብታችንን እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈል የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በትጋት በመፈለግ ነው። ይህን ማድረግ የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ ለምሳሌ “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” መስበክ እንችላለን። (ሥራ 20:20) ብዙዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድም ይመሠክራሉ። እነዚህ አስፋፊዎች፣ ለአንድ ሰው ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ከግለሰቡ ጋር ውይይት ለመጀመር ጥረት ያደርጋሉ። ግለሰቡ ጥሩ ምላሽ ከሰጠ የመንግሥቱን መልእክት በዘዴ ይነግሩታል።
18-19. (ሀ) የእውነትን ዘሮች ውኃ ማጠጣት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የረዳው እንዴት ነው?
18 “ከአምላክ ጋር አብረን” ስንሠራ የእውነትን ዘር መዝራት ብቻ ሳይሆን ማጠጣትም አለብን። አንድ ሰው ፍላጎት እንዳለው ካስተዋልን፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ወይም ሌላ ሰው ግለሰቡን እንዲረዳው ለማመቻቸት እንጥራለን፤ ዓላማችን ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር መርዳት ነው። ግለሰቡ በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ በአስተሳሰቡና በዝንባሌው ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ይሖዋ ይረዳዋል፤ ይህን የማየት አጋጣሚ ማግኘታችን ያስደስተናል።
19 በደቡብ አፍሪካ የሚኖር ጠንቋይ የነበረን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና በተማረው ነገር በጣም ተደሰተ። ይሁንና የአምላክ ቃል የሞቱ ሰዎችን ማነጋገርን በተመለከተ ምን እንደሚል ሲማር ከባድ ፈተና ገጠመው። (ዘዳ. 18:10-12) ውሎ አድሮ ግን አምላክ አስተሳሰቡን እንዲቀርጽለት ፈቃደኛ ሆነ። ከጊዜ በኋላ የጥንቆላ ሥራውን አቆመ፤ እርግጥ ይህን ማድረጉ መተዳደሪያውን አሳጥቶታል። በአሁኑ ወቅት 60 ዓመት የሆነው ይህ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ መንገዶች ላደረጉልኝ እርዳታ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ለምሳሌ ሥራ እንዳገኝ ረድተውኛል። ከሁሉ በላይ ግን በሕይወቴ ላይ ለውጥ እንዳደርግ የረዳኝን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ፤ ከተጠመቁ ምሥክሮቹ አንዱ ሆኜ ላገለግለው የቻልኩት እሱ ስለረዳኝ ነው።”
20. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
20 በዚህ ርዕስ ላይ በዓይን የማይታዩ አራት ሀብቶች ተብራርተዋል። ከእነዚህ ሀብቶች ሁሉ የላቀው፣ ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው የጠበቀ ወዳጅነት ነው። ይህ ሀብት ሌሎቹን በዓይን የማይታዩ ውድ ሀብቶች ለማግኘት አስችሎናል፤ እነዚህ ሀብቶች አምላክን በጸሎት የማነጋገር መብት፣ የቅዱስ መንፈሱ እርዳታ እንዲሁም አገልግሎታችንን ስናከናውን ከሰማይ የምናገኘው ድጋፍ ናቸው። እንግዲያው ለእነዚህ በዓይን የማይታዩ ሀብቶች ያለንን አድናቆት እያሳደግን ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲሁም ይሖዋ ከእሱ ጋር እንዲህ ያለ አስደናቂ ወዳጅነት እንድንመሠርት ስለፈቀደልን ምንጊዜም እሱን እናመስግን።
መዝሙር 145 አምላክ የሰጠው የገነት ተስፋ
^ አን.5 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ፣ ከአምላክ ስላገኘናቸው በዓይን የሚታዩ አንዳንድ ውድ ሀብቶች ተመልክተናል። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ በዓይን ስለማይታዩ ውድ ሀብቶች እንመለከታለን፤ በተጨማሪም ለእነዚህ ውድ ሀብቶች አድናቆታችንን እንዴት ማሳየት እንደምንችል እናያለን። ይህ ርዕስ እንዲህ ያሉት ውድ ሀብቶች ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ያለንን አድናቆት ለማሳደግም ይረዳናል።
^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ (1) አንዲት እህት የይሖዋን የፍጥረት ሥራ እየተመለከተች ከእሱ ጋር ስለመሠረተችው ወዳጅነት ስታሰላስል።
^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ (2) ይህችው እህት ለመመሥከር የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጣት ወደ ይሖዋ ስትጸልይ።
^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ (3) ይህች እህት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የመንግሥቱን መልእክት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ድፍረት አገኘች።
^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ (4) እህት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመሠከረችላትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና። እህታችን በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስትካፈል የመላእክትን ድጋፍ አግኝታለች።