“ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ርኅራኄ አሳዩ
ኢየሱስ ምሥራቹን እንዴት መስበክ እንዳለባቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ ተናግሯል። (ሉቃስ 10:3, 5, 6) በአገልግሎታችን ላይ የሚሳደቡ አልፎ ተርፎም የኃይል ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ርኅራኄ ማሳየት ከባድ እንዲሆንብን እንደሚያደርግ አይካድም።
ሩኅሩኅ የሆነ ሰው ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ነገርና ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስተውላል፤ ይህም እንዲያዝንላቸውና እነሱን ለመርዳት እንዲነሳሳ ያደርገዋል። ሆኖም ለምንሰብክላቸው ሰዎች ያለን ርኅራኄ እየቀነሰ ከመጣ በአገልግሎት ላይ የምናሳየው ቅንዓትና የምናገኘው ውጤትም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል። በሌላ በኩል ደግሞ በሚነድ እሳት ላይ ማገዶ ስንጨምር እሳቱ ይበልጥ እንደሚቀጣጠል ሁሉ ርኅራኄ ስናዳብርም ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት ይበልጥ ይቀጣጠላል!—1 ተሰ. 5:19
ርኅራኄ ማሳየት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ይሖዋ፣ ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ይሖዋን ምሰሉ
ይሖዋ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በስሙ ላይ ሲሰነዘር የቆየውን ነቀፋ ችሎ መኖር አስፈልጎታል። ያም ቢሆን “ለማያመሰግኑና ለክፉዎች [ደግነት]” ማሳየቱን ቀጥሏል። (ሉቃስ 6:35) ደግነቱን ያሳየበት አንዱ መንገድ ታጋሽ በመሆን ነው። ይሖዋ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ” ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) አምላክ ክፋትን የሚጠላ ቢሆንም የሰዎችን ሕይወት ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም።—2 ጴጥ. 3:9
ይሖዋ፣ ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች በማሳወር ረገድ ምን ያህል እንደተሳካለት ያውቃል። (2 ቆሮ. 4:3, 4) በርካታ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የተሳሳቱ ትምህርቶችን ስለተማሩና መጥፎ ዝንባሌዎችን ስላዳበሩ እውነትን መቀበል ከባድ ይሆንባቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ሰዎች የመርዳት ፍላጎት አለው። ይህን እንዴት እናውቃለን?
ይሖዋ ለጥንቶቹ የነነዌ ሰዎች የነበረውን አመለካከት እናስብ። እነዚህ ሰዎች ዓመፀኞች የነበሩ ቢሆንም ይሖዋ እነሱን አስመልክቶ ለዮናስ እንዲህ ብሎታል፦ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተው የማያውቁ ከ120,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችና በርካታ እንስሶቻቸው ለሚኖሩባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ ላዝን አይገባም?” (ዮናስ 4:11) ይሖዋ የነነዌ ሰዎች በመንፈሳዊ እንደተጎዱ ስለተገነዘበ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ዮናስን በመላክ ምሕረት አሳይቷቸዋል።
እኛም ልክ እንደ ይሖዋ የሰዎችን ሕይወት ከፍ አድርገን እንመለከታለን። ለመልእክታችን አዎንታዊ ምላሽ አይሰጡም ብለን የምናስባቸውን ሰዎች ጭምር በቅንዓት በመርዳት እሱን መምሰል እንችላለን።
ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ምሰሉ
እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም በመንፈሳዊ ለተጎዱ ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። “[ሕዝቡን] ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) ኢየሱስ ከላይ ከሚታየው ነገር አልፎ ይመለከት ነበር፤ እሱ ሲናገር ለማዳመጥ የመጡት ሰዎች የሐሰት ትምህርቶችን እንደተማሩና በሃይማኖት መሪዎቻቸው በደል እንደደረሰባቸው አስተውሏል። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ፣ እንቅፋት ሊሆኑባቸው በሚችሉ የተለያዩ ነገሮች የተነሳ አዎንታዊ ምላሽ እንደማይሰጡ ቢያውቅም ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’—ማር. 4:1-9
ሰዎች ለመልእክታችን አዎንታዊ ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜ ከላይ ከሚታየው ነገር አልፈን በመሄድ እንደዛ ያለ ምላሽ የሰጡበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለብን። አንዳንዶች ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች
የሚያደርጓቸውን መጥፎ ነገሮች ማየታቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ስለ ክርስትና አሉታዊ አመለካከት እንዲያድርባቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ስለምናምንባቸው ነገሮች የሐሰት ወሬ ሰምተው ይሆናል። ማኅበረሰቡ ወይም የቤተሰባቸው አባላት እንዳያገሏቸው በመፍራት ለመልእክታችን አሉታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችም አሉ።በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ምላሽ የማይሰጡት በሕይወታቸው ውስጥ በደረሰባቸው አሳዛኝ ነገር የተነሳ ስሜታቸው ስለተጎዳ ሊሆን ይችላል። ኪም የተባለች አንዲት ሚስዮናዊት እንዲህ ብላለች፦ “በምንሰብክበት አንድ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች በጦርነት ምክንያት ንብረታቸውን ሁሉ አጥተዋል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ተስፋ የላቸውም። ብስጩዎች ከመሆናቸውም ሌላ ሰዎችን ለማመን ይቸገራሉ። በዚህ ክልል ውስጥ ብዙውን ጊዜ መልእክታችንን የሚቃወሙ ሰዎች ያጋጥሙናል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ስሰብክ የኃይል ጥቃት ተሰንዝሮብኛል።”
ኪም እንዲህ ባለ ሁኔታ ሥር ርኅራኄ ማሳየቷን እንድትቀጥል የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች ሲያመናጭቁኝ በምሳሌ 19:11 ላይ የሚገኘውን ‘ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል’ የሚለውን ጥቅስ ለማስታወስ እሞክራለሁ። በክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ያሳለፉትን ሕይወት ማስታወሴ ርኅራኄ እንዳሳያቸው ይረዳኛል። ደግሞም የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ተቃዋሚዎች አይደሉም። በዚያው ክልል ውስጥ ጥሩ ጥሩ ተመላልሶ መጠየቆች አሉን።”
ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘እኔ በሰዎቹ ቦታ ብሆን ኖሮ ለመንግሥቱ መልእክት ምን ምላሽ እሰጥ ነበር?’ ለምሳሌ ያህል፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ ወሬ ሰምተናል እንበል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ሥር እኛም አሉታዊ ምላሽ ልንሰጥ ስለምንችል ሌሎች ርኅራኄ እንዲያሳዩን እንፈልጋለን። ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር እኛም ልናደርግላቸው እንደሚገባ የሚገልጸውን የኢየሱስን ትእዛዝ ማስታወሳችን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳ የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት እንድናደርግና ርኅራኄ እንድናሳይ ያነሳሳናል።—ማቴ. 7:12
ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ጳውሎስን ምሰሉ
ሐዋርያው ጳውሎስ የኃይል ጥቃት ለሰነዘሩበት ተቃዋሚዎች እንኳ ሳይቀር ርኅራኄ አሳይቷል። ለምን? እሱ ራሱ ቀደም ሲል ምን ዓይነት ሰው እንደነበር አልረሳም። እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም . . . ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል።” (1 ጢሞ. 1:13) ይሖዋና ኢየሱስ ታላቅ ምሕረት እንዳሳዩት ተገንዝቧል። ከሚሰብክላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እሱ በአንድ ወቅት የነበረውን ዓይነት ስሜት እያንጸባረቁ እንዳሉ ሳያስተውል አልቀረም።
ጳውሎስ ከሰበከላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በሐሰት ትምህርቶች የተተበተቡ ነበሩ። ጳውሎስ ሰዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ሲመለከት ምን ተሰማው? ሥራ 17:16 በአቴንስ ሳለ “ከተማዋ በጣዖት የተሞላች መሆኗን አይቶ መንፈሱ ተረበሸ” ይላል። ሆኖም ጳውሎስ ስሜቱ እንዲረበሽ ያደረገውን ያንኑ ሁኔታ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ተጠቅሞበታል። (ሥራ 17:22, 23) “በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን [ለማዳን]” ሲል የስብከት ዘዴውን እንደየሰዎቹ ሁኔታ ይቀያይር ነበር።—1 ቆሮ. 9:20-23
በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥሙን ሰዎች የሚሰጡትን አሉታዊ ምላሽ ወይም የሚያምኑባቸውን የተሳሳቱ ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ [የሚገልጸውን] ምሥራች” በዘዴ በማስተዋወቅ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ኢሳ. 52:7) ዶረቲ የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በክልላችን ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ ጨካኝና ምክንያታዊነት የጎደለው እንደሆነ ተምረዋል። እንዲህ የሚሰማቸው ሰዎች ሲያጋጥሙኝ በቅድሚያ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ስላላቸው አድናቆቴን እገልጽላቸዋለሁ፤ ከዚያም አምላክ አፍቃሪ እንደሆነና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስደሳች ተስፋ እንደሰጠን በሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እረዳቸዋለሁ።”
“ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ”
ወደ “መጨረሻዎቹ ቀናት” መገባደጃ ይበልጥ እየተጠጋን በሄድን መጠን ከምንሰብክላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1, 13) ሆኖም የሰዎች ባሕርይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ መሄዱ ርኅራኄ ከማሳየት ወደኋላ እንድንል እንዲያደርገን ወይም ደስታችንን እንዲያሳጣን መፍቀድ አይኖርብንም። ይሖዋ “ምንጊዜም ክፉውን በመልካም [እንድናሸንፍ]” የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። (ሮም 12:21) ጄሲካ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “አብዛኛውን ጊዜ፣ ትሕትና የጎደላቸውና ለእኛም ሆነ ለመልእክታችን አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ያጋጥሙኛል። ይህ የሚያበሳጭ እንደሆነ አይካድም። አንድን ሰው ሳነጋግር ይሖዋ ለግለሰቡ ያለውን ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንድችል በልቤ እጸልያለሁ። ይህም በራሴ ስሜት ላይ ከማተኮር ይልቅ ግለሰቡን መርዳት በምችልበት መንገድ ላይ እንዳተኩር ይረዳኛል።”
በተጨማሪም አብረውን የሚያገለግሉትን ወንድሞችና እህቶች ማበረታታት የምንችልበትን መንገድ ማሰብ ይኖርብናል። ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “ከመካከላችን አንዳችን በአገልግሎት ላይ መጥፎ ነገር ካጋጠመን በዚያ ላይ ላለማተኮር ጥረት አደርጋለሁ። ውይይቱን አዎንታዊ ወደሆነ ርዕሰ ጉዳይ ለመቀየር፣ ለምሳሌ አንዳንዶች አሉታዊ ምላሽ ቢሰጡም አገልግሎታችን በሚያስገኘው ጥሩ ውጤት ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ።”
ይሖዋ በአገልግሎት ላይ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን ጠንቅቆ ያውቃል። ምሕረት በማሳየት ረገድ የእሱን ምሳሌ ስንከተል ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ሉቃስ 6:36) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የሚያሳየው ርኅራኄ የጊዜ ገደብ አለው። ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን የስብከት ሥራችንን በጥድፊያ ስሜት ማከናወናችን አስፈላጊ ነው። (2 ጢሞ. 4:2) “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ በማሳየት፣ የተሰጠንን ኃላፊነት በቅንዓት መወጣታችንን እንቀጥል።