በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 30

ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችን ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው?

ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችን ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው?

“በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ።”—1 ቆሮ. 9:22

መዝሙር 82 “ብርሃናችሁ ይብራ”

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ አገሮች ምን ዓይነት ለውጥ እየታየ ነው?

ላለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት በዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖት ነበራቸው። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው። ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖት እንደሌላቸው በግልጽ ይናገራሉ። *ማቴ. 24:12

2. ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው?

2 ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው? * አንዳንዶች ሕይወታቸው ያተኮረው ተድላን በማሳደድ ላይ ስለሆነ ወይም የኑሮ ጭንቀት ትኩረታቸውን ስለከፋፈለባቸው ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 8:14) ቀደም ሲል ሃይማኖተኛ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በአምላክ መኖር ማመናቸውን ትተዋል። ሌሎች በአምላክ መኖር ቢያምኑም ሃይማኖት ጊዜ ያለፈበት፣ አላስፈላጊ እንዲሁም ከሳይንስና ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ከጓደኞቻቸውና ከአስተማሪዎቻቸው አሊያም ከመገናኛ ብዙኃን ይሰማሉ፤ በአምላክ መኖር ለማመን የሚያበቃ አሳማኝ ማስረጃ ግን አግኝተው አያውቁም። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ገንዘብና ሥልጣን ለማግኘት በሚስገበገቡ የሃይማኖት መሪዎች ድርጊት የተነሳ ሃይማኖትን ጠልተዋል። በአንዳንድ አገሮች፣ መንግሥታት በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥለዋል።

3. የዚህ ርዕስ ዓላማ ምንድን ነው?

3 ኢየሱስ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት” እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (ማቴ. 28:19) ታዲያ ሃይማኖት የሌላቸውን ሰዎች አምላክን እንዲወዱና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው ያደገበት አካባቢ ለመልእክታችን በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ እንደሚችል መገንዘብ አለብን። ለምሳሌ፣ በአውሮፓ ያደገ ሰው የሚሰጠው ምላሽ ከእስያ የመጣ ሰው ከሚሰጠው ምላሽ የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምን? በአውሮፓ የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰነ ደረጃ ያውቃሉ፤ እንዲሁም ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ሲነገር ሰምተዋል። እስያ ውስጥ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ቢያውቁ እንኳ እውቀታቸው አነስተኛ ነው፤ በፈጣሪ መኖርም ላያምኑ ይችላሉ። የዚህ ርዕስ ዓላማ፣ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ያደጉበት አካባቢ የትም ሆነ የት የሁሉንም ዓይነት ሰዎች ልብ መንካት እንድንችል መርዳት ነው።

አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ

4. አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚያበቃ ምን ምክንያት አለን?

4 አዎንታዊ ሁኑ። ሃይማኖት የሌላቸው በርካታ ሰዎች በየዓመቱ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ቀድሞውንም ቢሆን ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ በሃይማኖቶች ውስጥ በሚያዩት ግብዝነት ይመረሩ ነበር። ሌሎቹ ግን ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸው ነበሩ፤ ብዙዎቹ መጥፎ ልማዶቻቸውን ማስወገድ አስፈልጓቸዋል። በእርግጥም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን በይሖዋ እርዳታ እንደምናገኝ መተማመን እንችላለን።—ሥራ 13:48፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4

በመጽሐፍ ቅዱስ ለማያምኑ ሰዎች ስትመሠክር ምሥራቹን የምትሰብክበትን መንገድ እንደ ሁኔታው አስተካክል (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት) *

5. አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መልእክታችንን እንዲያዳምጡ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

5 ደግና ዘዴኛ ሁኑ። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መልእክታችንን እንዲያዳምጡ የሚያደርጋቸው የምንናገረው ነገር ሳይሆን የምንናገርበት መንገድ ነው። በደግነትና በዘዴ ከያዝናቸው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ እንደምናስብላቸው ከተሰማቸው ደስ ብሏቸው ያዳምጡናል። የእኛን አመለካከት እንዲያዳምጡ አናስገድዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ስለ ሃይማኖት ያላቸውን አመለካከት ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ከማያውቁት ሰው ጋር ስለ ሃይማኖት ማውራት አይፈልጉም። ሌሎች ደግሞ ስለ አምላክ ምን አመለካከት እንዳላቸው ሰዎችን መጠየቅ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። አንዳንዶች፣ በተለይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ መታየት ያሳፍራቸዋል። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ስሜታቸውን ለማክበር ጥረት እናደርጋለን።—2 ጢሞ. 2:24 ግርጌ

6. ሐዋርያው ጳውሎስ የሰዎችን ሁኔታ ከግምት እንደሚያስገባ ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

6 ከአንድ ሰው ጋር ስንወያይ “መጽሐፍ ቅዱስ፣” “ፍጥረት፣” “አምላክ” ወይም “ሃይማኖት” እንደሚሉት ያሉትን ቃላት መጠቀማችን እንዳላስደሰተው ካስተዋልን ምን ማድረግ እንችላለን? የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ሰዎቹን የምናነጋግርበትን መንገድ ማስተካከል እንችላለን። ጳውሎስ ከአይሁዳውያን ጋር ሲወያይ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳ ነበር። በአርዮስፋጎስ ከግሪክ ፈላስፎች ጋር ሲወያይ ግን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አልጠቀሰም። (ሥራ 17:2, 3, 22-31) እኛስ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የምናነጋግረው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ከሆነ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አለመጥቀሳችን የተሻለ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ መታየት እንደጨነቀው ከተሰማን ደግሞ ትኩረት በማይስብ መንገድ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ጥቅሱን ልናሳየው እንችላለን።

7. አንደኛ ቆሮንቶስ 9:20-23 እንደሚጠቁመው የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

7 የሌሎችን አመለካከት የምትረዱና ጥሩ አድማጭ ሁኑ። በምናነጋግራቸው ሰዎች አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩትን ነገሮች ለመረዳት መሞከር ይኖርብናል። (ምሳሌ 20:5) እስቲ የጳውሎስን ምሳሌ እንደገና እንመልከት። ጳውሎስ ያደገው በአይሁዳውያን መካከል ነው። በመሆኑም ለአሕዛብ ሲሰብክ፣ የሚሰብክበትን መንገድ ማስተካከል አስፈልጎት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢያውቁ እንኳ እውቀታቸው በጣም ውስን ነው። እኛም በክልላችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች አመለካከትና ስሜት መረዳት እንድንችል ምርምር ማድረግ አሊያም በጉባኤያችን የሚገኙ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖችን ማማከር ያስፈልገን ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23ን አንብብ።

8. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጀመር የሚያስችለው አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

8 ዓላማችን “መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው” ማግኘት ነው። (ማቴ. 10:11) በዚህ ረገድ ውጤታማ ለመሆን፣ ሰዎች አመለካከታቸውን እንዲገልጹ መጠየቅ ከዚያም በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል። በእንግሊዝ የሚኖር አንድ ወንድም ሰዎችን በሚያነጋግርበት ጊዜ የትዳር ሕይወትን አስደሳች ማድረግ፣ ጨዋ ልጆች ማሳደግ አሊያም ደግሞ ግፍ ሲፈጸምብን መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አመለካከታቸውን ይጠይቃቸዋል። የሚሰጡትን ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ “ከዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በፊት የተጻፈ ምክር ባሳይህ ደስ ይለኛል” ይላቸዋል። ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ እንደሆነ ሳይናገር፣ አስቀድሞ የተዘጋጃቸውን ጥቅሶች ከስልኩ ላይ ያሳያቸዋል።

የሰዎችን ልብ ለመንካት ጥረት አድርጉ

9. ስለ አምላክ መወያየት የማይፈልጉ ሰዎችን መርዳት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

9 ስለ አምላክ መወያየት የማይፈልጉ ሰዎችን ልብ ለመንካት፣ የእነሱን ትኩረት የሚስቡ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳት እንችላለን። ለምሳሌ፣ ብዙዎች ተፈጥሮን ያደንቃሉ። ስለዚህ እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “የሳይንስ ሊቃውንት አዳዲስ ነገሮችን ሲፈለስፉ ብዙውን ጊዜ ተፈጥሮን እንደሚኮርጁ ታውቅ ይሆናል። ለምሳሌ፣ የድምፅ ማጉያ የሚሠሩ ሰዎች ስለ ጆሮ ያጠናሉ፤ ካሜራ የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ስለ ዓይን ያጠናሉ። አንተ ተፈጥሮን ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ተፈጥሮ በአጋጣሚ የተገኘ ነገር ነው? ወይስ ፈጣሪ አለው?” ግለሰቡ የሚሰጠንን ምላሽ በጥሞና ካዳመጥን በኋላ እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ “መሐንዲሶች ጆሮንና ዓይንን በማጥናት አዲስ ነገር ሲፈጥሩ እየኮረጁ ያሉት ማን ያወጣውን ንድፍ ነው? በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ገጣሚ የጻፈው ሐሳብ ይገርመኛል፤ ‘ጆሮን ያበጀው እሱ መስማት አይችልም? ወይስ ዓይንን የሠራው እሱ ማየት አይችልም? . . . ለሰዎች እውቀት የሚሰጠው እሱ ነው!’ ብሏል። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ከዚህ ገጣሚ ጋር ይስማማሉ።” (መዝ. 94:9, 10) ከዚያም jw.org® ላይ “ቃለ መጠይቅ እና ተሞክሮ” በሚለው ዓምድ ሥር “ስለ ሕይወት አመጣጥ የተሰጡ አስተያየቶች” በሚለው ሥር ካሉት ቪዲዮዎች አንዱን ልናሳየው እንችላለን። (የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ተመልከት።) አሊያም ደግሞ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? ወይም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች ከተባሉት ብሮሹሮች አንዱን ልንሰጠው እንችላለን።

10. ስለ አምላክ መወያየት ከማይፈልግ ሰው ጋር ውይይት መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?

10 ብዙ ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ይመኛሉ። ይሁንና ብዙዎች ምድር ትጠፋለች ወይም ለመኖሪያነት የማትመች ቦታ ትሆናለች ብለው ይሰጋሉ። በኖርዌይ የሚያገለግል አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንደተናገረው ስለ አምላክ መወያየት የማይፈልጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ዓለም ሁኔታ ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው። ይህ ወንድም ሰዎችን ሲያነጋግር ሰላምታ ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ ይላቸዋል፦ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚሰማህ ማወቅ ፈልጌ ነበር። የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ የሚችለው ማን ይመስልሃል? ፖለቲከኞች፣ የሳይንስ ሊቃውንት ወይስ ሌሎች?” የሚሰጡትን ምላሽ በትኩረት ካዳመጠ በኋላ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገር ጥቅስ ያነብላቸዋል አሊያም ጥቅሱን በቃሉ ይነግራቸዋል። ምድር እንደማትጠፋ እንዲሁም ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የአንዳንዶችን ትኩረት ይስባል።—መዝ. 37:29፤ መክ. 1:4

11. ምሥራቹን በተለያየ መንገድ ለመስበክ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? በሮም 1:14-16 ላይ የተገለጸውን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

11 በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ስናነጋግር ምሥራቹን በተለያየ መንገድ ለመስበክ ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። ለምን? ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ነው። የአንዳንዶችን ትኩረት የሚስበው ነገር ሌሎችን ላያስደስታቸው ይችላል። አንዳንድ ሰዎችን በቀጥታ ስለ አምላክ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብናወያያቸው አይከብዳቸው ይሆናል፤ ሌሎችን ግን መጀመሪያ ላይ ስለ ሌሎች ጉዳዮች ብናወያያቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለማነጋገር ጥረት ማድረግ አለብን። (ሮም 1:14-16ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ የጽድቅ ዝንባሌ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እውነት እንዲያድግ የሚያደርገው ይሖዋ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም።—1 ቆሮ. 3:6, 7

ከእስያ ለመጡ ሰዎች እውነትን መንገር

በርካታ የመንግሥቱ አስፋፊዎች፣ ክርስቲያን ካልሆኑ አገሮች ለመጡ ሰዎች ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ለዕለታዊ ሕይወት የሚጠቅም ምክር ያካፍሏቸዋል (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)

12. ከእስያ የመጡና ፈጣሪ ሊኖር እንደሚችል ጨርሶ አስበው የማያውቁ ሰዎችን ልብ ለመንካት ምን ማድረግ እንችላለን?

12 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አስፋፊዎች ከተለያዩ የእስያ አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር ይገናኛሉ፤ አንዳንዶቹ የመጡት መንግሥታት በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደቦች ከጣሉባቸው አገሮች ነው። በበርካታ የእስያ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ፈጣሪ ሊኖር እንደሚችል ጨርሶ አስበው አያውቁም። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ የማወቅ ጉጉት ስላላቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ቀጥተኛ ግብዣ ይቀበላሉ፤ ሌሎች ግን አዲስ ነገር ለመማር መጀመሪያ ላይ ያመነታሉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን ልብ ለመንካት ምን ማድረግ እንችላለን? ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ አስፋፊዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ሆኖ ያገኙት ዘዴ አለ፤ መጀመሪያ ላይ ሰዎቹን ስለ ሌሎች ጉዳዮች የሚያዋሯቸው ሲሆን በግለሰብ ደረጃ ለእነሱ አሳቢነት ያሳዩዋቸዋል፤ ከዚያም አጋጣሚው ሲመቻች፣ አስፋፊዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋቸው ሕይወታቸው እንዲሻሻል የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ይነግሯቸዋል።

13. ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው የሚችለው ምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮች የብዙዎችን ትኩረት ይስባሉ። (መክ. 7:12) ኒው ዮርክ ውስጥ ቻይንኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች የምትሰብክ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለሰዎቹ አሳቢነት ለማሳየትና የሚናገሩትን ለማዳመጥ ጥረት አደርጋለሁ። ወደዚህ አካባቢ የመጡት በቅርቡ እንደሆነ ካስተዋልኩ ‘እየለመዳችሁ ነው? ሥራ ማግኘት ቻላችሁ? ከአካባቢው ሰዎች ጋር እየተግባባችሁ ነው?’ ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።” እንዲህ ማድረጓ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለእነሱ ለማካፈል አጋጣሚ የሚከፍትበት ጊዜ አለ። ይህች እህት አጋጣሚው ሲመቻች፣ የምታነጋግረውን ሰው እንዲህ ትለዋለች፦ “ከሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ቁልፉ ምን ይመስልሃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ ላሳይህ? ምሳሌው ‘ጠብ መጫር ግድብን ከመሸንቆር ተለይቶ አይታይም፤ ስለዚህ ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ’ ይላል። ይህ ምክር ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚረዳን ይመስልሃል?” (ምሳሌ 17:14) እንዲህ ያሉ ውይይቶች፣ ሌላ ጊዜ ተመልሰን እንድናነጋግራቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ለይተን እንድናውቅ ይረዱናል።

14. በሩቅ ምሥራቅ የሚኖር አንድ ወንድም በአምላክ መኖር እንደማያምኑ የሚናገሩ ሰዎችን የሚረዳው እንዴት ነው?

14 በአምላክ መኖር እንደማያምኑ የሚናገሩ ሰዎች ካጋጠሙንስ? በሩቅ ምሥራቅ ለሚኖሩ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች በመስበክ ብዙ ተሞክሮ ያካበተ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ፣ በዚህ አካባቢ የሚኖር ሰው ‘በአምላክ አላምንም’ ሲል በአካባቢው ያሉ በርካታ ሰዎች የሚያመልኳቸውን አማልክት እንደማያመልክ መናገሩ ነው። ስለዚህ እኔም አብዛኞቹ አማልክት ሰዎች የፈጠሯቸው እንደሆኑና እውነተኛ እንዳልሆኑ እነግረዋለሁ። ከዚያም ‘ሰው ለራሱ አማልክት ሊሠራ ይችላል? የሚሠራቸው አማልክት እውነተኛ አማልክት አይደሉም’ የሚለውን በኤርምያስ 16:20 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነብለታለሁ። ቀጥሎም ‘እውነተኛውን አምላክ ሰዎች ከሠሯቸው አማልክት መለየት የምንችለው እንዴት ነው?’ ብዬ እጠይቀዋለሁ። የሚሰጠውን ምላሽ በጥሞና ካዳመጥኩ በኋላ ‘አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ንገሩን’ የሚለውን በኢሳይያስ 41:23 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አነብለታለሁ። ከዚያም ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከተናገራቸው ትንቢቶች አንዱን አሳየዋለሁ።”

15. በምሥራቅ እስያ የሚኖር አንድ ወንድም ከሚያደርገው ነገር ምን እንማራለን?

15 በምሥራቅ እስያ የሚኖር አንድ ወንድም ደግሞ ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርግ የሚከተለውን ዘዴ ይጠቀማል። እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች፣ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሕጎች አሳያቸዋለሁ። ከዚያም እነዚህ ነገሮች፣ ሕያውና ጥበበኛ የሆነ ፈጣሪ ለመኖሩ እንዴት ማስረጃ እንደሚሆኑ አስረዳቸዋለሁ። አንድ ሰው የአምላክን መኖር በተመለከተ አመለካከቱ በተወሰነ መጠን እየተለወጠ እንደሆነ ካስተዋልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚል አሳየዋለሁ።”

16. በዕብራውያን 11:6 ላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ማዳበር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና፣ ስለ አምላክ መኖር ያላቸው እምነት እንዲጠናከር አዘውትረን ልንረዳቸው ይገባል። (ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው መርዳታችን አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ስለ አንዳንድ ትምህርቶች በተደጋጋሚ ጊዜ መወያየት ሊያስፈልገን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ላይ ማንሳት ይኖርብን ይሆናል። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች እንደያዘ፣ ከሳይንስና ከታሪክ አንጻር ትክክል እንደሆነ ወይም ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮች እንዳሉት ጠቅሰን በአጭሩ መወያየት እንችላለን።

17. ለሰዎች ፍቅር ማሳየታችን ምን ውጤት አለው?

17 ሃይማኖት ላላቸውም ሆነ ለሌላቸው ሰዎች ፍቅር በማሳየት፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ልንረዳቸው እንችላለን። (1 ቆሮ. 13:1) እነዚህን ሰዎች ስናስተምር ዓላማችን አምላክ እንደሚወዳቸውና እነሱም እንዲወዱት እንደሚፈልግ እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። ስለ ሃይማኖት ግድ ያልነበራቸው ወይም ሃይማኖት የለሽ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር ማዳበር ስለቻሉ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠምቀዋል። ስለዚህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑረን፤ እንዲሁም ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅርና አሳቢነት እናሳይ። ሰዎችን እናዳምጥ። ስሜታቸውንና አመለካከታቸውን ለመረዳት ጥረት እናድርግ። ጥሩ ምሳሌ በመሆን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እናስተምራቸው።

መዝሙር 76 ምን ይሰማሃል?

^ አን.5 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ በአገልግሎት ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች እናገኝ ይሆናል። ለእነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መንገር እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ እና በይሖዋ ላይ እምነት እንዲጥሉ እነሱን መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይህ ርዕስ ያብራራል።

^ አን.1 ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከእነዚህ አገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ሆንግ ኮንግ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ስፔን፣ ቻይና፣ ቼክ ሪፑብሊክ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ አልባኒያ፣ አውስትራሊያ፣ አዘርባጃን፣ አየርላንድ፣ እስራኤል፣ ኦስትሪያ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ቬትናም።

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች የሚለው አገላለጽ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎችንም ይጨምራል።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ሆስፒታል ውስጥ አብሮት ለሚሠራ ሰው ሲመሠክር፤ በኋላ ላይ ሰውየው jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን ይጎበኛል።